ከዓመታት በፊት የእጅ መንሻ ሆኖ እንዳገለገለ በእድሜ የገፉ ሰዎች ይናገራሉ። ከባልንጀራው ጋር በድንገት የተጋጨ ሰው የሰፈሩን ሽማግሌዎች ሰብስቦ ካሳ ይከፍላል። ተጎጂው ጉዳቱን እንዲረሳ በሽማግሌዎች ከሚወሰንለት የመካሻ ስጦታዎች መካከል “ሲጦ” ይገኝበታል።
“ከሠላሳ ዓመታት በፊት ብዛት ያለው የ“ሲጦ” ተክል በሀዋሳ ከተማ ይገኝ ነበር። አሁን ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሚገኝበት ሕንጻ እስከ አዲሱን መናኸሪያ አልፎ ሲጦ ሞኖፖል ድረስ በአረንጓዴው የሲጦ ተክል የተወረረ የችግኞች መገኛ ነበር። ትልቅ ቦታ ስለሚሰጠው እንክብካቤ ይደረግለታል” ያሉን አቶ አብነት ናቸው። ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ በሀዋሳ ከተማ እንደኖሩ የሚናገሩተት አቶ አብነት ጎመን መሳይ አረንጓዴ መልክ ያለው የ“ሲጦ” ቅጠል ማራኪ ዕይታ እንዳለው ይናገራሉ። ከማሳ ሲሰበሰብም ሆነ ሲቀነጠስ የራሱ ስነ-ስርአት ያለው ስለመሆኑም አብራርተዋል። “የቤቱ አባወራ በእንክብካቤ ካደገው ተክል ቅጠሎችን በጥንቃቄ ይቀነስጥና ለምለሙን ቅጠል መርፌን ተጠቅሞ በጅማት ይይዛል። በአንድ ላይ የተሰፋው ቅጠል በጸሐይ እንዲደርቅ ይደረጋል። የደረቀው የ“ሲጦ” ቅጠል ይወቀጥና ይሸጣል ወይም ይቀመጣል” ብለዋል።
“ሲጦ” በሀዋሳ እና አካባቢዋ የሚዘወተር ሱስ አስያዥ ቅጠል ነው። በሲዳምኛ የተለያየ አጠራር ቢኖረውም በአብዛኛው ግን “Tanibo” (ተንቦ) እና Senku (ሰንቁ) ተበሎ ይጠራል። የሲጦ ቅጠልን በዝርያ ከሚመሳሰሉ ቅጠሎች መካከል “ጋያ”፣ “ጌሾ”፣ “ሱረት” ይገኙበታል። በሌሎች አካባቢዎች “ትምባሆ” በሚል መጠሪያው ይታወቃል። በሲዳማዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ለዚህ ማሳያ የሲዳማ አባወራዎች ቤታቸውን ለመጎብኘት ለሚመጣ የክብር እንግዳ ሲጦን የሚጠቀም እንደሆነ በመጠየቅ ፈላጊ ከሆነ ልክ እንደ ቡና ቁርስ ይቀርብለታል። "ሲጦን" እንደመደለያ ይጠቀሙበት እንደነበረም ይነገራል። ለአብነት ያክል አንድ ሰው ከአንዱ ባለንጀራው ጋር የተጣላ እንደሆነ እና ተጎጂ ከሆነ ሲጦን በኮባ ቅጠል ብቻ በመሸፋፈን ካሳ እንዲከፈለው ይደረጋል። እንደአጠቃላይ አክባሪውም ማክበሩን፤ ተከባሪውም መከበሩን የሚያውቁበት ባህላዊ መግባቢያ ሆኖ ለረዥም ዘመናት አገልግሏል።
በቀደመው ዘመን በህላዊ ይዘት ያለው “ሲጦ” አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ በወጣቶች ዘንድ ተዘውታሪ እየሆነ መጥቷል። ጫትን እና ሲጋራን እንደመሰሉ ማኅበራዊ እጾች የቤተሰብ እና የአካባቢ ራስ ምታት ወደ መሆን እየተቃረበ ነው። የሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በዙሪያዋ የሚገኙት አጎራባች ከተሞች ማለትም አርቤጎና፣ ሀገረ ሰላም፣ ወንዶ ገነት እና በመሳሰሉት ወረዳዎች ተዘውታሪ በመሆን ላይ ይገኛል።
ወጣት አስቻለው “ሲጦ”ን መጠቀም ከጀመረ አምስት ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይናገራል። አጠቃቀሙ ወደ ሱስ ደረጃ እንደደረሰም አልሸሸገም። ስለ አጠቃቀሙ እና ጥቅሙ ሲያስረዳ “ሲጦ የተፈጨ ዱቄት ነው። አወሳሰዱም በአፍንጫ ነው። በአፍንጫ ወደ ውስጥ ይሳባል። ሲወሰድ እስከ ራስ ቅል ድረስ የሚሰማ የሚመስል ስሜት አለው። እንደ ማስነጠስም ሊያደርግ ይችላል። ያነቃቃል። የብርታት ስሜት ይፈጥራል። የምወስደው ይንን መነቃቃት ፈልጌ ነው። በቀን ውስጥ እስከ አምስት ጊዜ ልጠቀመው እችላለሁ” ሲል አብራርቷል።
የሲጦ ተጠቃሚዎች ዋነኛ አገልግሎቱ ድብርትን ማስወገድ ቢሆንም በጉንፋን መድኃኒትነት የሚወስዱት መኖራቸውንም ነግረውናል። ጉንፋንን ለመዋጋት ጀምረውት ሱስ የሆነባቸው ስለመኖራቸውም ሰምተናል።
የሲጦ ሱሰኛ ስለመሆኑ ነግሮን ስሙን እንድንደብቅለት የነገረን ወጣት በበኩሉ ሲጦን ሳይጠቀም ቀኑን ማሳለፍ እንደማይችል ይናገራል። “ሲጦን ካልወሰድኩ ከሰው መግባባት አልችልም። ድብርት ይለቅብኛል፣ እነጫነጫለሁ፣ ከሰው ጋር እጣላለሁ በአጠቃላይ ሥራዬን መስራት አልችልም” ብሏል።
“ሲጦ” በከተማዋ በሚገኙ የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች በቀላል ዋጋ መገኘቱ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር እንዲጨምር አስገድዷል። ከሀዋሳ ከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ከሳንቲም ደረጃ ጀምሮ ሲሸጥ ሀዋሳ ውስጥ ከሁለት ብር እስከ አምስት ብር ድረስ ይሸጣል።
ከማነቃቃት በተጨማሪ ድፍረት እንደሚሰጥ የሚነገርለት ሲጦ የሚያዘወትሩት ወጣቶች ዝርፊያን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎችን እንዲፈጽሙ ስለማደፋፈሩ ከአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉ ተጠቃሚዎቹ ያስረዳሉ።
የሀዋሳ ከተማ መናኸሪያ ክ/ከተማ ነዋሪ የሆነው ተክለፃድቅ ገዛኸኝ “ጓደኞቼ ጉንፋን እየደጋገመ ሲያስቸግረኝ ሲጦ እንድወስድበት መከሩኝ። ስለማላውቀው ፈርቼው ነበር። በእነርሱ ማበረታቻ ለመውሰድ ተስማማሁ። የጌሾ መልክ ያለው የተወቀጠ ቅጠል ነው። በአውራ ጣቴ እና በአመልካች ጣቴ ትንሽ ዱቄት ቆንጥሬ በአፍንጫዬ ወደ ላይ ሳብኩት። አጅግ ያቃጥላል። በተመሳሳይ ደቂቃ ያስነጥሳል። እነርሱ እንዳሉት ከጉንፋኑ በተወሰነ ደረጃ ቢያሽለኝም ከሱሱ ግን እራሴን ማላቀቅ አልቻልኩም። አሁንም ተዘፍቄበታለሁ” ሲል ቁጭቱን ገልጾአል።
ቀስ በቀስ የተጠቃሚዎች ቁጥር የበዛለት ማኅበራዊ አደንዛዥ እጽ ስጋት ወደ መሆን ደረጃ በማደግ ላይ ነው። ሲጦን ጨምሮ ሌሎቹም የሚጨሱ እና የሚሸተቱ የትንባሆ ዝርያዎች በጤና ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት እና በውስጣቸው የያዙት ንጥረ ነገር ምን እንደሆነ መረጃ እንዲሰጡን የዋቻሞ ዮኒቨርሲቲ የፋርማሲ ት/ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ዶ/ር ብሩክ ክብረአብን ጠይቀናቸው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
“ሲጦ የተባለው ባህላዊ የሱስ አስያዥ ቅጠል ከአደንዛዥ ዕፆች ውስጥ የሚመደብ ነው። አብዛኛውን የአዕምሮ ክፍል ሲያጠቃ ያጠቃል። በስፋት እንደሚታወቀው ማሪዋና እና ኮኬን የመሳሰሉ አደንዛዥ ዕፆች የሚያጠቃው የአዕምሮ ክፍል እንደሆነ ሁሉ ሲጦም በተመሳሳይ ያጠቃል። ለምሳሌ የማዞር ስሜት፣ የድብርት ያስከትላል። በራስ መተማመንንም ያሳጣል”
እንደ ዶ/ር ብሩክ ገለፃ ከኒኮቲን ዝርያዎች ውስጥ የሚመደበው ቅጠሉ ጉንፋንን ለመከላከል ተብሎ መወሰዱ ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ።
በህይወት ያሉ ተገዢዎቹን ለበርካታ የጤና እና የማኅበራዊ ችግሮች የሚዳርገው “ሲጦ” በሕይወት የሌለ አስከሬንም በቅጡ እንዳይቀበር የጎንዮሹ ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ አዲስ ዘይቤ ከዓይን እማኞች ሰምታለች። በማንኛውም ምክንያት ህይወቱ ያለፈ የሲጦ ሱሰኛ እግሩ ወደላይ ታዝሮ ተዘቅዝቆ ይሰቀላል። ከአስከሬኑ የሚወጣው ሽታ ያለው ፈሳሽ ሰዎች ከአካባቢው እንዲርቁ እስከማስገደድ ሊደርስም ይችላል። በሕይወት የተጠቀሙት ሲጦ በፈሳሽ መልክ ከአስከሬኑ እንደሚወጣ እና ግብአተ መሬቱም የሚፈፀመው ሙሉ ፈሳሹ ከአፍንጫው ውስጥ ወጥቶ ሲያልቅ እንደሆነም ከተጠቃሚዎች ሰምተናል።