በ 5 የካቲት 2013 ዓ.ም ወንድዬ ያለው የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ሰበር- ዜና በተባለ ከ 157,000 በላይ አባላት ባለው የፌስቡክ ግሩፕ ላይ “ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው ረዳ ሞተው ተገኝተዋል” በማለት አጋርቷል። ከልጥፉ ጋር ተያይዞም ቃሬዛ የያዙ ወታደሮች ምስል እና ሙሉ ቪዲዮ ለመመልከት ያስችላል የተባለ የተሌግራም ማስፈንጠሪያ ይገኛል። ሆኖም ሀቀቼክ ልጥፉን መርምሮ ምስሉ የደብረፅዮን ገ/ሚካኤል እና የጌታቸው ረዳን አስከሬን እንደማያሳየው እና ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።
ከ25 ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሕወሃት በሚመራው የትግራይ ልዩ ኃይል እና በፌዴራል መንግሥት በሚመራው ኃይል መካከል የትጥቅ ትግል ተካሂዷል። 19 ህዳር 2013 ዓ.ም የፌዴራል መንግስት የክልሉን ዋና ከተማ መቐለ ከተማ መቆጣጠሩ ተዘግቧል። ከቅርብ ጊዜ ወዲም የህወሓት ከፍተኛ ሃላፊዎች እና ወታደራዊ መኮንኖች በቁጥጥር ስር እያዋሉ መሆኑንም ተስተውሏል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የህወሃት የጀርባ አጥንት የሚባሉት ስብሃት ነጋ ፣ የቀድሞው የትግራይ ፕሬዝዳንት አባይ ወልዱ ፣ የትግራይ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ተከስተ (ፒ.ኤች.ዲ) እና ሌሎችም ይገኙበታል። 6 ጥር 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሰጠው መግለጫ ሶስት የህወሃት ባለስልጣናት፤ የህወሃት የፖለቲካ መሪ የነበሩት አባይ ፀሃዬ ፣ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን እና የህወሃት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ እና ሌሎች የቀድሞ ወታደራዊ አባላት መገደላቸው ተነግሯል።
ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ24 የካቲት 2012 ዓ.ም አርሚ ታይምስ (Army times) በተባለ የወታደራዊው ማህበረሰብ ዜና እና መረጃ ምንጭ በሆነ ድረ ገፅ። ምስሉ ጥቅም ላይ የዋለው በስልጠና ወቅት ሰለሚደርስ አደጋ በተፃፈ ጽሑፍ ላይ ሲሆን “18 ጥር 2012 ዓ.ም ወታደራዊ ስልጠና በሚሰጥበት ወቅት የበረራ ፓራሜዲክሶች አስቸኳይ የቀዶ ህክምና ጥሪ ደረሳቸው” ሲል ይነበባል። ምስሉ የተነሳው የአሜሪካ ጦር ፎቶግራፍ አንሺ በሆነው የመጀመሪያ ክፍል ሳጅን ጋሪክ ሞርገንዌክ (Sgt. 1st Class Garrick W. Morgenweck) ነበር።
በተጨማሪም በልጥፉ ላይ “ሙሉ ቪዲዮ በቴሌግራም ተለቋል፤ ሊንኩን ተጭነው ይግቡ” የሚል ፅሁፍ ከቴሌግራም ማስፈንጠሪያ ጋር የሚገኝ ሲሆን በቴለግራም ቻናሉ ውስጥ አለ የተባለው ቪዲዮም ይሁን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያለው ምንም አይነት መረጃ አይገኝም።
ምንም እንኳን በቁጥጥር ስር የዋሉ እና የተገደሉ የህወሃት ባለስልጣናት ቢኖሩም ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው ረዳ ስላሉበት ሁኔታ የሚታወቅ መረጃ የለም። ስለሆነም ሀቅቼክ ባደረገው ምርመራ ምስሉ የደብረጺዮን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው ረዳን አስክሬን የማያሳይ በመሆኑ እና ከመረጃው ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።
አጣሪ፡ ርሆቦት አያሌው
ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው
አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ
ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው።