በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1219 ዕድሜያችን መድረሱ ተረጋግጦ የጋብቻ ይፈቀድልን ጥያቄዎች በየደረጃው ባሉ የፍትህ ተቋማት መቅረቡን የክልሉ ፍትህ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አለምሸት ካሳው ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የንቃተ ህግ ከሚሰራባቸው ዘርፎች መካካል የሕፃናት ጋብቻ ወይም ያለዕድሜ ጋብቻ አንዱ ነው። በአማራ ክልል ያለዕድሜ ጋብቻ ወይም ከህፃናት ጋብቻ ጋር በተያያዘ በሴክተሮች ቅንጅታዊ አሰራር በርካታ ተግባራት መከናወኑም ተነግሯል።
እንደ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ማብራሪያ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ለፍትህ ተቋማት የሚቀርቡት ወላጆች ልጆቻቸውን ለመዳር ካላቸው ፍላጎትና ዕድሜያቸው ለጋብቻ ያልደረሱ ህፃናት ጋብቻ በህግ የተከለከለ እና ተፈፅሞ ሲገኝ የዕርምት ርምጃ የሚያስወስድ በመሆኑ ነው ብለዋል።
እንደ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተጋቢዎች እድሜያቸው መድረሱ ወይም አለመድረሱ የሚያጠራጥር ከሆነ በጤና ተቋማት በሚደረግ ምርመራ የሚረጋገጥ ይሆናል ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል 438ቱ ለአቅመ ጋብቻ መድረሳቸው በጤና ተቋም በተደረገ ምርመራ በመረጋገጡ ጋብቻ እንዲፈፅሙ እንደተፈቀደላቸው ታውቋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በዘጠኝ ወሩ ከቀረቡ ጥቄዎች መካካል 495ቱ በተደረገላቸው ምርመራ ለአቅም ጋብቻ ያልደረሱ መሆኑ በጤና ተቋማት የተረጋጋጠ በመሆኑ ጋብቻው ቢፈፀም የሚያደርሰውን መጠነ ሰፊ ጉዳት በማስገንዘብ ጋብቻው አንዳይፈፀም ተደርጓል።
እንደ ክልሉ ፍትህ ቢሮ መረጃ ለአቅመ ጋብቻ አለመድረሳቸው በጤና ተቋማት ተረጋግጦ ጋብቻው ቢፈፀም የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለማሰገንዘዝብ ጥረት ቢደረግም ይህን ችላ ብለው ጋብቻቸውን የፈፀሙ 78 ተጋቢዎች ላይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ክስ በመመስረት ዘጠኙን ማስቀጣት የተቻለ ሲሆን የቀሪዎቹ ጉዳይ በክርክር ሂደት ላይ ይገኛል።
የክልሉ ሴቶች ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ያለፉት ዘጠኝ ወራት ሪፖርት አንደሚያመለክተው በአጠቃላይ በከልሉ 4741 የልጅነት ጋብቻ ጥቆማዎች የደረሱ ሲሆን 1246ቱ በድርድር አንዳይፈፀሙ ማቋረጥ የተቻለ ሲሆን 825ቱ በጤና ተቋማት የእድሜ ምርመራ አድርገው እድሜያቸው የደረሰ መሆኑ ስለተረጋገጠ ጋብቻ እንዲፈፅሙ ተደርጓል፡፡
እንደ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ማብራሪያ ያለዕድሜ ጋብቻ የሚፈፀምበት ምክንያት በጥናት መለየት ያለበት ሆኖ በዋነኝነት ግን በተለምዶ በወላጆች መካከል ዝምድና ለመፍጠር ልጆችን ማጋባት በምክንያትንት ሊጠቀስ ይችላል ይላሉ፡፡
በማስቀጣት ሂደቱ ወላጆች የገንዘብ እና ሌሎች አስተማሪ ቅጣቶች የሚወሰንባቸው ሲሆን ጋብቻ የፈፀሙ ህፃናት ተጋቢዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ከነበረ ወደ ትምህርት ገበታቸው አንዲመለሱ እንደሚደረግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስረድተዋል።
እንደ አቶ አለምሽት ማብራሪያ የህጻናት ጋብቻ የሚፈጸምበት መንገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስልቱን እየቀየረ እና እየረቀቀ መምጣቱን ይናገራሉ። የህፃናት ጋብቻን መከላከል በሁሉም ሴክተሮች ቅንጅታዊ አሰራር የሚሰራ በመሆኑ ፍትህ ቢሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ሰነዶችን በመፈራረም የመከላከል እና የግንዛቤ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የህጻናት ጋብቻ በጤና፣በስነ-ልቦና፣በኢኮኖሚ እንዲሁም በማህበራዊ ግንኙነት የሚያስከትለው ችግር ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የህፃናት ጋብቻን የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበትና በተጨማሪም ወንጀሉ ተፈፅሞ ሲገኝ በህግ ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን መረዳት አስፈላጊ እንደሆነ የፍትህ ቢሮው አሳስቧል።