ኅዳር 7 ፣ 2014

በጦርነቱ ለተጎዱ በ 'አይዞን' መተግበሪያ ከ100ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ

City: Addis Ababaቴክማህበራዊ ጉዳዮች

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ከቻፓ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር 'አይዞን' በተሰኘ መተግበሪያ  ከ100 ሺህ በላይ ዶላር መሰብሰቡን አስታወቀ።

Avatar: Henok Terecha
ሄኖክ ተሬቻ

Henok is a reporter at Addis Zeybe. He is passionate about storytelling and content creation.

በጦርነቱ ለተጎዱ በ 'አይዞን' መተግበሪያ ከ100ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ከቻፓ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር ባለማውና ለሀገራዊ ጉዳዮች ሀብት ለማሰባሰብ በበለጸገው 'አይዞን' በተሰኘ መተግበሪያ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ከ100 ሺህ በላይ ዶላር መሰብሰቡን አስታወቀ።

ይህ መተግበሪያ ባለፈው ለህዳሴ ግድብ ሀብት ማሰባሰቢያ ከተሰሩት መተግበሪያዎች የሚለየው ማንኛውም ሀገራዊ ጉዳዮች ሲከሰቱ በዘላቂነት ገቢ የሚሰበሰብበት በመሆኑ ነው ሲሉ አቶ ነብዩ ሰለሞን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዲፕሎማት ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል። 

“መተግበሪያው ዳያስፖራው ካለበት ሆኖ የእጅ ስልኩን በመጠቀም በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጁ ፕሮጀክቶችን አንዲደግፍ የሚያስችለው ሲሆን፣ ወደ ስራ በገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ500 በላይ ከሆኑ የዳያስፖራ አባላት ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ማሰባሰብ ችሏል” ሲሉ ገልጸዋል። 

መተግበሪያው ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት የሚመለከታቸው መንግስታዊ አካላት ፈቃድ እንዲያገኝ የተደረገ ሲሆን፣ ድረገጹ በኢትዮጵያ መረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በኩል እውቅና ተሰጥቶታል፤  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም አለም አቀፍ የክፍያ ማስተላለፊያ መስመሩን አመቻችቷል።

መተግበሪያው በአንድ ጊዜ በርካታ አገራዊ ፕሮጀክቶችን በማቅረብ ከዳያስፖራው በአንድ ቋት ሀብት ለማሰባሰብ እንዲያስችል ሆኖ የተዘጋጀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በመተግበሪያው ሀብት እየተሰባሰበ ያለው ለሀገራዊ ጉዳይ በግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ድጋፍና በቀጣይም ሌሎች የጤና ፣ የትምህርት እና ሌሎች ፕሮጀክቶችንም የሚያካትት እንደሚሆን ተገልጾአል።

ይህ መተግበሪያ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ዳያሰፖራ ኤጀንሲ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን አሁን የሚሰበሰበው ገንዘብ ለብሔራዊ አደጋና ስጋት አመራር ኮሚሽን በኩል በጦረነቱ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች ድጋፍ እንዲውል ይደረጋል ሲሉ ነግረውናል።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ሚልየኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅልው ለከፋ እንግልትና ረሀብ የተዳረጉ ሲሆን፤ በግለሰቦችና ተቋማት በኩል ተጎጂዎችን ለመደገፍ ያለሙ በርካታ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ይስተዋላል። ይሁን እንጂ የድጋፍ አሰባሰቡ ቅንጅት የጎደለው ነው የሚሉ ትችቶችም ይሰነዘሩበታል።

ከዳያስፖራው የሚሰበሰቡ ድጋፎችን ወጥነት ባለው መልኩ ለመሰብሰብ ያግዛል የተባለው ይህ መተግበሪያ  በቀጣይ እንደየክስተቶቹ የሚመለከታቸው አካላት ገንዘብ ለመለገስ ይህንኑ መተግበሪያ የሚጠቀሙ ይሆናልም ተብሏል። 

ይሄው በገንዘብ ሚኒስቴር፣ ብሄራዊ ባንክና ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዕውቅና የተሰጠው https://eyezonethiopia.com/page/about-eyezon የገንዘብ ማሰባሰቢያ ድረ-ገጽ፤ በቀላልና አስተማማኝ መንገድ ከፈቃደኛ ለጋሾች ገንዘብ ማሰባሰብ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

ቻፓ የተሰኘው የቴክኖሎጂ ድርጅት ከዚህ ቀደም ሁለት መተግበሪያዎችን ሰርቶ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን እነዚህ መተግበሪያዎች ለታላቁ ህዳሴ ግደብ የገቢ ማሰባሰቢያነት የሚውሉ 'ኢት ኢዝ ማይዳም' እና 'ማይገርድ' በመባል የሚጠሩ መተግበሪያዎችን አበልጸጎ ስራ ላይ እንዲውሉ አድርጓል።

አስተያየት