ሰኔ 9 ፣ 2014

ክሪፕቶከረንሲ ወይም ምናባዊ ገንዘብን በአዋጅ ብቻ መቆጣጠር ይቻላል?

City: Addis Ababaኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ክሪፕቶከረንሲን በህገ ወጥነት ቢፈርጀውም የዲጂታል ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ድርጊቱን ለመከላከል የተሻለና አዋጭ የሚሆነው መፍትሄ የራስ የሆነ ምናባዊ ገንዘብ መፍጠር ነው ይላሉ

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ክሪፕቶከረንሲ ወይም ምናባዊ ገንዘብን በአዋጅ ብቻ መቆጣጠር ይቻላል?
Camera Icon

Credit: Adobe Stock Photos

ክሪፕቶከረንሲ (ወይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “ምናባዊ ገንዘብ” በማለት የሰየመው) የዲጂታል ምንዛሪ ሲሆን ባንክ ወይም መንግስትን የመሰለ ሌላ ማዕከላዊ ተቆጣጣሪ አካል ሳይኖር ብሎክቼይን የተባለ የኮምፒዩተር ኔትዎርክን የሚጠቀም የምንዛሪ አይነት ነው። በክሪፕቶከረንሲ መገበያያ ግለሰቦች በኮይን የሚለካ የገንዘብ መጠን ይኖራቸዋል። ክሪፕቶከረንሲ ተጠቃሚዎች ያላቸው የገንዘብ መጠንና መረጃ ኮምፒዩተራይዝድ በሆነ የዲጂታል አካውንት እንዲቀመጥላቸው ያስችላል። በዚህ የዲጂታል አካውንታቸውም የግብይት ዝርዝራቸው፣ አዲስ ኮይን የሚያጠራቅሙበት መንገድ፣ የኮይን ባለቤትነትና ዝውውራቸው ለየት ባለ የምስጠራ መንገድ (cryptography) የሚጠበቅ ይሆናል። ክሪፕቶከረንሲ ልክ እንደ የወረቀት ገንዘብ የሚታይና የሚዳሰስ ቅርፅ የሌለውና ያልተማከለ የአሰራር ስርአትን የሚከተል የዘመኑ አዲስ የፋይናንስ ፈጠራ ነው። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የሀገሪቱ የገንዘብ መደብ ብር በመሆኑ እና “በየትኛውም የክፍያ መፈፀሚያ ሰነድም ሆነ ስርዓት ያለ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የገንዘብ ዝውውርም ሆነ ገንዘብ ነክ አገልግሎት መስጠት አይቻልም” ሲል አሳስቧል።

የኢኮኖሚክስ ባለሙያ እና አማካሪ የሆኑት አቶ ያሬድ ኃይለመስቀል ከአዲስ ዘይቤ ጋር ባደረጉት ቆይታ የክሪፕቶከረንሲ መነሻ የኑሮ ውድነትን መቅረፍ መሆኑን አስረድተዋል። “መንግስታት በማንኛውም ወቅት ገንዘብ ማተም መቻላቸው በሰዎች እጅ ላይ ያለውን ገንዘብ ዋጋ እንዲያጣ ያደርገዋል። ይህ የመንግስታት ያልተገደበ ገንዘብ የመፍጠር አቅም መንግስታት ለሚፈልጉት ክፍያ ገንዘብ እንዲኖራቸው ቢያደርግም በሰዎች እጅ ላይ ያለውን ገንዘብ ዋጋ ማሳጣቱ ለክሪፕቶከረንሲ መፈጠር ሰበብ ሆኗል” ሲሉ ባለሙያው ይገልፃሉ።

ክሪፕቶከረንሲ ብሎክቼይን የተባለ የአካውንት አይነት የሚጠቀም ሲሆን በንግድ አውታረመረብ ውስጥ ግብይቶችን ለመመዝገብ እና  ባለቤትነትን የመከታተል ሂደትን ያመቻቻል።

በ2009 እ.አ.አ የተጀመረው ቢትኮይን በዓለማችን የመጀመሪያው የክሪፕቶከረንሲ አይነት ሲሆን እንደ ኤክስፕሎዲንግ ቶፒክስ መረጃ ከሆነ ክሪፕቶከረንሲን የሚጠቀሙ ሌሎች የግብይት መንገዶች በአራት ዓመታት ውስጥ ቁጥራቸው ወደ 50 አድጓል። በመቀጠል በአንድ ዓመት ውስጥ በአስር እጥፍ ቁጥራቸው ጨምሮ 500 የክሪፕቶከረንሲ አይነቶች ተግባራዊ ሆነዋል። በ2022 እ.አ.አ ደግሞ በመላው ዓለም ከ18 ሺህ የሚበልጡ የክሪፕቶከረንሲ መገበያያዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑ ተመላክቷል።  

ቢትኮይን የተሰኘው የክሪፕቶከረንሲ መገበያያ መነሻ የሆነችው የአሜሪካ ዶላር ዓለም አቀፍ መገበያያ በመሆኑ የሀገሪቱ መንግስት ዶላር ሲያትም በዶላር ያለገደብ መታተም የሚከሰተው ተፅዕኖ ከአሜሪካ አልፎ ወደተለያዩ የዓለም ሀገራት ይደርሳል። በዚህ ምክንያት ሰዎች እንደፈለጉ የማያትሙት መገበያያ ያስፈልጋል በሚል መነሻ እንደፈጠሩት አቶ ያሬድ ይናገራሉ። ኢተር፣ ሊትኮይን እና ሞኔሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ ከሆኑ የክሪፕቶከረንሲ አውታሮች መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው።

ይህ ያልተማከለ መገበያያ መንገድ በመላው ዓለም ከሚታየው የገንዘብ ዋጋ ማጣት ጋር ተያይዞ በብዙኃኑ ዘንድ እየተለመደ መጥቷል የሚሉት ባለሙያው “በርካታ የፈጠራ ውጤቶች እንደመጡ ተቀባይነት አያገኙም። አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት እነዚህን የክሪፕቶከረንሲ መገበያያዎችን ለማስቀረት ጥረት ቢደረግም የተሳካለት የለም። ይልቁንም መቆጣጠር እንደማይቻል የተረዱ ሀገራት የራሳቸው የሆነ ዲጂታል ገንዘብ ወደማዘጋጀት ገብተዋል” ይላሉ።

በዚህ ረገድ ባለሙያው በምሳሌነት ያነሷት ቻይና የማዕከላዊ ባንክ ዲጂታል ምንዛሪ (Central Bank Digital Currency) የሚባል የክሪፕቶከረንሲ ዓይነት በመፍጠር ላይ መሆኗን ይጠቁማሉ። 

“በዓለም ታሪክ ወርቅ፣ አሞሌ፣ ማርትሬዛን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የመገበያያ መንገዶች ጥቅም ላይ እየዋሉ መጥተው አሁን ባለንበት ጊዜ የአሜሪካ ዶላር ዓለም አቀፍ መገበያያ ሆኗል፤ ምናልባትም ቀጣዩ ዓለም አቀፍ መገበያያ ክሪፕቶከረንሲ የመሆን እድሉ ሰፊ ቢሆንም አሁን ባለበት ሁኔታ ይቀጥላል ወይስ የሚቀየሩ ነገሮች ይኖራሉ? የሚለው በጊዜ ሂደት የሚፈታ ነው” ይላሉ አቶ ያሬድ።

ክሪፕቶከረንሲ ተጠቃሚዎች ትርፍ ሊያገኙ የሚችሉባቸው በርካታ መንገዶች ያሉ ሲሆን አንዳንድ ተቋማት ለአገልግሎታቸው ወይም ንግዳቸው አዳዲስ ደንበኞችን ለመሳብ እንደስጦታ በሚሰጧቸው፣ የክሪፕቶከረንሲ ዋጋ በየጊዜው የሚለያይ በመሆኑ ገዝተው በማስቀመጥ ዋጋው እየተወደደ ሲሄድ በመሸጥ እንዲሁም በተወሰኑ የክሪፕቶከረንሲ ባለቤቶች ዘንድ ደግሞ እንደገንዘብ ወለድ በማግኘት ሊሆን ይችላል። 

“ይህን ቴክኖሎጂ ማስቆም ይቻላል ወይ?” የሚል የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የኢኮኖሚክስ ባለሙያው ማስቆም የማይቻል እንደሆነ ያስረዳሉ። 

ክሪፕቶከረንሲ አንደኛው ጥቅም ሰዎች ለፍተው ያገኙትን ገንዘብ መንግስት በሚያትመው ጥሬ ገንዘብ ሳቢያ የሚፈጠርበትን የዋጋ ግሽበት ማስቀረት መቻሉ ነው። እንደ ጉዳት የሚታየው ደግሞ የባንኮችን ስራ መገዳደሩና የሚነሱበት የደህንነት ስጋቶች ናቸው። 

በኢኮኖሚክስ ዘርፎች ላይ ጥልቀት ያላቸው ትንታኔዎችን በመፃፍ የሚታወቀው ወርልድ ፋይናንሽያል ሪቪው የተሰኘው ድረ ገፅ ባወጣው ፅሁፍ፣ ክሪፕቶከረንሲ ወይም ምናባዊ ገንዘብ የግለሰቦችን የመረጃ ደህንነት መጠበቁ፣ ዘላቂነት ያለውና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑ፣ የዋጋ ግሽበትን ማረጋጋት እንዲሁም ያልተማከለ መሆኑና የገንዘብ ዝውውር ሰንሰለትን ማሳጠሩ የሚጠቀሱ መልካም ጎኖቹ እንደሆኑ ያትታል። 

በአንፃሩ ደግሞ የላላ ቁጥጥር ያለው በመሆኑ ለወንጀል ተግባራት መስፋፋት፣ ተቆጣጣሪ አልባ በመሆኑ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ተጠያቂ አለመኖሩ፣ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ መሆኑና በስህተት ወዳልተፈለገ ሰው የተዘዋወረ ገንዘብ ወደባለቤቱ የመመለስ እድሉ አነስተኛ መሆኑ ደግሞ በምናባዊ መገበያያዎች ላይ እንደ ጉዳት የሚነሱ ሁኔታዎች እንደሆኑ ፅሁፉ ይገልፃል።

በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ዘይቤ አስተያየቱን ያጋሩት የኢኮኖሚክስ አማካሪው አቶ ያሬድ እንደሚገልፁት “ክሪፕቶከረንሲ  ግለሰቦች የሚስጥር ቁጥራቸውን በመጠቀም በእጅ ስልኮች እና ኮምፒዩተሮች ላይ ገንዘብ ተቀማጭ ሊያደርጉ የሚችሉበት የምንዛሪ አይነት ነው። በዚህ ረገድ ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ከደንበኞች በመቀበል፣ ብድር ለሚፈልጉት በማበደር በወለድ መቀበል ከዚያም ደግሞ ተቀማጭ ላደረጉት ሰዎች ወለድ በመክፈል ላይ የተመሰረተ የቢዝነስ ሞዴል ያላቸው በመሆናቸው ባንክ የሚቀመጥ ገንዘብ ከሌለ ለኪሳራ ሊዳረጉ ይችላሉ” ሲሉ ከባንኮች የሚነሳውን ስጋት ያስረዳሉ። በተጨማሪም የመገበያያው መቀመጫ ባንክ አለመሆኑ፣ ዋጋው የሚዋዥቅ በመሆኑ እንዲሁም ቴክኖሎጂው ተለዋዋጭ ስለሚሆን የራሱ ስጋት ይኖረዋል።

በኢትዮጵያ የምናባዊ ገንዘብ አጠቃቀም እየጨመረ ነው ያለው የሀገሪቱ ብሔራዊ ባንክ “ይህ ተግባር ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ውጪ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚደረግበት እና በተለይም በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ለማሸሽ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን መረዳት ተችሏል” ሲል ስጋቱን ገልጿል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የክሪፕቶከረንሲ ግብይት የሚያከናውኑባቸው ከኢትዮጵያ ውጪ የሚሰጡ ጥቂት የማይባሉ መንገዶች አሉ። ለአዲስ ዘይቤ ሀሳቡን ያካፈለና ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ እንደሚያስረዳው በኢትዮጵያ ብር የክሪፕቶከረንሲ ኮይን መግዛት እንዲሁም መሸጥ የሚቻልባቸው የግብይት ድረ ገፆች አሉ። ክሪፕቶከረንሲዎች በዶላር ዋጋ የሚሸጡ ቢሆንም ልክ እንደጥቁር ገበያ ሻጮች ትርፋቸውን አስበው በሚያቀርቡት ዋጋ ይሸጣል። ሻጮች እና ገዢዎች በሚስማሙበት ባንክ አማካይነት ገንዘብ ከተቀባበሉ በኋላ ለገዢው ገንዘቡ ይደርሰዋል፤ ይህን ዶላርም ወደ መረጡት የክሪፕቶከረንሲ ዓይነት በመገበያያ ድረገፆቹ አማካኝነት መቀየር እንደሚችሉ ባለሙያው ያስረዳል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የክሪፕቶከረንሲ ተጠቃሚዎችም የዲጂታል ምንዛሪውን ከሚጠቀሙ ንግድና አገልግሎት አቅራቢዎች ግዢ መፈፀም ይችላሉ።

ኢትዮጵያ የክሪፕቶከረንሲ ተጠቃሚ ብትሆን ለኢኮኖሚዋ  ስለሚኖረው ፋይዳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 2018 እ.አ.አ Assessing the Role of Cryptocurrency Project in Ethiopia: The Case Study of Achiversklub School of Cryptocurrency በሚል ርዕስ በተደረገ አንድ ጥናት የቀረበው መረጃ ኢትዮጵያ የብሎክቼይን ተጠቃሚ እንድትሆን ያለመ ፕሮጀክት ተዘጋጅቶ እንደነበር ይናገራል። በፕሮጀክቱም ከ30 እስከ 100 የሚሆኑ የሶፍትዌር ባለሙያዎችን የማሰልጠን እቅድ መያዙ ተመላክቷል።

ከ100 ለሚበልጡ የቴክኖሎጂ ተቋማት ሰራተኞችና ባለሙያዎች በቀረበው የጥናት መጠይቅ መሰረት “ክሪፕቶከረንሲ በኢትዮጵያ ውስጥ መለመድ አለበት?” ለሚለው ጥያቄ 38 በመቶው መላሾች “ቢሆንም ባይሆንም ችግር የለውም” ሲሉ 35 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ “መለመድ አለበት” ብለዋል። ለዚሁ ጥያቄ 24 በመቶ የሚሆኑት “አያስፈልግም” ሲሉ የተቀሩት 3 በመቶ መልስ አልሰጡም። 

ክሪፕቶከረንሲ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ መሆኑን በተመለከተ ሌላኛው እንደ እንከን የሚታይ ጉዳይ መሆኑን የሚስማሙት አቶ ያሬድ ሀይለመስቀል ለተጠቃሚዎች ግን ዓለም አቀፍ መገበያያ መሆን መቻሉ ገንዘባቸውን በውጭ ምንዛሬ ለማስቀየር ምንም ሳይለፉ በሁሉም ሀገራት ላይ እንዲጠቀሙት ያስችላቸዋል ይላሉ። 

ለምሳሌ ከኢትዮጵያ የሚወጣ አንድ ተጓዥ እጁ ላይ ያለውን ብር ወደ ዶላር ቀይሮ መውጣት የግድ ይለዋል፤ ክሪፕቶከረንሲ ደግሞ ይህን ያስቀራል። ክሪፕቶከረንሲ ለተጠቃሚዎች ነፃነት የሚሰጥ ቢሆንም በሀገራት የታክስ አሰባሰብ እና የግለሰቦችን የሀብት መጠን ማወቅ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።         

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረግ ያለበት ሰዓት ደርሷል የሚሉት የኢኮኖሚክስ ባለሙያው ስለዚህ ይህን የሚቆጣጠረው አካል ከዓለም አቀፍ ሁኔታው ጋር የሚራመድ አሰራር እንደሚያስፈልገው ይናገራሉ። እንደባለሙያው ማብራሪያ “ክሪፕቶከረንሲን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም መገንባት ያስፈልጋል እንጂ በአዋጅ መቆጣጠር የሚቻል ነገር አይደለም። ግለሰቦች ለውጭ ሀገር የሆነ ስራ ሰርተው በክሪፕቶከረንሲ ክፍያ ቢፈፀምላቸው ተቆጣጣሪው አካል ይህን የማወቅ እድል የለውም”።  

ባለሙያዎች የሚያቀርቡት ሌላኛው አማራጭ መፍትሔ ኢትዮጵያ የራሷን ክሪፕቶከረንሲ መፍጠር ነው። በተጨማሪም የወረቀት ገንዘብ ማተም በራሱ ተጨማሪ ወጪ ነው የሚሉት አቶ ያሬድ ከተነሱት ኃሳቦች አንፃር ኢትዮጵያን ጨምሮ ሀገራት ከክሪፕቶከረንሲ አሰራር እንዴት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ጥናቶችን ማድረግ እና ስርዓቱን ማስተዳደር የሚችል አቅም መፍጠር እንጂ ለማስቆም መሞከር ትክክለኛ ውሳኔ አይደለም።

የ ቴክ ቶክ የቴክኖሎጂ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁ ሰለሞን ካሳ በቅርቡ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፁ እንዳሰፈረው የክሪፕቶከረንሲ አሰራር በተፈቀደባቸው አገራትም ቢሆን፣ አሰራር እና ደንብ ይዘጋጅላቸዋል። ለምሳሌ በአሜሪካን አገር United States Financial Crimes Enforcement Network (FinCEN) የሚባል የመንግስት ተቋም አለ። ይህ ተቋም ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የክሪፕቶከረንሲ ግብይትን እንዲከታተል ሃላፊነት እንደሰጠው ገልጿል።

እነዚህ ተቋማት በሃገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴር መመዝገብ የሚኖርባቸው ሲሆን፣ ከ10 ሺህ ዶላር የበለጠ የክሪፕቶ ልውውጥ ሲፈጽሙ ለመንግስት ማሳወቅ፣ እንዲሁም ሃገሪቱ የምትመራበትን Bank Secrecy Act (BSA) የተሰኘ ህግ ሙሉ በሙሉ ማክበር አለባቸው። 

ሰለሞን ካሳ የግል እይታውን ሲያስቀምጥ “ክሪፕቶከረንሲ በሃገር ደረጃ ሊሰጥ የሚችለውን ጥቅም በደንብ አጢኖ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ በመፈለግ ከሌሎችም ሃገራት ልምድ ወስዶ የሚያፈልገውን ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ተግባራዊ በማድረግ የቴክኖሎጂው ተቋዳሽ ለመሆን ማሰብ ይቻላል”።

ኢንቨስቶፒድያ የተሰኘው የኢኮኖሚ መረጃዎች ሰብሳቢ ድረ ገፅ ያቀረበው መረጃ እንደሚያመለክተው 103 ሀገራት የክሪፕቶከረንሲ ልውውጥ እንዲኖር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እና አስተዳደር አላቸው። እስከ ኖቬምበር 2021 እ.አ.አ ድረስ ደግሞ ቻይና፣ ግብፅ፣ ኳታር እና አልጄሪያን ጨምሮ ዘጠኝ ሀገራት ክሪፕቶከረንሲ ወይም ምናባዊ ገንዘብን ሙሉ በሙሉ የሚከለክሉ ሀገራት ነበሩ። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርብ በሰጠውና አነጋጋሪ በሆነው መግለጫው መሰል ምናባዊ መገበያያ መንገዶች በሀገሪቱ ህግ የማይፈቀድ መሆናቸውን ጠቅሶ መሰል ተግባራት ላይ ጥቆማ እንዲሰጠው ተማፅኗል። ሆኖም አለም ላይ ካለው የፋይናንስ ግብይትና እድገት አንፃር የብሔራዊ ባንኩ ውሳኔ ትክክለኛነትና ዘላቂነትን የዘርፉ ባለሙያዎች ጥያቄ ውስጥ ከተውታል። 

አስተያየት