ደሴ ከተማ ውስጥ ስራ አጥነትን ያቃልላሉ፣ ለበርካቶችም የስራ እድል መፍጠሪያ ይሆናሉ ተብሎ ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶባቸው የተገነቡ ከ80 በላይ አነስተኛ ሼዶች ለተጠቃሚዎች መተላለፍ ቢችሉም አብዛኞቹ ግን ከታለመላቸው አላማ ውጭ እያገለገሉ ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት በብዙዎች ዘንድ የቅሬታ ምንጭ ሆነዋል። አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎችም ይህንኑ ይመሰክራሉ።
አቶ ሰለሞን ጌታቸው የደሴ ከተማ ዳውዶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ሲሆን በዳሶቹ አጠቃቀም ዙሪያ የታዘበውን ችግር "ሼዶቹ ለተጠቃሚ ሲተላለፉ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ አንቀሳቃሾች ተብሎ ነበር። አሁን ላይ ያለው እውነታ ግን አብዛኞቹ ከታለመላቸው ዓላማ ውጭ መኖሪያ ቤት፣ መቃሚያ ቤት፣ መጠጥ ቤት ሆነው ይገኛሉ። ይህ ጉዳይ በከተማችን የወጣት ሱሰኝነት እንዲበራከትና ወንጀል እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።"
በጉዳዩ ዙሪያ ለአዲስ ዘይቤ ሃሳባቸውን ከገለጹት ውሰጥ የ28 ዓመት ወጣት የሆነው አቤል ግርማ አንዱ ነው። "የጣውላ ስራ ባለሙያ እንደመሆኔ የመስሪያ ቦታ /ሼድ/ እንዲሰጠኝ ከጠየቅኩ ሁለት ዓመት ያልፈኛል። ሼዶቹ ለአምስት ዓመት ውል የሚሰጡ ናቸው። ይሁን እንጅ አብዛኞቹ ከሰባት ዓመት በላይ ቢሆናቸውም አስካሁን ድረስ እየተጠቀሙበት ይገኛል። ይህ ደግሞ የሌሎችን እድል የሚዘጋ በመሆኑ መስተካከል ይገባዋል" በማለት ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙት ዳሶች ላይም ቁጥጥር እንደማይደረግ ጠቁሟል።
ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ታልመው የተገነቡት ዳሶች በዘመድ አዝማድ አሰራር ስለተላለፉ ተጠቃሚዎቹ እንደፈለጉ ሊጠቀሙባቸው ችለዋል ያሉት ደግሞ የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ መንገሻ አለምነህ ናቸው። አሰራራቸውንና የደረሱበትን ውጤት የሚገመግም አካል የለም ያሉ ሲሆን አያይዘውም "የሚመለከተው የመንግስት አካል ሼዶቹ ያሉበትን ሁኔታ በመገምገም በትክክል የሚሰሩትን እያበረታታ በሌሎች ተግባር ላይ የተሰማሩትን ከቦታው ላይ በማስለቀቅ በማህበር ተደራጅተው የመስሪያ ቦታው ላጡ ወጣቶች ማስተላለፍ ይኖርበታል" በማለት ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
ወጣቶችን በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት በተፈለገው መጠን የተዘጋጀ የስራ ቦታ ካለመኖሩም በላይ በደሴ ከተማ ላይ አጋጥሞ በነበረው ጦርነት ምክንያት ተጨማሪ ሼድ መገንባት እንዳልተቻለና ከማህበረሰቡ የተነሳው ቅሬታ እውነት መሆኑን ያመኑት የደሴ ከተማ ስራና ስልጠና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሚኒሻው በሪሁን ሲናገሩ፤
"በበጀት ዓመቱ 24 ሼዶችን ለመገንባት እቅድ የነበረ ቢሆንም በወቅታዊ ችግር ምክንያት ማሳካት አልተቻለም። ከዚህ በፊት የተሰሩት ላይ የአምስት ዓመት ውለታ ተወስዶባቸው የተላለፉ ቢሆንም አብዛኞቹ የውለታ ጊዜያቸው ያለፈ ስለሆነና ከታለመለት አላማ ውጭ እየተሰራባቸው የሚገኙ እንዳሉ ግንዛቤው ቢኖርም በተለያየ ምክንያት አስለቅቆ ለአዲስ ኢንተርፕራይዞች ማስተላለፍ አልቻለም" ብለዋል።
የውለታ ሰነዶችን የማጣራት ስራ መጀመራቸውንም ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።
"ከሰማኒያ በላይ ሼዶች በጦርነቱ ጊዜም ቢሆን ጉዳት ያልደረሰባቸውና መሰረተ ልማታቸው የተሟላላቸው ሲሆኑ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአምስት ዓመት ውለታ ጊዜያቸው ስላለፈ መምሪያው ሼዶቹን እንዲለቁ ደብዳቤ ጽፎላቸዋል። ይህን ማድረግ ካልቻሉ በህግ አግባብ እያስለቀቅን ለተተኪዎች የማስተላለፍ ስራ ይሰራል" ብለዋል።
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የንብረት ዝርፊያና ውድመት ተፈጽሞብናል የሚሉና በዳሶቹ እየተገለገሉ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የሚያቀርቡትን አቤቱታ እንዴት መፍታት እንዳሰቡ ለመምሪያው ምክትል ኃላፊ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ " የአብዛኛዎቹ ኢንተርፕራይዞች የውለታ ጊዜ ጦርነት ከመከሰቱ በፊት የተጠናቀቀ ስለሆነ ምክንያታቸው ተቀባይነት አይኖረውም። የንብረት ዝርፊያን በተመለከተ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በትክክል የተዘረፈባቸውን የመለየት ስራ በመስራት ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል ፤ በሌሎቹ ላይ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል" ብለዋል። ጥቂቶችም ቢሆኑ የመምሪያውን ጥያቄ ተቀብለውና ለተተኪ ወጣቶች በማሰብ የመስሪያ ሼዶቹን ላስረከቡ ኢንተርፕራይዞች ምስጋና እናቀርባለን በማለት ሃላፊው ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
በሃገራችን ኢትዮጵያ ለስራ እድል ፈጠራ ይረዳ ዘንድ በመንግስት በኩል ከተያዙት በርካታ ዘዴዎች መካከል ብድርና የቦታ አቅርቦት ማመቻቸት ግንባር ቀደም ናቸው። በዚህም በርካቶች ተጠቃሚ ሆነዋል። ነገር ግን በዚያው ልክ ስራ ላይ ያልዋሉና እየባከኑ የሚገኙ ቦታዎች መኖራቸውም የደሴዎቹ ሼዶች ማሳያዎች ናቸው።