ከመቐለ 37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ኣጉላዕ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ረዘነ በርኸ በሕወሓት ታጣቂ ኃይሎች ታፍነው መወሰዳቸው ተሰምቷል፡፡ አቶ ረዘነ የኣጉላዕ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ሆነው ከመሾማቸው በፊት ቂሐን አንደኛ ደረጃ ት/ቤት በመምህርነት ሲያገለግሉ እንደቆዩ ታውቋል፡፡
መቐለ የሚገኘው የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ከአካባቢው ነዋሪዎች እንደሰማው አቶ ረዘነ በጊዚያዊ አስተዳደርነት የተመደቡት ኣጉላዕ ከተማ ቢሆንም ወደ ሌሎች የወረዳው አካባቢዎች ተዘዋውረው ይሰሩ ነበር፡፡
የብልጽግና ፓርቲ አባል አለመሆናቸውን ደጋግመው ይናገሩ ነበር የተባለላቸው አቶ ረዘነ ‹‹ጁንታው ተደምስሷል፣ ተስፋ አታድርጉ›› የሚል ተደጋጋሚ ንግግር ያደርጉ እንደነበር ነዋሪዎች አስታውሰዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ በዛሬው ዕለት ባወጣው መረጃ በትግራይ ክልል 20 ሰዎች በታጣቂ ኃይሎች ሲገደሉ 22 ያህሉ ታፍነው መወሰዳቸውንና 4 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አሳውቋል፡፡