ግንቦት 17 ፣ 2013

5 የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ቅሬታ አቀረቡ

ምርጫ 2013ዜናዎች

5 የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የማስታወቂያ ሥራ እና የፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ መርሃግብር አለመካተታቸው አግባብነት የሌለው እንደሆነ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

5 የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ቅሬታ አቀረቡ

ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የማስታወቂያ ሥራ እና የፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ መርሃግብር ላይ ያልተካተቱ አምስት የሕትመት መገናኛ ብዙኃን በምርጫ ቦርድ እና በመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቅሬታ አቀረቡ። አዲስ ምንጭ፣ ሀበሻ ወግ፣ መርፌ እና ግዮን መጽሔት እንዲሁም ኢትዮ ሀበሻ ጋዜጣ መርሃግብሮቹ ላይ አለመካተታቸው አግባብነት የሌለው እንደሆነ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። 

''የእኛ አስተዋጽኦ ለምን ተረሳ?'' የሚሉት የመርፌ መጽሔት ባለቤት እና አዘጋጅ ዮናታን ዮሴፍ (ዶ/ር) መጽሔቶች እንደማንኛውም የመገናኛ ብዙኃን በምርጫው ሂደት ተሳታፊ መሆን ነበረባቸው ይላሉ።  

በምርጫ ቦርድ እንዲሁም በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በሂደቱ አካል አለመሆናቸው ቅር እንዳሰኛቸው የገለጹት የሕትመት ሚዲያዎቹ ጥያቄያቸውን በጋራ በመሆን ለሁለቱ ተቋማት ለማቅረብ ማቀዳቸውን ዶ/ር ዮናታን ይናገራሉ።

ጥያቄያቸው ምላሽ ካገኘ ከዚህ በኋላ በቀሩት ቀናት በቅስቀሳው ለመሳተፍ እንደሚፈልጉ የመጽሔቱ ባለቤት ጨምረው ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል። 

የአዲስ ምንጭ መጽሔት አዘጋጅ አቶ ውብሸት ታየ ''ምርጫ ቦርድ ለመራጮች የሚሰራው ማስታወቂያ በመጽሔታችን ላይ እንዲታተም እኛ ጥያቄ ማቅረብ አልነበረብንም፡፡ ራሱ ምርጫ ቦርድ ሊያሰራን ይገባ ነበር'' ይላሉ፡፡ ድርጅታቸው ሁኔታውን በዝምታ ሳያልፈው ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ቢጽፍም ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ከቦርዱ ምላሽ አለማግኘታቸውንም ነግረውናል፡፡

በተጨማሪም አቶ ውብሸት በግል የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ላይ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን እንዲያካሂዱ ቢደረግ ሁለት ጥቅም አለው ይላሉ፡፡ ‹‹የአንባቢ ቁጥር እንዲጨምር እና የሕትመት ሚድያው (ጋዜጣ ወይም መጽሔት) ከማስታወቂያው ድጎማ እንዲያገኙ ያደርጋል›› ያሉ ሲሆን ምርጫ ቀጣይነት ያለው መርሀ-ግብር እንደመሆኑ ለወደፊት ሁኔታዎቹ እንዲስተካከሉ ከሌሎች አዘጋጆች ጋር በጋራ በመሆን እየመከሩ መሆናቸውን ይናገራሉ። 

የኢትዮ ሃበሻ ጋዜጣ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የጊዮን መጽሔት ዋና አዘጋጅ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ማህተመወርቅ በበኩላቸው ምርጫ ቦርድ ለመገናኛ ብዙኃን በመደበው በጀት ተሳታፊ ሆነው የምርጫ ቅስቀሳ ማስታወቂያዎችን ለመስራት ያልተካተቱበትን ምክንያት በደብዳቤ መጠየቃቸውን ገልጸው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ቢሆኑም ምላሽ አለማግኘታቸውን ያብራራሉ።   

''ምርጫ ቦርድ በጋዜጣዊ መግለጫዎቹ ላይ እንኳን አይጋብዘንም'' የሚሉት ዋና አዘጋጁ ''ከዚህ በቀደሙት ምርጫዎችም ሆነ በአሁኑ ምርጫ የፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ላይ የግሉ የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ተሳታፊ አይደረጉም፡፡ ምርጫ ቦርድ እና የብሮድካስት ባለሥልጣን እድሉን ነፍጎናል'' ይላሉ። አክለውም ቅስቀሳው በጽሑፍ ቢቀርብ ከ1 እና 2 ገጽ የበለጠ ቦታ ሰለማይዝ ተጸእኖ አይኖረውም፡፡ ያለክፍያ የሚታተመው የፓርቲዎች ቅስቀሳ በክፍያ በሚታተመው የምርጫ ቦርድ ማስታወቂያ ይካካስ ነበር ብለዋል።    

የሀበሻ ወግ መጽሄት ዋና አርታኢ አቶ ቴዎድሮስ ካሳ የመጽሔቶች በምርጫው ሂደት ያለመሳተፍ ጥያቄ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ሊመልስ ይገባል በማለት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

የሕትመት ሚድያዎቹን ቅሬታ አስመልክቶ ሐሳባቸውን የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የአየር ሰዓት ድልድል ኮሚቴ አባል አቶ አበራ ወንድወሰን በገንዘብ እጥረት ምክንያት የሕትመት መገናኛ ብዙኃንን በቅስቀሳው መርሃግብር ላይ እንዳይካተቱ ማድረጉን ይናገራሉ፡፡

 አብዛኛው የሕትመት መገናኛ ብዙኃን የፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ የገንዘብ አቅም አለመኖር ሁሉንም የህትመት መገናኛ ብዙኃን ለቅስቀሳ ማካተት እንዳልተቻለ ያስረዳሉ።

“ቅስቀሳው ያለ ክፍያ የሚደረግ በመሆኑና በህትመት ሚዲያዎቹ ላይ የሚይዘው የቦታ ስፋት ሚዲያዎቹን የማስታወቂያ ገቢያቸውን ሊያሳጣቸው ይችላል ብለን በማመናችን አላካተትናቸውም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

''ሰፊ ሽፋን ላላቸው ለአንዳንድ የመንግሥት ጋዜጦች ድልድል አድርገናል'' የሚሉት አቶ አበራ ''ይህ አሰራር ከበፊትም የነበረ ነው አቅም እንደሌላቸው የሚታወቁትን ከህትመት የመገናኛ ብዙኃን ባለፈ ለአንዳንድ ቴሌቪዥን እና የማኅበረሰብ ራዲዮ ድልድል አይደረግም'' ይላሉ። 

''ቅስቀሳው ተፈላጊ ወይም ተደማጭ ተብሎ በሚታሰብ ከዜና በኋላ ባለ ሰዓት የሚከናወን ሲሆን የፓርቲዎቹ ቁጥር ስለሚበዛ ሰፊ ሰዓት እንመድባለን'' የሚሉት የአየር ሰዓት ድልድል ኮሚቴ አባል አቶ አበራ በሳምንት ለሚወጡ መጽሔቶች መመደብ ግን ይከብዳል ይላሉ።  

እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ስለ አቅማቸው እና ፍላጎታቸው ከሕትመት ሚድያዎች ጋር መክረዋል ወይ ስንል ላነሳነው ጥያቄ ''እንዲሁ በሳይንሳዊ እሳቤ የሚታወቅ ነገር ነው'' ብለዋል። አክለውም የሰዓት እና የጊዜ እርዝማኔ በምርጫ ቦርድ መርህ መሰረት አድርገው እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት።

ምርጫ ቦርድ ተወካዮች ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኃን የሚያደርጉት የቅስቀሳ መርሃግብር የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው ማስታወቂያ ለመስራት ጣቢያዎቹ ስላስገቡት ደብዳቤ ምላሽ እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች ከመስጠት ተቆጥበዋል።

አስተያየት