ጎንደር በአማራ ክልል ደማቅ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ ለአለፉት ሁለት ዓመታት በሀገራችን የባጀውን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ የቱሪዝም አንቅስቃሴው መዳከሙ ይነገራል። ለመሆኑ የጎንደር ከተማ አሁናዊ የቱሪዝም አንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
በጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የቅርስ ጥናትና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ አይቸው አዲስ በአለፉት ጥቂት ዓመታት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው ጦርነት በጎንደር ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ የራሱን አሉታዊ አሻራ አስቀምጦ አልፏል ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል በሀገራችን የተደረገውን ጦርነት ተከትሎ በምዕራባዊያን ሚዲያ የተካሄደው ዘመቻ የራሱን አሉታዊ ሚና ሳያሳድር አልቀረም ሲሉ የቡድን መሪው የግል አስተያየታቸውን ሰተዋል፡፡ ጦርነቱን ተከትሎ የመጡ ችግሮች ማለትም ሰው የማገት ወንጀል፣ አላስፈላጊ የመሳሪያ ተኩስ እና ሌሎች ችግሮች ተዕፅኖ ነበራቸው። ይህም በቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ ኪሰራ አሳድሮ እንደነበር አይካድም ብለዋል አቶ አይቸው ለመቀዛቀዙ ምክንያት ሲያቀርቡ፡፡
በከተማው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ተዳክሞ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በርካታ ችግሮች አስተናግደዋል ያሉት ቡድን መሪው በዚህም አምስት ሆቴሎች ስራ ለማቆም ተገደው አንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በከተማ አስተዳደሩ የተደራጁ የቱሪዝም ፖሊሶች የከተማው ቱሪዝም አንቅስቃሴ ክፉኛ በመዳከሙ ለመበተን መገደዳቸውን አውስተዋል፡፡ የቱሪዝም ፖሊሶቹ ስራቸው በዋናነት የጎብኝዎችን ደህንነት እና ተሽከርካሪ እንዲሁም መሰል ቁሳቁሶች መጠበቅ ነወ።
በከተማው ከቱሪዝም ጋር በተገናኘ በማህበር የተደራጁ 71 አስጎብኝዎች፣ 34 "አጓጓዦች" ወይም የላዳ ታክሲ ሾፌሮች፣ 18 "የእናት ጓዳ" ባህላዊ ምግብ ለጎብኚዎች አቅራቢዎች እና ሌሎችም ማህበራት የከተማው የቱሪዝም መፋዘዝ ስራቸውን እንዳቀዛቀዘው ተነግሯል፡፡ በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የማህበራቱ አባላት ህይወታቸውን የሚመሩበት ጊዜያዊ መፍትሄ ለመፈለልግ በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም እንዳልተሳካ ቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡
በዘርፉ ከተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መጎዳት በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ ከዘርፉ በዓመት ያገኝ የነበረውን በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ አሳጥቷታል ፤ ይህም በሴክተሩ ሌሎች የቱሪዝም ስራዎች ላይ ችግር ማሳደሩ አይቀርም ብለዋል አቶ አይቸው የችግሩን ተሻጋሪነት ሲያብራሩ፡፡ ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ ሌሎች የቅርስ ጥበቃና ጥገና ስራዎች መስራት ያስችል እንደነበር በመጠቆም።
ከ71 በላይ አባላት ያሉት የጎንደር ከተማ ቱሪስት አስጎብኚዎች ማህበር ሰብሳቢ ፈንታሁን ያለው የጎንደር ከተማ ቱሪዝም በአለፉት ሁለት ዓመታት በጣም መቀዛቀዙን ይገልፃል፡፡ በዚህም የተነሳ አንዳንድ የማህበሩ አባላት በችግር ምክንያት ትዳራቸውን እስከመፍታት የደረሰ ማህበራዊ ችግር እንደደረሰባቸው ገልጾ ችግሩ በመክፋቱ የተነሳ የስራ ዘርፍ የቀየሩ መኖራቸውን አስረድቷል፡፡
ተዳክሞ የነበረው የቱሪዝም አንቅስቃሴ የጥምቀት በዓልን ተከትሎ ለጥቂት ግዜ በትንሹም ቢሆን መነቃቃት አሳይቶ የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ በከተማዋ የተከሰተው ግጭት፣ በተደጋጋሚ የሚሰማው አላስፈላጊ ተኩስ፣ እየተለመደ የመጣው ሰው የማገት ወንጀል ቱሪዝሙን አንደገና አዳክሞታል ተብሏል፡፡
በከተማዋ በተለምዶ የቴዎድሮስ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በፍጥነት ፎቶ አንስቶ በማተም ለጎብኚዎች አገልግሎት የሚሰጠው ወጣት ታሪክ አትንኩት በቅርቡ ተከስቶ የነበረው ግጭት በስራቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሮ አንደነበር ይናገራል፡፡ አብረውት ይሰሩ የነበሩ ባልደረቦቹ ቱሪዝሙ ተቀዛቅዞ በመሰንበቱ ስራ ለመቀየር መገደዳቸውን እንዲሁም ሰው የማገት ወንጀል መበራከቱ የንግድና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ መታዘቡን ተናግሯል፡፡
በጎንደር ከተማ ብዙም በአደባባይ የማይወራው ሰው የማገት ወንጀል ብዙዎችን ዋጋ እንዳስከፈለ የከተማው ኗሪዎች ይናገሯሉ፡፡ ለከተማ አስተዳደሩ በሰላማዊ ሰልፍ ሳይቀር አቤት ማለታቸውን ተከትሎ የፀጥታ መዋቅሩ ቁልፍ አጀንዳ አድርጎታል፡፡ በተደጋጋሚ እየተከሰተ የሚገኘውን የአጋች ታጋች ድራማ ነጻ ከወጡ ታጋቾች አንደበት ተረድተናል፡፡
ወጣት ገዙ ሞገስ (ለደህንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ) ሃምሌ 22/2013 ዓ.ም. ታመው ሆስፒታል የተኙ እናቱን ለማየት ከአንድ ሌላ የሆስፒታሉ ተማሪ ጋር ወደ ቅጥር ግቢው በባጃጅ እየገባ በነበረበት ወቅት ነበር የተያዘው።
“በግምት ከምሽቱ 2 ስዓት አካባቢ ነበር። ከእኛ በተቃራኒ ሌላ ባጃጅ ሁለት ሰዎችን አሳፍሮ ከሆስፒታሉ ወደ ከተማ በመጓዝ ላይ ነበር፡፡ ጨለማን ተገን አድርገው የቆሙ ስድስት ታጣቂዎች ሁለቱንም ባጃጆች አስቆሟቸው። በሁኔታው ብንደናገጥም ሰዎቹ የቀድሞውን የመከላከያ ደንብ ልብስ ስለለበሱ ለፍተሻ ይሆናል ብለን ገምተን ያለ ምንም ማቅማማት ቆምን” ያለው ገዙ ታጣቂዎቹ ፊታቸውን በጨርቅ ሸፍነው እንደነበረና በአቅራቢያው ወደሚገኘው ተራራ እንዲሄዱ እንዳዘዟቸው ያስታውሳል። ገዙ እንደሚለው ለፍተሻ ይሆናል ብሎ የገመተው አንደኛው የባጃጅ ሾፌር “እኛ እኮ ህጋዊ ነን” ብሎ መታወቂያ ካርዱን ቢያሳያቸውም አንደኛው ታጣቂ ጀርባውን በሰደፍ እንደመታውና ከዛ በኋላ መታገታቸውን እንዳወቁ ይናገራል።
“እኛን መሃል አድርገው እነሱ ፊትና ኋላ እየመሩን ወንዙን ተከትለን በጨለማው ውስጥ ባለ ቀጭን መንገድ ጉዟችንን ቀጠልን። ድንገት አንደኛው የባጃጅ ሾፌር ጨለማውን ተገን አድርጎ ወደ ወንዙ ዘሎ በመግባት አመለጠ፤ ተከታትለው ቢተኩሱበትም ማግኝት ስላልቻሉ እኛን ይዘው ጉዟችን ቀጠልን” ይላል።
በግምት ሶስት ስዓት ያህል እንደተጓዙ እና የተዘጋ የአርሷደር ቤት ሲያገኙ ቁልፉን ሰብረው እንዳስግቧቸው የሚናገረው ገዙ እስከዚያ ድረስ አጋቾቹ ምን እንደሚፈልጉ እንዳልነገሯቸው ያስታውሳል። “ቤቱ ውስጥ ከገባን በኋላ ገንዘብ እንደሚፈልጉና በማግስቱ ወደ ቤተሰብ ደውለን ይህን ማሳወቅ እንዳለብን ነግረውን በኪሳችን የያዝነውን ስልክና ቦርሳ ሁሉንም ነገር ወሰዱ” ብሏል ወቅቱ አስፈሪ አንደነበር እያስታወሰ፡፡
በማግስቱ እያንዳንዳቸው ቤተሰቦቻቸውን አንድ አንድ ሚሊዮን ብር እንዲያመጡ እንዲጠይቁ እንዳዘዟቸው፣ ከብዙ ልመና በኋላ በመቶ ሽህ ብር መስማማታቸውን የገለጸው ወጣቱ “ገንዘቡን ይዞ የሚመጣው ሰው ለፀጥታ አካላት ቢያሳውቅ እንደሚገሉን ስለነገሩን ቤተሰቦቻችንን አስጠነቀቅናቸው ነበር። ግማሾቹ አጋቾች እኛን ሲጠብቁ ሌሎቹ ብሩን ለመቀበል ወደ ቀጠሮው ቦታ ሄዱ” ብሏል።
አስጨናቂውን ሂደት ሲያብራራ ቤተሰቦቻቸው ፖሊስ ይዘው ወደ ተቀጠሩበት ቦታ ይሄዱና እነሱም እናልቃለን የሚል ስጋት አድሮባቸው እንደነበር ያስታውሳል፡፡
እነገዙ የታገቱት አምስት ሆነው ሲሆን ቤተሰቦቻቸው ሊከፍሉላቸው የቻሉት ለአራቱ ብቻ ነበር። አምስተኛውን ታጋች አንለቀውም በማለት ወስነው የነበሩት አጋቾች በብዙ ልመና እሱንም ከተከፈለላቸው ታጋቾች ጋር አብረው ፈተውታል።
“በታገትን በሶስተኛው ቀን ተለቀቅን፤ ነገር ግን ሲያመጡን በጣም ጨለማ ስለነበር እንዴት መመለስ እንዳለብን አናውቅም ነበር፡፡ አጋቾቹ ቢለቁንም በፍርሃት ቆፈን ታፍነን ነበር። ትንሽ እንደተጓዝን መከላከያ ሰራዊት አባላት አግኝተውን ወደ ከተማ አደረሱን፡፡ በወቅቱ ቤተሰቦቻችን ገንዘብ መሰብሰብ ስለነበረባቸው አብዛኛው የከተማው ኗሪ ሁኔታችንን አውቆት ነበር” ይላል ገዙ።
ይህ ብዙዎችን ለብዙ እንግልት እና ኪሳራ የዳረገው የእገታ ወንጀል ጎንደር ከተማ ውስጥ በተደጋጋሚ ተከስቷል፡፡ በዚህም በግለሰብ ደረጃ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ በተጨማሪ በከተማዋ ገፅታ ላይ የራሱን አሉታዊ ሚና እየተጫወተ ስለሚገኝ የሚመለከተው አካል ችግሩን ለመቅረፍ መስራት አለበት ይላል ወጣት ገዙ አሁን አሁን መሻሻል እንደሚታይ በመግለጽ፡፡
አቶ አይቸው አዲስ እንደገለጹት በ2014 በጀት ዓመት በአለፉት ዘጠኝ ወራት 52,800 የሀገር ወስጥ ቱሪስት ለማስተናገድ ታቅዶ 79 በመቶ (41,429) ብቻ ማሰተናገድ ተችሏል፡፡ ከተስተናገዱት የሀገር ወስጥ ጎብኝዎች 507,429 ብር ገቢ የተገኘ ሲሆን የባለፉት ዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ6 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ለዚህም እድገት በዚህ ዓመት ጥምቀትን በጎንደር ለማክብር የነበረው አንቅስቃሴ በምክንያትነት ተጠቅሷል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ15,000 በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ለማስተናገድ ዕቅድ ቢያዝም ማሳካት የተቻለው 1 በመቶውን ወይም (310) ብቻ ነው። ይህም ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ18 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ተነግሯል፡፡ ከውጭ ሀገር ቱሪስቶች የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3.7 ሚሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ 8 በመቶውን (326,116 ብር) ብቻ ማግኘት መቻሉን አቶ አይቸው ነግረውናል፡፡
ከባለፈው አመት ጀምሮ በጎንደር ከተማ በተደጋጋሚ ሲከሰት የቆየው ሰው የማገትና ገንዘብ የመጠየቅ ወንጀል በከተማው ሕዝብና የጸጥታ መዋቅር ርብርብ መቀነስ በመቻሉ በአሁኑ ወቅት የከተማዋ ቱሪዝም በትንሹም ቢሆን መነቃቃት ማሳየቱ ተነግሯል። በከተማው ይስተዋል የነበረው አላስፈላጊ ተኩስም እየቀነሰ መምጣቱ ታውቋል።
በተለይ የጥምቀት በዓልን ተከትሎ በመጣው የከተማዋ የቱሪዝም መነቃቃት ተዘግተው የነበሩ ሆቴሎች አንደገና ስራ እንዲጀምሩ አስችሏቸዋል። ነገር ግን በቅርቡ በከተማው ተከስቶ የነበረው ግጭት በመነቃቃት ላይ የነበረውን ቱሪዝም መልሶ አቀዝቅዞታል ይላሉ ነዋሪዎቹ የከተማውን አሁናዊ የቱሪዝም አንቅስቃሴ ሲገልፁ፡፡
በሌላ በኩል የከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በትንሹም ቢሆን በሀገር ውስጥ ጎብኝዎች አማካኝነት መሻሻል እያሳየ መምጣቱን የአስጎብኝዎች ማህበር ሰብሳቢ ፈንታሁን ያለው ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን ይላል የማህበሩ ሰብሳሰቢ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላትም ሆነ ለመንግስት ገቢ በማስገኘት ወሳኝ ሚና ያለው የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ሁኔታ አሁንም በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።
"እኛ የማህበሩ አባላት የረጅም ዓመት ልምድ ያለን እና ለዓመታት ያገለገልን ቢሆንም አሁን የከተማው የቱሪዝም ዘርፍ በመጎዳቱ እኛም ለከፋ ችግር ተዳርገናል" ብሏል ፈንታሁን።
የማህበሩ አባላት ለክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም ለክልሉ መንግስት ችግራቸውን በተደጋጋሚ በመግለጽ ጊዜያዊ መፍትሄ አንዲፈለግላቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር። ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ "ፕሮፖዛል" አዘጋጅተው እንዲያመጡ በተጠየቁት መሰረት አቅርበውና ድጋፍ ሰጭ ድርጅት ከተገኘ ጉዳያቸው እንደሚታይ ተነግሯቸው ምላሽ እየጠበቁ ይገኛሉ።
በርካታ ቱሪስት የምታስተናግደው የጎንደር ከተማ ከዚህ ቀደም "በትራንስፎርመር" ችግር ምክንያት የምሽት ጎብኝዎችን አታስተናግድም ነበር አቶ አይቸው እንደነገሩን። ነገር ግን ከፌደራል መንግስት በተደረገ የአራት ትራንስፎርመሮች ድጋፍ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ የምሽት ጉብኝት የሚጀመር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአለፈው አመት በጎንደር ከተማ ለብዙዎች ስጋት የነበረው የእገታ ወንጀልም ባለፉት ወራት መሻሻል ማሳየቱን የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ከጎንደር ከተማ ኗሪዎች ጋር በነበረው ቆይታ መገንዘብ ችሏል፡፡
የ69 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው የጎንደር ከተማ ኗሪ አቶ አለማየሁ ግርማ በከተማዋ በምሽት በርካታ ተኩስ ይሰማ እንደነበር ገልጸው አሁን አሁን ይህ እየቀረ በመሆኑ ደስተኛ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ “በከተማዋ በተደጋጋሚ ይታይ የነበረው ሰው የማገት ወንጀል ህግ የማስከበር እክል ያመጣው ችግር ነው፡፡ አሁን ግን የፀጥታ መዋቅሩ ባደረገው ጥረት መሻሻሎች መስተዋል ጀምረዋል” ብለዋል ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በቅርቡ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢ.ዜ.አ) በሰጡት መግለጫ በከተማው ሰው በማገት ወንጀል የተጠረጠሩ 36 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና በምርመራ ላይ እንደሚገኙ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል የጎንደር ከተማን ሰላም ለመመለስ በተደረገ ጥረት 4,649 ያልተመዘገቡ የጦር መሳሪያዎች ይዘው የነበሩ ግለሰቦች በመንግስት ጥሪ መሰረት መመዝገባቸውን የከተማ አስተዳደሩ በቅርብ በሰጠው መግለጫ አሳውቋል፡፡ ይህም በከተማዋ በምሽት የሚደረግን ህገወጥ ተኩስ እና እንቅስቃሴ በማረም ረገድ በኗሪዎቹ ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡