ሰኔ 12 ፣ 2014

ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ፍትህን እንዲጋፈጡ ለኢትዮጵያ ተላልፈው ሊሰጡ ይችላሉ?

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮች

ዚምባብዌ መንግስቱ ኃ/ማርያም ኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጧት ከጠየቀች አስፈላጊውን የህግ አግባብ በመከተል አሳልፋ ልትሰጣቸው እንደምትችል በቅርቡ አመላክታለች፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህ እንዲሆን ይፈቅዱ ይሆን?

Avatar: Abiy Solomon
አብይ ሰለሞን

አብይ የአዲስ ዘይቤ ዋና አዘጋጅ ሲሆን በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ዘርፎች ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ጋዜጠኛ ነው። አብይ በዴይሊ ሞኒተር፣ ሪፖርተር፣ ፎርቹን፣ ቢቢሲ ሚድያ አክሽን በተለያዩ የኤዲቶርያል የስራ መደቦች አገልግሏል።

ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ፍትህን እንዲጋፈጡ ለኢትዮጵያ ተላልፈው ሊሰጡ ይችላሉ?
Camera Icon

Credit: Alamy Stock Photos

ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ መንግስቱ ኃይለማርያም የሚለውን ስም ሲሰማ በአእምሮው ውስጥ ሁለት ተቃራኒ ምስሎች መከሰታቸው አይቀርም። የመጀመሪያው በችግር ውስጥ ሆኖ ጀግንነትን፣ እምቢተኝነትን፣ የሀገር ፍቅርን፣ አንድነትንና ሉዓላዊነትን የሚያሳይ የጠንካራ መሪ ምስል ነው። በሌላ በኩል፣ የእኚህ የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዝደንት ምስል በገዳይነት፣ ጨቋኝነት፣ጨካኝነት እና በጦር ሰባኪነት ቀለም ይሳላል።

የምስሉ አይነት ምንም ይሁን ምን የመንግስቱ ኃ/ማርያም ስም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በትልቁ ተቀርጿል። መንግስቱ ለዘመናት የዘለቀውን እና አይበገሬ የነበረውን ንጉሣዊ አገዛዝ አፍርሰዋል። ከዚያም በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትና ግለሰቦች ላይ በ”ፀረ-አብዮተኝነት” እና በ “ቀይ ሽብር” ስም በማያዳግም እርምጃቸው እስከወዲያኛው አሰናብተዋቸዋል። በቀጣናውም ተወዳዳሪ ያልነበረውን ወታደራዊ ሃይል መገንባት ችለዋል።

ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም መንግስቱ ኃ/ማርያም በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከሀገር መሰደዳቸውና ወደ ዚምባብዌ እንዳቀኑ ተሰማ። በወቅቱ ወደ መዲናዋ እየተቃረቡ የነበሩት የኢህአዴግ ኃይሎች በመጨረሻም ግንቦት 20 ቀን አዲስ አበባን ተቆጣጠሩ።

በ1983 ዓ.ም የኢህአዴግ አማፂያን የስልጣን መንበሩን ሲቆጣጠሩ የኮሎኔል የመንግስቱ ኃይለማሪያም አገዛዝ መጨረሻው ሆነ።

በ 1999 ዓ.ም በዋነኝነት በዘር ማጥፋትና በሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ተከሰው በሌሉበት ሞት የተፈረደባቸው መንግስቱ ከሃገር ከወጡ በኋላ ዚምባብዌ የመሸሸጊያ ቦታ ሆናቸው ቆይታለች። በተላለፈባቸው የፍርድ ውሳኔ የሚጠብቃቸው መንግስቱ ላለፉት ሶስት አስር አመታት ይህን ዕጣ ፈንታ ማምለጥ ችለዋል። 

በ 2017 እ.አ.አ. የመንግስቱ የቅርብ ጓደኛ የነበሩት የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣን መውረድ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ለኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጡ መንገድ ይጠርጋል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር። ይሁን እንጂ ሙጋቤ ከስልጣን ከወረዱበት ቀን አንስቶ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ምንም ሳይፈጠር ቆይቷል። 

ይህ ቢሆንም ቅሉ፣ በአሁን ወቅት ስልጣን ላይ ያለው የዚምባብዌ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ ከቀረበለት መንግስቱ ኃ/ማርያምን አሳልፎ የመስጠት ፍላጎት እንዳሉት ምልክቶች መታየት ጀምረዋል። የዚምባብዌ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ፍሬድሪክ ሻቫ ባለፈው ወር ባደረጉት ንግግር ይህን የመንግስታቸውን አቋም በግልፅ አንፀባርቀዋል። 

ይህም የዚምባብዌ የቀድሞ አቋም ላይ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥ እንዳለ አመላክቷል። በ2009  እ.ኤ.አ. የዚምባብዌ የቀድሞ የማስታወቂያ ሚኒስትር መንግስቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስምምነቶች መሠረት በሀገሪቱ ውስጥ እንደ ስደተኛ የመኖር መብት እንዳላቸው ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

ስደተኛው ፍርደኛ መንግስቱ

የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት በመንግስቱ ኃ/ማሪያም አስተዳደር ወቅት ለፈጸሙት ወንጀሎች ተከሰው የፍርድ ሂደቱ ለ12 ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል። 

ተከሳሾቹ በ209 በዘር ማጥፋት፣ የዘር ማጥፋትን በመቀስቀስና ለዚያም በመዘጋጀት፣ በከፋ የሰው ግድያ፣ በከባድና ሆን ተብሎ በተፈፀመ የአካል ጉዳት፣ ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም እና ከህግ ውጭ የሆነ እስር በመፈፀም ወንጀሎች በጋራ እና በተናጠል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።

ባለስልጣናቱ በልዩ አቃቤ ህግ የተከፈተባቸው ክስ በ2008 እ.አ.አ ሲጠናቀቅም አብዛኞቹ የሞት ፍርድ ተላልፎባቸዋል። በ2011 እ.አ.አ የኢትዮጵያ መንግስት ከ23 በላይ ለሆኑ ከፍተኛ የደርግ ለስልጣናት የተጣለባቸውን የሞት ፍርድ በምህረት ወደ እድሜ ልክ ቢቀይርም ይህ ይቅርታ መንግስቱ ኃ/ማርያምን አላካተተም ነበር።

መንግስቱ በዚምባብዌ በስደት እና ሽሽት መኖር ከጀመሩ ከ30 አመታት በላይ ሆኗቸዋል። መንግስቱን በዙምባብዌ ቆይታቸው ለመጎብኝት እድል ያገኙ ጥቂት ሰዎች ስለ ሁኔታቸው ካቀረቡት መረጃ ባለፈ ስለ መንግስቱ የሃራሬ ህይወት እምብዛም የሚታወቅ ነገር የለም።

ከእነዚህ እድሉን ካገኙ የቅርብ ጎብኚዎች አንዷ ደራሲ እና የቀድሞ ጋዜጠኛዋ ወ/ሮ ገነት አየለ ስትሆን በ1992 ዓ.ም በዚምባብዌ ሃራሬ ከተማ ውስጥ በሚገኘውና ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት የመንግስቱ መኖሪያ ተገኝታ አነጋግራቸዋለች። በጉብኝቷም ወቅት ከመንግስቱ ጋር ያደረገችውን ቃለ-ምልልስ እና በጊዜው የነበራትን ምልከታ በማጠናቀር “የሌተናል ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች” የተሰኘ መጽሃፍ አሳትማለች። 

ወ/ሮ ገነት በመጽሐፏ እንደገለፀችው፣ መንግሥቱ የዚምባብዌ መንግሥት ለአጋር ሀገራት መሪዎች ከሠራቸው ቪላ ቤቶች መካከል በአንዱ ይኖሩ ነበር። የእሳቸው ቤት ከሌሎች በአቅራቢያው ካሉት ትላልቅ እና የመዋኛ ገንዳዎች ካሏቸው መኖሪያ ቪላዎች ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ነው ስትልም ተናግራለች። በመኖሪያቸው በተገኘችበት ወቅት መንግስቱን “ጓድ” ብለው ከሚጠሯቸው ዚምባብዌያውያን ጠባቂዎች በቀር ማንም ኢትዮጵያዊ በአካባቢያቸው እንዳልነበሩም ገነት በመፅሐፏ ታስረዳለች።

“በድንገት በማጉረጥረጥ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጠረጴዛውን በመደለቅ፣ ቀጥለው ደግሞ ወንበራቸው ላይ ለጠጥ በማለት፣ ወይም ወደፊት ጠጋ ብለው አንዳንዴ በሹክሹክታ አንዳንዴ በለሆሳስ ሲናገሩ . . . መላ ሁኔታቸው ላይ ቆፍጣናነት ይታይበታል” ስትል የሚገኙበትን ሁኔታ ታሳያለች።

ደራሲዋ ሁኔታቸውን ስትገልፅ “በስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በቴሌቪዥን እና በፎቶ እንጂ በአካል ባላውቃቸውም መንግስቱ ተለውጠዋል። ሲነገር እንደምሰማው እስከአፍንጫቸው የታጠቁ፣ እንደነብር የሚቁነጠነጡ፣ በዓይናቸው ብቻ አፈር ድቤ የሚያስገቡ አጃቢዎቻቸው ከበዋቸው ባላገኛቸውም፣ በአማረ ዩኒፎርም ተንቆጥቁጠው ስልጣን የሚሰጠውን ግርማና ሞገስ ባይላበሱም፣ መንግስቱ ከተፈጥሮ ያገኙት ወዘና አልተለያቸውም” በማለት በመፅሃፏ የመንግስቱን ሁኔታ ገልፃለች።

የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ወ/ሮ ገነት በዚህ ዘገባ ላይ ያላትን አስተያየት በጠየቃት ወቅት ከቀናት በፊት መንግስቱን ለመጎብኘት ሀራሬ አቅንታ መመለሷን በመናገር መንግስቱ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው የመሰጠታቸው ጉዳይ ላይ ግን አስተያየት ለመሰንዘር ፈቃደኛ አልሆነችም።

ሌላው መንግስቱን በአካል የማግኘት እድል የነበራቸው ግለሰብ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ናቸው። ከአራት አመታት በፊት መንግስቱ ኃ/ማርያምን በሃራሬ ያገኟቸው አቶ ኃይለማርያም በማህበራዊ ድህረ-ገጾች ላይ ባጋሩትና ከጥቂት ቆይታ በኋላ እንዲወርድ በተደረገው ፎቶ አማካኝነት መንግስቱ የሚገኙበትን ሁኔታ ገልፀዋል።

በምስሉ ላይ የነበረው የኃ/ማርያም ደሳለኝ መግለጫም  “የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን አገኘኋቸው። በሀገሬ ያሉ ብዙ የቀድሞ የመንግስት መሪዎች እና ባለስልጣናት በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ የስልጣን ሽግግር ካደረጉ በኋላ ያላቸውን አቅም በተለያየ አቅም ሲያዋጡ ለማየት እመኛለሁ” ይል ነበር።

መንግስቱ ኃ/ማርያም በ1983 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ሸሽተው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ በዚምባብዌ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል። ይህም በ1960ዎቹ የነፃነት ትግል ወቅት ኮሎኔል መንግስቱ የዚምባብዌን ወታደሮች በማሰልጠንና በማስታጠቅ ላደረጉት ውለታ ምላሽ እንደሆነ የሙጋቤ መንግስት በተደጋጋሚ ይናገር ነበር።

መንግስቱ - ነፍሰ ገዳይ ወይስ አርበኛ?

መንግስቱ ኃ/ማርያም በዘር ማጥፋት እና በሌሎች የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀሎች ተከሰው የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸው ይታወቃል። 

የመንግስቱ ኃ/ማርያም የ‘ቀይ ሽብር’ ዘመቻ ሲታወስ አሁንም አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ህመም የሚሰማቸው አያሌ ኢትዮጵያውያን አሉ። በዚህ ዘመቻ በተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና በሌሎች ዜጎች ላይ በተወሰደው ደም አፋሳሽ እርምጃ እስከ 750,000 የሚደርሱ ወገኖች ህይወታቸውን እንዳጡ የሚነገር ሲሆን  አብዛኞቹ ሰለባዎቹም ምሁራን ነበሩ።

መንግስቱን ነፍሰ በላ አድርገው የሚገልጿቸው አካላት በርካታ የቀድሞ ‘ጓዶች’ን እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ለቀጠፈውና የደርግ መንግሥት ለፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ግድያ መንግስቱን ቀዳሚ ተጠያቂ ያደርጓቸዋል።

የደርግ የፖሊት ቢሮ አባል፣ የኢህዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመንግስቱ የቅርብ ሰው የነበሩት አቶ ፋሲካ ሲደልል በቅርቡ ከጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ መንግስቱ ግድያን በተመለከተ ስለነበራቸው አቋም ጠቆም አድርገው አልፈዋል።

አቶ ፋሲካ ‘የሻምላው ትውልድ’ የተሰኘ መጽሃፋቸው መውጣቱን ተከትሎ ባደረጉት በዚህ ቃለ መጠይቅ ላይ ሲናገሩ “ፕሬዝዳንቱን ብዙ አስተያየት ሰጪዎች አያውቋቸውም … ፕሬዝዳንቱ በጣም ችኩል፣ ሰው ለመግደል ጨርሶ የማያመነቱ ሰው ናቸው። ትዕግስት የሌላቸው ሰው ናቸው። በማንኛውም ባየነው ነገር በኩዴታው ሰዎችም ሆነ በሌሎች በተወሰደው እርምጃ እንደምናየው ለቅፅበት ማሰብ፣ ለቅፅበት እድል መስጠት አይሞክሩም። ወዲያው እርምጃ የሚወስዱ ሰው ናቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

አቶ ፋሲካ ከ40 ዓመታት በኋላ ዛሬ ላይ ሆነው የመንግስቱን ባህሪ ሲያስታውሱ “በዚህ ረገድ የመፈንቅለ መንግስቱን ሞካሪዎቹን ባለመግደላችን ወቅሰውናል። ‘እኔ እንድገድል ለምን አቆያችሁልኝ’ ይሉ ነበር። ለፍርድ የቀረቡት የመፈንቅለ መንግስቱ ሞካሪ ጄነራሎች በሕይወት በመቆየታቸውም ይበሳጩ ነበር” በማለት ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ መንግስቱ ኃ/ማርያም በአገዛዛቸው  ለተፈፀሙት ግድያዎች እንደ ግለሰብ ተጠያቂ እንደማይሆኑ በመግለፅ የሚቀርብባቸውን ክስ አጥብቀው ያስተባብላሉ።

መንግስቱ ኃ/ማርያም በ1999 እ.አ.አ ከደቡብ አፍሪካው ዕለታዊ ጋዜጣ ‘ዘ ስታር’ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በግላቸው ማንንም እንዳልገደሉ ነገር ግን በጊዜው በተደረጉና የብዙ ሰው ህይወት ባለፈባቸው ጦርነቶች ትእዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል። የቀይ ሽብር ዘመቻ በሁለት የተለያዩ ማህበራዊ ቡድኖች መካከል የተደረገ ውጊያ ነው” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ጋዜጣው በቃለ ምልልሱ ዘገባ ላይ መንግስቱን ሲገልፃቸው "ንግግራቸው በተቃውሞ የተሞላ፣ በንዴት የጦፉ መራራ ሰው" በማለት ፅፏል። 

በቃለ ምልልሱ መንግስቱ ሲናገሩ ኢትዮጵያን ከፊውዳሊዝም ያወጣ መሪ መሆናቸው ተጠቃሽ ሌጋሲያቸው እንደሆነ አፅዕኖት ሰጥተዋል። በተጨማሪም "እኔ መናገር የምችለው ነገር ቢኖር ለ17 ዓመታት ያለ ዕረፍት የሚፈጠሩትን ተደራራቢ ችግሮች ለመፍታት በመጣር፣ ከአንድ ከጦርነት በኋላ ሌላ ጦርነት በማስተናገድ ያሳለፍኳቸው እያንዳንዳቸው ቀናትና ሰዓታት አስቸጋሪ መሆናቸውን ብቻ ነው” ማለታቸውም ተጠቅሷል።

በጨካኝነት የሚስሏቸው እንዳሉ ሁሉ መንግስቱን አሁንም ጀግና፣ ቆራጥ፣ ወደር የሌለው የሀገር ፍቅርና የማይናወጥ አቋም ያለው ሀቀኛ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ብለው የሚያወድሷቸው ደጋፊና አድናቂዎችም አሏቸው። እነዚህ ደጋፊዎቻቸው ለመንግስቱ ካላቸው ፍቅር የተነሳ ፈፅመዋል ተብለው የሚከሰሱበትን ግፍና በደል ሁሉ ሀገራቸውን ለማስከበር፣ ሉዓላዊነቷና አንድነቷን ለማስጠበቅ እንዲሁም ከጠላቶቿ ለመከላከል የወሰዷቸው አማራጭ የሌላቸው እርምጃዎች ናቸው በማለት ከደሙ ንፁህ ያደርጓቸዋል።

ዚምባብዌ ከአሁን በኋላ አስተማማኝ ቤታቸው ልትሆን ትችላለች?

የዚምባብዌ መከላከያ ሰራዊት ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን ህዳር 15 ቀን 2010 ዓ.ም ከስልጣን አወረዳቸው። ፕሬዝዳንት ኢመርሰን ምናንጋግዋ ስልጣኑን ተረክበው ስራቸውን ሲጀምሩ በሙጋቤ ዙሪያ ያሉ ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ቃል ገብተው ነበር።

ይህን በተመለከተ በ1994 እ.አ.አ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸሙትን ወንጀለኞች ዚምባብዌ ማስጠለሏን እንድታቆም እና አሳልፋ እንድትሰጥ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚደረገው ጥሪ ያየለበት ጊዜ ሲሆን ይህም ጥሪ የመንግስቱ ኃይለማርያምን ስም ሳይጠቅስ አላለፈም።

በ1999 እ.አ.አ መንግስቱ ኃ/ማርያም ለህክምና ከሄዱበት ከደቡብ አፍሪካ ተላልፈው እንዲሰጧት ኢትዮጵያ ጥያቄ እንዳቀረበች ተዘግቦ ነበር። በወቅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎች ድርጅቶች ግፊቱን አጠናክረው በመቀጠል መንግስቱ ለፈፀሙት የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀሎች ለፍርድ እንዲቀርቡና ለተከሰሱበት የዘር ማጥፋት ወንጀል መልስ እንዲሰጡ ይወተውቱ ነበር። ሆኖም ኢትዮጵያ ያቀረበችው ጥያቄ በደቡብ አፍሪካ መልስ ከማግኘቱ በፊት መንግስቱ ወደ ዚምባብዌ ተመልሰዋል።

በጊዜው መንግስቱ ኃይለማርያምን በማስጠለላቸው ምክንያት ለሚደርስባቸው አለም አቀፍ ጫና መልስ ለመስጠትና ጥያቄውንም ለማለዘብ ፕሬዝዳንት ሙጋቤ ያደረጉት አንድ ነገር የአሜሪካ እና የካናዳ መንግስታት ዙምባብዌ ለመንግስቱ ኃ/ማርያም ከለላና ጥበቃ እንድትሰጥ ድጋፍ ማድረግ እንችላለን ማለታቸውን ይፋ ማድረግ ነበር።

በ1999 እ.አ.አ ‘ኒው ሂውማኒታሪያን’ ባወጣው ዘገባ በተጠቀሰው የሮበርት ሙጋቤ ንግግር “አሜሪካንና ካናዳ መንግስቱ ኃይለማርያምን ለመንከባከብ የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን ካልቻልን በገንዘብ ማገዝ እንደሚችሉ ያላቸውን ፍላጎት አሳውቀውናል” በማለት ተናግረዋል። ይህን መረጃ በሃራሬ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም ያረጋገጠው ሲሆን ኤምባሲው በሰጠው ማብራሪያ በወቅቱ ለመንግስቱ ኃ/ማርያም መሸሸጊያ ቦታ ማመቻቸት በኢትዮጵያ ተጨማሪ ደም መፋሰስ እንዳይኖር ያደርጋል የሚል እምነት የአሜሪካ መንግስት እንደነበረው ገልጿል።

ባለፈው ወር የዚምባብዌ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ፍሬድሪክ ሻቫ ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “የኢትዮጵያ ህዝብ መንግስቱ ኃ/ማርያምን በተመለከተ ለዚምባብዌ መንግስት ጥያቄ ካቀረበ የዚምባብዌ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግሥት ለሚቀርብለት ሕጋዊ ጥያቄ ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል” ብለዋል።

የመንግስቱ ኃይለማርያምን ተላልፎ የመሰጠት ኃሳብ ከተቃወሙት መካከል ኡጋንዳዊው ጠበቃ፣ የምርመራ ጋዜጠኛ እና የግጭት አፈታት ባለሙያ ዴቪድ ኒኮራች ይገኝበታል። ዴቪድ ካፒታል ኤፍ ኤም ድረ ገፅ ላይ ባሰፈረው ፅሁፍ በሰጠው አስተያየት “አንዳንዶቻችን የመንግስቱ ኃ/ማርያምን ተላልፎ መሰጠት ከበፊት ጀምሮ የምንቃወመው በፍትህ ስለማናምን ሳይሆን ሊያመጣ የሚችላቸውን አስከፊ መዘዞች እና ኢትዮጵያውያንን ሊያስከፍል የሚችለውን ዋጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው” ብሏል።

ዴቪድ ኒኮራች ፅሁፉን ሲደመድም ዚምባብዌ መንግስቱን አሳልፋ ለመስጠት ወይም ላለመስጠት ስትወስን ሰለሞናዊውን ጥበብ ተግባራዊ በማድረግና ውሳኔው የሚያስከትለውን መዘዝ ሁሉ በመመርመር መሆን አለበት በማለት አክሏል። አያይዞም “ዚምባብዌ ውሳኔዋ በማስተዋል ላይ ካልተመሰረተ ትልቁን አዳ የሚከፍሉት የዚምባብዌ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ይሆናሉ” ሲል ስጋቱን አጋርቷል።

የመንግስት ፍላጎት እና አሳልፎ የመስጠት ህጋዊ ሂደት

የመንግስቱ ኃ/ማርያም ተላልፎ መሰጠት እውን የሚሆነው ኢትዮጵያ ፍላጎት ካሳየችና ተላልፈው እንዲሰጧት ከጠየቀች ብቻ ነው። በተጨማሪም ዚምባብዌ ይህን ጥያቄ ለመቀበል ካላት ፍቃደኝነት ጀርባ ያለው ፍላጎቷ ትክክለኛ መሆኑም ሌላው መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በስልጣናቸው መባቻ በተለይ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰፊ እውቅናና ተቀባይነት ካተረፉባቸው ነገሮች አንዱ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታታቸው እና በስደት ላይ ላሉ ፖለቲከኞችና ፍርደኞች ምህረት ማድረጋቸው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በ2010 ዓ.ም ባደረጉት ንግግር በስልጣን ላይ ያሉ የኢትዮጵያ መንግስታት ከነሱ ቀድመው የነበሩ መሪዎችን የመበቀል ታሪክን አንስተው “ዋጋ ቢስ ነው!” ማለታቸው የሚታወስ ነው። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው ሲናገሩ አፄ ኃይለሥላሴ በልጅ እያሱን፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም በኃይለሥላሴ ላይ ያደረጉትን የበቀል እርምጃ ጠቅሰው ለኢትዮጵያውያን ምንም ለውጥ እንዳላመጣና ይህንን አዙሪት ለማስቆም ውሳኔ ላይ መድረስ አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ያንፀባረቁት አመለካከታቸው እንዳለ ሆኖ በመንግስቱ ኃ/ማርያም ላይ ያላቸውን አቋም እንዲህ ነው ብሎ በግልፅ መናገር አዳጋች ነው። መንግስቱን አሳልፎ እንዲሰጥ የመጠየቅ፣ ምህረት የመስጠት እና ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ የማየት እድል በደፈናው በአስቸጋሪ ሁኔታዎች የተሞላ ይመስላል።

ጠ/ሚ አብይ አህመድ ነሐሴ 19 ቀን 2010 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አዋጆች በህገ መንግስቱ የሚገዙ ህጎች መሆናቸውን በመናገር፣ በ“ምህረት አሰጣጥ እና አፈጻጸም ሥነ-ሥርዓት” አዋጅ ለ‘ቀይ ሽብር’ ወንጀለኞች ይቅርታ መስጠትን እንደሚከለክል በማስታወስ መንግስቱ ኃይለማርያምም በአዋጁ ምህረት አግኝተው ወደ ሀገር መግባት እንደማይችሉ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በህገመንግስቱ ምህረትን በተመለከተ የተቀመጠው አንቀፅ ከተሻሻለና የቀይ ሽብርና መሰል ወንጀሎች በምህረት ይቅር እንዲባሉ ከተፈቀደ ኮሎኔል መንግስቱ የዚህ ይቅርታ አካል እንዲሆኑ የሚያስችላቸው እድል እንዳለ ጠቁመዋል።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የምህረት አሰጣጥና አተገባበር አዋጅ ቁጥር 1089/2009 “የተፈፃሚነት ወሰን” በሚለው አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ “ይህ አዋጅ በማናቸውም የወንጀል ክስ በተከሰሱ ተጠርጣሪዎች፣ ተከሳሾች ወይም ሰዎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል” ይላል። ነገር ግን በሚቀጥለው አንቀፅ “በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተደነገገው ቢኖርም ይህ አዋጅ የዘር ማጥፋት፣ የሞት ቅጣት፣ በግዳጅ መሰወር ወይም ማሰቃየትን በሚመለከቱ የተደረጉ ወንጀሎች ላይ ተፈጻሚ አይሆንም” ሲል ገደብ የሚደረግባቸውን የወንጀል አይነቶች ጠቅሷል።

የምህረት አሰጣጡ ተጨባጭ ሁኔታ ይህ ሆኖ ሳለ “ያልተገመተው ቢፈጠርና መንግስቱ ኃ/ማርያም ለኢትዮጵያ ተላልፈው ቢሰጡ ምን ሊፈጠር ይችላል?” የሚል ጥያቄ ያቀረብልነት የህግ ባለሙያ እና ተንታኝ አቶ አብዱራዛቅ ናስር “ፍርዱን ተከትሎ በህግ የሚፈጸመው የመጀመሪያው ነገር እስራት ነው። ሆኖም፣ ይህ ማለት የሞት ቅጣቱ ተፈፃሚ ይሆናል ማለት አይደለም” በማለት መንግስቱ ወደ ሃገር ቢመጡ በቅድሚያ ሊገጥማቸው የሚችለውን የህግ እርምጃ ይገልፃል። 

“ማንኛውም በሌለበት የቅጣት ውሳኔ የተላለፈበት ግለሰብ በአካል በቁጥጥር ስር በሚውልበት ጊዜ በሌለበት የተላለፈበትን የፍርድ ውሳኔ የመከላከል ህጋዊ መብት አለው” ሲል አቶ አብዱራዛቅ ያስረዳል። 

እንደ የህግ ባለሙያው ማብራሪያ፣ መንግስቱ ኃ/ማርያም የተላለፈባቸውን ውሳኔ በሚያቀርቡት ክርክርም ሆነ ማስረጃ ማስቀየርና መከላከል ካልቻሉና ፍርዳቸው በሃገሪቱ ርዕሰ ብሔር ወደ እድሜ ልክ እስራት ካልተቀየረላቸው በስተቀር ሊጠብቃቸው የሚችለው ቀድሞ የተወሰነባቸው የሞት ፍርድ ይሆናል። 

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 28 ላይ እንደ ዘር ማጥፋት ያሉ ወንጀሎች በሕገ ደንቡ እንደማይታገዱና ወንጀሎቹ በሕግ አውጭው ወይም በማንኛውም የመንግሥት አካል ምህረት ወይም ይቅርታ ሊሻሻሉ እንደማይችሉ ተደንግጓል። በዚሁ አንቀፅ በተመሳሳይ ወንጀሎች የተከሰሱ እና የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው ሰዎችን በተመለከተ የሃገሪቱ ርዕሰ ብሔር ቅጣቱን ወደ እድሜ ልክ እስራት ሊለውጥ እንደሚችል ተገልጿል።

በዘመናቸው ከነበሩት አቻዎቻቸው የአፍሪካ አምባገነኖች መካከል እስካሁን በህይወት መቆየት የቻሉት የ85 አመቱ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም አሁን ባሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ስለ ወደፊት እጣ ፈንታቸው በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። በኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ቀደምት መሪዎችና ባለስልጣናት ፍትህ እናሰፍናለን በሚሉ ተተኪዎቻቸው የበቀል ሰለባ ሆነዋል። መንግስቱ እስካሁን ከዚህ የበቀል አዙሪት ሸሽተው መቆየት ቢችሉም ይህን ታሪካዊ እጣ ፈንታ ያመልጡ ይሆን? መስጠት የሚቻለው ብቸኛ መልስ ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ እንደሆነ ነው።

አስተያየት