ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ እና ሱዳን ካርቱም በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ኤምባሲ ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር የተባሉ ግለሰቦች አዲስ አበባ ውስጥ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ማስታወቁ የሚዘነጋ አይደለም።
ብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት አውጥቶት በነበረው መግለጫ ላይ ጥቃቱን ሊፈፅሙ ነበር ያላቸውን አካላት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ከመግለፁ ውጪ የዚህ ጥቃት ዕቅድ ባለቤት ማን እንደሆነ በግልፅ ሳያስቀምጥ በጥቅሉ “ከውጭ የሽብር ቡድን አባላት ተልዕኮ በመቀበል” በሚል ነበር ያለፈው።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ባወጣው ዘገባ አዲስ አበባ እና ካርቱም በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ለመፈፀም በማሴር ላይ የነበረችው ኢራን እንደሆነች የአሜሪካ እና እስራኤል ባለሥልጣናት ነግረውኛል ሲል ዘግቧል።
ከዚህ ቀደም አሜሪካ በሰነዘረችው ጥቃት የኢራን ከፍተኛ የጦር አዛዥ የነበሩት ቃሲም ሱሊማኒ መገደላቸውንና በተያያዘም በቅርቡ የአገሪቱ ከፍተኛ የኒኩለር ተመራማሪ የነበሩ ግለሰብ በተመሳሳይ መገደላቸውን ተከትሎ አፍሪካ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የምዕራብያውያን ጥቅሞች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ኢራን የየአገራቱን ደካማ ጎን ስትፈልግ እንደነበር የአሜሪካ የደህንነት ሰዎች ነግረውኛል ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ አስነብቧል።
በፔንታጎን የአፍሪካ ደህንነት ጉዳዮችን የሚከታተለው ክንፍ ዳይሬክተር ሄዲ በርግ እንደተናገሩት ከሆነ 15 ሰዎች የተያዙበት የአዲስ አበባው የጥቃት ዕቅድ ኢራን ለተገደሉባት ወታደራዊ አመራር እና ሳይንቲስ በብቀላ መልክ ምላሽ የመስጠት ዕቅድ አንድ አካል ነበር፤ አቀነባባሪዋም ኢራን ሲሉ ከሰዋል።
አዲስ አበባ የሚገኘው የኢራን ኤምባሲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው ይህ ክስ መሰረተ ቢስና በታመሙ የውጪ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች የሚቀነቀን የሐሰት ወሬ ነው ማለታቸው ተነግሯል።
ከኅዳር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከአውሮፓ፣ አፍሪካ እና እስያ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ጋር በመሆን ጥብቅ ክትትል እና የመረጃ ልውውጥ ሳደርግ ነበር ያለው ብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት የህቡዕ ቡድኑ በአዲስ አበባ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት፣ የጥናት እና የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ ሲያካሂድ እንደቆየ የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች አግኝቻለሁ ማለቱ የሚታወስ ነው።
በህቡዕ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት መካከል ጥቂቶቹ ከመያዛቸው በፊት በኤምባሲው ሕንፃ አካባቢ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ይዘው ለድብቅ ሴራቸው ሲንቀሳቀሱ እንደነበርና የሽብር ጥቃቱን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት መካከል የቡድኑን አባላት ሲመራ የነበረው የ35 ዓመቱ ዓሊ አህመድ አርዳይቶ እና መሐሙድ አብዱልቃኒ የተባለ ሌላ ተጠርጣሪ ከፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመር ቢሮ ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን አገልግሎቱ አውጥቶት በነበረው መግለጫ ጠቁሟል። በጠቅላላ አዲስ አበባ ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ብዛት 15 ነው።