በምስራቅ ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ ዳዋ እና ሸበሌ በተባሉ ቦታዎች እየተባባሰ በመጣው አስከፊ ድርቅ ለረሃብ የተጋለጡ ዝንጀሮዎች ሰዎች ላይ ጥቃት መሰንዘር መጀመራቸውን ኒውስዊክ ዘገበ።
በአካባቢው በሰብአዊ ስራዎች ላይ የተሰማራውን አለም አቀፍ ድርጅት ሴቭ ዘ ቺልድረንን ጠቅሶ ኒውስዊክ እንዳስነበበው በአካባቢው የዱር ዝንጀሮዎች ነዋሪዎችን ማጥቃት ሰለመጀመራቸው ከሶስት ወር በፊት ሪፖርቶች ድርጅቱ እየደረሱት እንደሆነ ገልጿል።
በአሁኑ ጊዜ በሃገሪቱ የሚታየው ድርቅ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አስከፊ እንደሆነ በመጥቀስ የሴቭ ዘ ቺልድረን የምስራቅ ኢትዮጵያ የኦፕሬሽን ማናጀር አቶ አብድራዛቅ አህመድ እንደተናገሩት የዱር ዝንጀሮዎቹ ለየት ባለ ሁኔታ ቁጡና አመፀኛ እየሆኑ መምጣታቸውንና ነዋሪዎችም የተራቡትን ዝንጀሮዎች በየጊዜው ለመከላከልና ለማባረር መገደዳቸውን ተናግረዋል።
በኦክስፋም መረጃ መሰረት በአለም ላይ በከባቢ አየር ለውጦች የተነሳ የኤሊኖ የአየር ንብረት የዝናብ ወቅቶችን መዘበራረቅና መዛባት በመፍጠሩ የውሃ ምንጮች እንዲደርቁ አድርጓል። ከዚህ የተነሳም በተለይ በሞቃት ሃገሮች ውሃ በፍጥነት እንዲተንና ደረቅ የአየር ንብረት እንዲሁም ድርቅ እንዲፈጠር አድርጓል። በኢትዮጵያም በ 50 አመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ ሊከሰት ችሏል።
ይህም በየአካባቢው የሚገኙ ህብረተሰቦች ላይ ጫና ከመፍጠሩም በላይ የዱር አራዊት አካባቢያቸውን ጥለው ህዝብ ወደሚኖርባቸው ቦታዎች እንዲገቡ አድርጓቸዋል።
የሴቭ ዘ ቺልድረኑ አቶ አብድራዛቅ እንደሚለው ዝንጀሮዎች በመሰረታዊነት ሰው የማያጠቁ ቢሆንም ያለው ሁኔታ አስከፊ በመሆኑ ተፈጥሯዊ ያልሆነና አስፈሪ ባህሪ እንዲያሳዩ አድርጓቸዋል። ድርቁ እንደ ከርከሮ ያሉ የዱር እንሰሳትን የሰዎች መኖሪያን ጥሰው እንዲገቡ እንዳስገደዳቸውና እንዲሄዱ ሲደረጉም እንቢተኝነትን እንደሚያሳዩ አቶ አብድራዛቅ አስረድቷል።
“እንሰሳቱ ሰዎችን በሚያበሳጭ ሁኔታ አመፀኛ ባህሪ በማሳየት ውሃ ወይም ምግብ ፍለጋ ወደ መኖሪያ ቤቶች ይዘልቃሉ፤ ህይወታቸውንም ለማትረፍ ያለ ምንም ፍርሃት ወደ መንደሮች ይገባሉ” ይላል አቶ አብድራዛቅ።
በዘገባው እንደተነገረው በዚህ ሁኔታ ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ወድቀዋል። ቁጥቋጦዎች ውስጥ የተደበቁ ዝንጀሮዎች በዚያ በሚያልፉና ማንኛውንም ነገር የያዙ ሴቶችንና ህፃናትን ውሃ እንደያዙ በማሰብ ጥቃት ይሰነዝሩባቸዋል።
በሶማሌ ክልል የሚገኙ የተለያዩ መንደሮች ከቤት እንሰሳት በተጨማሪ የተለያዩ የዱር እንሰሳት በተለይ ደግሞ ዝንጀሮዎች መታየታቸውን እንዲሁም አያሌ የዱር እንሰሳትም በሞት እየረገፉ እንደሆነ ሪፖርት እየደረሰው እንደሆነ ሴቭ ዘ ቺልድረን አስታውቋል።
በጉዳዩ ላይ ኒውስዊክ ያነጋገረው አቶ አብድራዛቅ እንደሚለው ሁኔታው እጅግ አደገኛ እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል። “ወላጆች ልጆቻቸውን ከቤት ለማስወጣት ፈርተዋል፤ ምክንያቱም በየቦታው የሚታዩት ዝንጀሮዎች ህፃናትን በማጥቃት ላይ ይገኛሉ” ሲል አቶ አብድራዛቅ የሁኔታውን አስከፊነት ገልጿል።
እንደ አቶ አብዱራዛቅ ማብራሪያ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ መጋባት ውስጥ ያሉ ሲሆን ህብረተሰቡን ስለ ሁኔታው አደገኛነት ለማስገንዘብና ህፃናትን በተቻለ መንገድ ከአደጋ ለመጠበቅ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
“እውነት ለመናገር ምን ማድረግ እንዳለብን አላውቅም። እንሰሳት አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ በውሃና ምግብ እጦት በረሃብ በመሞት ላይ ይገኛሉ። ሰዎች ህይወታቸውን ለማቆየት ከፍተኛ ትግል ውስጥ ባሉበት በዚህ ሰአት ስለ እንሰሳቱ ምን ማሰብ ይቻላል? እናም በግልፅ ልናገር የምችለው እነዚህን እንሰሳት ከአካባቢው ለማራቅ ምን ማድረግ እንደምንችል አናውቅም” በማለት አቶ አብድራዛቅ ስጋቱን አካፍሏል።
በጉዳዩ ላይ ለኒውስዊክ አስተያየታቸውን የሰጡት የእንሰሳት ባህሪ ባለሙያዋ ዶ/ር ታትያና ሃምል እንዳስረዱት እጅግ በከፋ የምግብ እጥረትና ድርቅ ወቅት የዱር እንሰሳት ለከፍተኛ ጭንቀት የሚጋለጡ ሲሆን ይህም ያለማመንታት ምግብ ፍለጋ ወደ ሰዎች መኖሪያ እንዲገቡና አመፀኛ እንዲሆኑ ያስገድዳቸዋል።
“እንሰሳቱ የሚያሳዩት አመፀኝነትና ጥቃት የመሰንዘር ዝንባሌ ሰዎች በምላሹ በሚያሳዩአቸው ባህሪ ሊባባስ ይችላል። ሰዎች እንሰሳቱን ላይ አደን ሊፈፅሙና ኃይል በመጠቀም ሊያሳድዷቸው የሚያደርጉት ጥረት እየጨመረ ከመጣ እንሰሳቱም በአንፃሩ ደፍረትና አመፅ ተላብሰው ጥቃት መሰንዘራቸው እያየለ ይመጣል” በማለት ባለሙያዋ እሳስበዋል።