ሰኔ 14 ፣ 2014

በምስራቅ አፍሪካ የቻይና ልዑክ ኢትዮጵያውያንን የማሸማገል ጥያቄ አቀረቡ

City: Addis Ababaፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተገኙበት የሰላም ጉባኤ ላይ ቻይና የሀገራቱን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መንገድ ግጭቶች እንዲፈቱ የበኩሏን ድርሻ መወጣት እንደምትፈልግ ገልጻለች

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

በምስራቅ አፍሪካ የቻይና ልዑክ ኢትዮጵያውያንን የማሸማገል ጥያቄ አቀረቡ
Camera Icon

Credit: Social Media

ትላንት ሰኔ 13 2014 ዓ.ም በቻይና መሪነት አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የሠላም ጉባኤ ላይ የተገኙት የቻይና የምሥራቅ አፍሪካ ልዑክ ዥዪ ቢንግ የቀጣናውን ግጭቶች ለማሸማገል ጥያቄ አቀረቡ።

ቻይና በምሥራቅ አፍሪካ አገራት የሚታዩ ግጭቶችን ላሸማግል የሚለውን ጥያቄ ባቀረበችበት የሰላም ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን ጨምሮ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የዑጋንዳ፣ የኬንያ፣ እና የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተገኝተው ነበር። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ላይ ተሳታፊ የነበረችው ጎረቤት ሀገር ኤርትራ ተወካዩዋን ሳትልክ መቅረቷ ተዘግቧል። ሆኖም ሀገሪቷ ተወካይዋን ያልላከችበትን ምክንያት እስካሁን ይፋ እንዳላደረገች ታውቋል።

የቻይና የምሥራቅ አፍሪካ ልዑክ በምሥራቅ አፍሪካ ግጭቶች እንዲፈቱ የማሸማገል ጥረቶችን ለማድረግ ዝግጁነታቸውን በገለጹበት መድረክ እንዳብራሩት በዚህ ረገድ የሚያደርጉት ማንኛውም እንቅስቃሴ የሀገራቱን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መንገድ እንደሚሆን አስረድተዋል። 

ላለፉት 19 ወራት የፌዴራል መንግሥት እና የህወኃት ሃይል በኢትዮጵያ ውስጥ ሲያካሄዱ የቆየቱን ጦርነት በሠላም ለመቋጨት ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ወራት አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ሲልኩ መቆየታቸው ይታወቃል።

የሠላም ጥረቱን በተመለከተ በቅርቡ ኢትዮጵያ የነበሩት የአፍሪካ ኅብረት የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑኩ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ፤ ሂደቱ አዝጋሚ ቢሆንም ከስድስት ወራት በፊት ከነበረው የተሻለ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል። በአሁን ሰአት በቻይና በኩል የመጣው የአሸማጋይነት ፍላጎትም የቀረበው ሁለቱም ወገኖች ለመደራደር ያላቸውን ሃሳብ ባሳወቁበት ወቅት ነው።

የፌደራል መንግሥት እና ሕወሓት ባለፉት ቀናት በታንዛንያ አሩሻ እያንዳንዳቸው አምስት ተወካዮችን ልከው ሊደራደሩ ነው የሚሉ መረጃዎች ቢወጡም፤ ሕወሓት ባወጣው መግለጫ የታንዛንያን ጥረት በማድነቅ “ዝግጁ የሆንኩት በኬንያ ለሚደረግ ድርድር ነው” ብሎ ነበር። ከዚህ ጋር አያይዞም የአሸማጋይነት ሚና እንዲወስዱ የምፈልገው የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ናቸው ማለቱ ይታወሳል። 

ህወሃት በመግለጫው ለማደራደር ሙከራ ሲያደርጉ የቆዩት በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ፣ ለዶክተር ዐቢይ አሕመድ ቀረቤታ እንዳላቸው በመግለጽ፤ ተአማኒነታቸው ላይ ጥያቄ እንዳለው ገልጾ ነበር።

የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ እስካሁን ድረስ በየትኛውም አገር ከሕወሓት ጋር ምንም አይነት ድርድር እንዳላደረገ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አማካይነት አሳውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ከዚህ በኋላ ከማንም ጋር ጦርነት እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ ገልጸዋል። 

መንግስት የቻይናን የማሸማገል ጥያቄ ይቀበል እንደሆነ ለማወቅ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎትን ለማናገር ከአዲስ ዘይቤ ሙከራ ቢደረግም ይህ ጽሑፍ እስከታተመበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አልተገኘም።

አስተያየት