ሰኔ 9 ፣ 2014

አይጠየፍ አዳራሽ፡ የተዋጊ ቡድኖች ተመራጭ ምሽግ

City: Dessieባህል ታሪክ

የአዳራሹ ግቢ ኮረብታማ ቦታ ላይ በመመስረቱ በጦርነት ጊዜ ጠላትን ለማጥቃት አመች እንደሆነ ይነገራል

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

አይጠየፍ አዳራሽ፡ የተዋጊ ቡድኖች ተመራጭ ምሽግ
Camera Icon

Credit: Social Media

በ1907 ዓ.ም የወሎ ገዥ በነበሩት በንጉሥ ሚካኤል ትዕዛዝ እንደተገነባ የሚነገረውና ደሴ ከተማ በንጉሡ ቤተ መንግስት ግቢ ውስጥ የሚገኘው አይጠየፍ አዳራሽ በትግራይ ኀይሎችና በመከላከያ ሰራዊት መካከል በቅርቡ ደሴ ከተማ ላይ በተደረገው ጦርነት ምክንያት ለብልሽትና ጉዳት ተዳርጓል።  

የአዳራሹ ግቢ ኮረብታማ ቦታ ላይ በመመስረቱ በጦርነት ጊዜ ጠላትን ለማጥቃት አመች በመሆኑ ምክንያት የመንግስት ወታደሮች ከተማውን ለቀው እስከወጡበት ጊዜ ድረስ አዳራሹ ግቢ ውስጥ በመሆን ሰራዊቱን የማስተባበር ስራና የተጎዱ የሰራዊቱ አባላቶች ማገገሚያ ቦታ በማድረግ ሲሰራበት ቆይቷል።

የመንግስት ኃይል ደሴ ከተማን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ የትግራይ ሃይሎች ደሴን ሲቆጣጠሩ በተመሳሳይ አዳራሹንና ግቢውን ካምፕ በማድረግ የወታደር ማዘዣ እና መኖሪያ ሆኖ ቆይቷል። 

በጦርነቱ ወቅት ደሴ ከተማ ላይ ከነበሩ የአይን እማኞች መካከል በአራዳ ክፍለከተማ ልዩ ስሙ መንበረጸሃይ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት የ47 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ፋንታሁን መካሻ ስለነበረው ሁኔታ ሲገልጹ "በጊዜው አይጠየፍ ግቢ የመንግስት ሰራዊት  እንደማዘዣነት ሲጠቀምበት ስለነበር ከተቃራኒ አቅጣጫ ሰራዊቱን ለማጥቃት በሚል በሚተኮስ ከባድ መሳሪያ አዳራሹ ይመታል በሚል ከፍተኛ ስጋት ይዞን ነበር" ብለዋል።

በንጉስ ሚካኤል ዘመን አይጠየፍ የሚለውን ስያሜ ከማግኘቱ በፊት የግብር ቤት እየተባለ ይጠራ የነበረው ይኸው አዳራሽ በርከት ያሉ ታሪክን የሚያወሱ ቅርሶች አሉት። አዳራሹ 'አይጠየፍ' የሚለውን ስያሜ ያገኘበት ዋነኛ ምክንያት ዘር፣ ብሔርና ቀለም እንዲሁም መደብ ሳይለይ ንጉሥ ከአሽከሩ፤ እመቤትም ከአገልጋይዋ ጋር በአንድነት ስለሚስተናገዱበት፣ ድሆችና የአካል ጉዳተኞች አድሎ ሳይደረግባቸው ስለሚመገቡበት ነበር። 

2 ሺ 131 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት ላይ የተገነባው አዳራሽ ግርግዳው ሲሚንቶ ፣ የኖራ ዱቄትና ዕንቁላልን በማቀላቀል የተሰራ ነው። አስር ሜትር ቁመትና አንድ ሜትር ውፍረት ባለው ሰባ ምሰሶዎች የተዋቀረ መሆኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡

አይጠየፍ አዳራሽን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የደሴ ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሲሆን አዳራሹ በቅርስነት ተመዝግቦ ጥበቃ እየተደረገለት ለጎብኝዎችና ጥናትና ምርምር ለሚሰሩ ሰዎችን ክፍት ሆኖ ቆይቷል።

ነገር ግን አዳራሹ የተገነባበት ቦታ በጣም ከፍ ያለ እና በዙሪያው ያለውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር እንዲያስችል ሆኖ የታነጸ በመሆኑ በተለያዩ ግዚያት በተነሱ ግጭቶች የተዋጊ ቡድኖች ተመራጭ መጠጊያ እንደሆነ የንጉሥ ሚካኤል ቤተመንግስት አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ መጅድ ይማም ያስታውሳሉ። 

"በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግስትና የኢህአዴግ ሰራዊት ደሴ ላይ ባካሄዱት ጦርነት የቤተመንግስቱ ግቢ ለጦር ካምፕነትና ማዘዣ ሆኖ በማገልገሉ ምክንያት ለከፍተኛ ውድመት ተዳርጎ ለብዙ አመታት አገልግሎት ሳይሰጥ ቆይቷል” ብለዋል አቶ መጅድ።  

እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ በጦርነቱ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩት ቤተመንግስቱና አዳራሹ ቀድሞ የነበራቸውን የኪነ ህንጻ ቅርጽና ውበታቸውን ሳይለቁ በመታደሳቸው ለቱሪስት መዳረሻነት እንዲሁም ለጥናትና ምርምር አገልግሎት እየሰጡ መቆየት ችለው ነበር። 

ሆኖም በዚህ አመት በተካሄደውም ጦርነት አይጠየፍ አዳራሽ ተመሳሳይ እጣፈንታ አጋጥሞታል። በቅርሱ ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን ምን ያህል እንደሆነና ለማስተካከል ምን እንደተከናወነ አቶ መጅድ ይማምን ጠይቀናቸው ነበር።   

“በተለይ የአዳራሹን ውስጠኛ ክፍል የምግብ ማብሰያ ኩሽናና መጸዳጃ በማድረግ ታሪክን የማጥፋትና የማበላሸት ስራ ተሰርቷል" ብለዋል።

ጦርነቱ የተካሄደበት ግዜ አጭር ባይሆን ኖሮ በቅርሱ ላይ ይደርስ የነበረው ውድመትና ጥፋት ከዚህ በላይ ይከፋ ነበር ያሉት የቤተመንግስቱ አስተዳዳሪ አቶ መጅድ ይማም አይጠየፍ አዳራሽንና አጠቃላይ የግቢውን ሁኔታ በማስተካከልና በማጽዳት ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመልሶ ለጎብኝዎች ክፍት መደረጉን ገልጸዋል።

ወ/ሮ ሰላማዊት አሰፋ የደሴ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ስለሁኔታው ሲገልጹ "ጦርነቱ የተካሄደው ከውጭ ጠላት ጋር እንዳለመሆኑ በሃገር ቅርሶች ላይ ከሁለቱም ወገን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸው ነበር። ምክንያቱም ያለመግባባት በንግግር ሊፈታ ይችላል። የወደመን ቅርስ ግን መመለስ አይቻልም። ይህ ሁኔታ የነበረህን ታሪክ ማጥፋት ነውና የሚመለከተው አካል ትውልዱን ማስተማር ይገባዋል" ብለዋል። 

አስተያየት