በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት በየአመቱ ታህሳስ እና ሀምሌ 19 የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል በድምቀት ይከበራል፡፡
ታዲያ በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት ያሉ ቢሆንም ለረጅም አመታት በዳበረው ሀይማኖታዊ ልማድ ምክኒያት ወደ ሀዋሳ ደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል እና ድሬዳዋ ቁልቢ ደብረ ሀይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ቀኑን ጠብቆ የሚጎርፈው የምዕመን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ለ አብነት እንኳን አዲስ ዘይቤ ካናገረቻቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ የሀይማኖታዊ ጉዞ አዘጋጆች አንዱ የፊታችን ሰኞ ለሚከበረው ክብረ በዓል 85 መኪናዎችን ማዘጋጀታቸውን እና በርካታ ሰዎች ወደ ሁለቱ አቢያተ ክርስቲያናት ለመሄድ መመዝገባቸውን ገልፀዋል፡፡
«ለገብርኤል ክብረ በዓል ይህ አይነቱ ጉዞ በስፋት የሚደረገው በታህሳስ እና በሀምሌ ወር ነው፡፡አምና ክረምት ላይ በኮሮና ምክኒያት የተጓዦች ቁጥር አንሶ ነበር፡፡ ባሁኑም እንደዛ ይሆናል ብለን ነበር ነገር ግን ቁጥሩ ወደ ድሮው መጠን ተመልሷል፡፡ እኛም ደግሞ ከወረርሸኙ ጋር ተያይዞ በጉዞ ወቅት ማድረግ ያለብንን ቅድመ ጥንቃቄዎች አድርገናል፡፡ለምሳሌ ማስክ እና ሳኒታይዘር በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅቷል» ይላል ካነጋገርናቸው የጉዞ አዘጋጆች አንዱ የሆነው መቅድም ኤልያስ፡፡
ታድያ ምዕመናኑን ለመቀበል የሚስተዋለው ሽር ጉድ እና ከሀይማኖታዊ ክብረ በዓሉ ጎን ለጎን ያለው ድባብ ምን ይመስላል? የሚለውን በሁለቱ ከተሞች የሚገኙት የአዲስ ዘይቤ ጋዜጠኞች ሙሉነህ ካሳ እና ሊድያ ፍቅሩ እንዲህ አስቃኝተውናል፡፡
ከአዲስ አበባ በስተ ምስራቅ 459 ኪሜ ርቀት ላይ ስለሚገኘው ቁልቢ ገብርኤል አመሰራረት የታሪክ መዛግብት እና የሀይማኖት ሊቃውንት ብዙ ፅፈዋል፡፡
ይኸውም በ9ኛው መቶ ክፍለዘመን ዮዲት ጉዲት በአቢያተ ክርስቲያናት እና ንዋያተ ቅዱን ላይ ስታደረስ የነበረውን ጥቃት ሽሽት በጊዜው የነበረው ንጉስ አንበሳ ወድም በአክሱም የነበሩ ታቦታትን ይዞ ወደ ዘዋይ ስለመምጣቱ የሚያትት ነው፡፡ ከ40 አመት በኋላም ታቦታቱን ይዞ ወደ አክሱም ቢመለስም የቅዱስ ገብርኤል ታቦት ግን እዛው ቀርቶ ነበር ይባላል፡፡ ታቦቱን እንዲመልሱ በጊዜው የተላኩት አባ ሌዊ ግን ወደ አክሱም ከመመለስ ይልቅ መልዓኩ ተገልጦላቸው እየመራ ቁልቢ ወደ ተባለው ቦታ እንደወሰዳቸው በዛም ቤተክርስቲያኑ ሊመሰረት እንደቻለ ነው የታሪክ ፅሁፎች የሚያስነብቡት፡፡
ዛሬም ታዲያ ከአመታት በኋለ ለአመታዊ በዓለ ንግሱ ድሬ ደዋ እንደ አዲስ ትደምቃለች፡፡ ገረገራው በቄጤማ መንገዱ በአረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ያሸበርቃል፡፡
በድሬደዋ ሀይማኖታዊ ክብረበዓሉ ብቻ ሳይሆን ምዕመኑ እና ክብረ በዓሉን ለመታደም የሚመጣው ቱሪስት በከተማው ግሩም ቆይታ እንዲኖረው ሽር ጉዱ ሳምንታት ቀድሞ ነው የሚጀምረው፡፡
በድሬዳዋ በሳማራት ሆቴል የእንግዳ መቀበያ ሰራተኛ የሆነችው ወ/ሪት አትጠገብ ሲሳይ « በአሁኑ ክብረ በአል ሁሉም የእንግዳ ማረፊያዎች ተይዘዋል፡፡ ሆቴላችን እንግዶቻችን ከኮሮና ቫይረስ ለመታደግ አስፈላጊውን ቅድመሁኔታ አሟልተን እየተበቅን ነው › ትላለች፡፡
በድሬዳዋ ኤምኤም ሆቴል ማናጀር የሆኑት አቶ ቤካ ለገሰ ደግሞ በበኩላቸው« ከባልፍው በተሸለ መልኩ እንግዶች ይመጣሉ ብለን እናስባለን እስካሁን ድረስ 90% ያህል የእንግዳ ማረፊያ ክፍል ተይዟል፡፡» ብሏል
እንዲህ ዝግጅታቸውን ያጠናከሩት ሆቴሎች ብቻም አይደሉም እንግዶች ሸምተው እንዲሄዱ የንግድ ሱቆቻቸውን በአዲስ እቃ ሞልተው እየጠበቁ ያሉ ነጋዴዎችም አሉ፡፡
ወ/ሮ ለምለም ተካልኝ በድሬዳዋ ከተማ በእጣን ንግድ የተሰማሩ ሲሆን ለክብረ በአሉ የሚመጡ እንግዶች እጣን ለመግዛት ወደ ሱቃቸው ጎራ እንደሚሉ ገልፀው እንደሁል ጊዜው ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ ሳያደርጉ እንግዶቻቸውን በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በሰልባጅ ንግድ የተሰማሩት አቶ ገዛኸኝ አበበ በየአመቱ ክብረ በአሉን ለማንገስ የሚመጡ እንግዶች ድሬዳዋ ደርሰው አሸዋ ሳይገቡ እንደማይወጡ ይገልፃሉ፡፡« በተለይ በአሁኑ ክብረ በአል እንግዶቹ በሚመጡበት ቀን የልብስ ቦንዳ የሚፈታበት ቀን ስለሆነ ጥሩ ገበያ ይኖራል ብዬ አስባለው» በማለት ነበር ለአዲስ ዘይቤ የገለፁት፡፡
መቼም ድሬ ዳዋ ሲባል ቀድመው አእምሮ ውስጥ ከሚመጡት ነገሮች መኃል እነደ ሙሸበክ ያሉ ጣፋጮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በጣፋጭ ምግብ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ሞሀመድ ከድር ታዲያ «ከወትሮ ብዛት ያለው ተጠቃሚዎች እንደሚኖረኝ እጠብቃለሁ፡፡ካለው ልምድ አንፃር እዚህ ከሚመገበው ሰው ይልቅ ደግሞ ይዘውት የሚሄዱት ብዙ ናቸው ፡፡» ይላሉ፡፡
ልክ እንደዚሁ ሁሉ በአመት ሁለቴ ለዚሁ ክብረበዓል የምታሸበርቀው ሌላዋ ከተማ ደግሞ ከአዲስ አበባ 279 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ሃዋሳ ናት፡፡
የሲዳማ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ህገመንግስታዊ ጥያቄው ከተመለሰለት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀዋሳ ከተማ ላይ የሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ-በዓል ላይ መታደም የሚፈለጉ ምንም አይነት ስጋት እንዳይገባቸው ዝግጅት መደረጉን እንዲሁም የፀጥታ ችግር ቢያጋጥም እንኳን ጊዜያዊ ችሎቶች እንዲቋቋሙ ከከተማው አመራሮች እና ከሀይማኖት አባቶች ጋር በመቀናጀት ኮሚቴ በማዋቀር ተሰርቷል፡፡ ይህንንም የከተማ አስተዳደሩ ህዝብ ግንኙነት ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ፤ የሆቴል እንቅስቃሴዎች እና የመዝናኛ ቦታዎችም የየራሳቸውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ታዝበናል፡፡
ለሚመጡ እንግዶች ዐይን ገብ የሆኑ የዘንባባ ባርኔጣ፣ ጥሬ ቡና፣ አሳ፣ የጀልባ ሽርሽር፣ የእጅ አምባር እና የአንገት ጌጣጌጥ ጌጦች ከብዙው በጥቂቱ የእንግዶችን ቀልብ ሳቢዎች ናቸው።
የኬርአውድ ኢንተርናሽናል ሆቴል ማርኬቲንግ እና ኦፕሬሽናል ስራ አስኪያጅ የሆነችው ወይዘሮ ሉሊት አስረስ «እስከአሁን ለክብረ-በአሉ በሚመጡ እንግዶች የመኝታ ክፍሎቻችን ከ 70 በመቶ በላይ ተይዘዋል» ትላለች፡፡
የሀዋሳ ሀይቅ ጀልባ መዝናኛ ሁለገብ ህብረት ስራ ማህበር ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታደሰ አለሙ ደግሞ «ጀልባዎቻችንን አከባቢያዊ ባህል እና የአኗኗር ዘይቤን በሚገልፅ መልኩ የቀለም ቅብ ቀብተን አዘጋጅተናል፤ የሀይቁን ዳርቻዎችንም ለሀይቁ መልካም ገፅታን ለመፍጠር በሚል ፅዱ አድርገን እንግዶቻችንን ሀይቁ ላይ ለማንሸራሸር በጉጉት እየጠበቅን ነው» በማለት የተደረገውን ዝግጅት ለአዲስ ዘይቤ አጫውቷል።
በተጨማሪም መክሊት የተንሳፋፊ መዝናኛ ማህበር ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዘቢባ አህመድ«ወደሀዋሳ የሚመጡ እንግዶች አሳ በስፋት ይመገባሉ፡፡ ኅዳር እና ታኅሣሥ የቅዝቃዜ፣ የውርጭ እና ንፋስ የሚበዛበት ስለሆነ አሳዎች ወደላይ አይወጡም ይደበቃሉ፡፡ እኛም እንግዶች ሲመጡ እጥረት እንዳይገጥመን በሚል ሦስት ፍሪጆችን ቀድመን አዘጋጅተን በቀን ያገኘነውን ያህል በእጥፍ ዋጋ ጭምር እየተረከብን እያከማቸን እንገኛለን» ብላለች፡፡
ወደከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግጅት ከወትሮው ላቅ ባለ መልኩ የሚሰጥ ሲሆን ለአብነት የትራንስፖርት፣ የአልጋ እና ሆቴሎች፣ የመዝናኛ እና ሌሎችምበቂ ዝግጅት ማድረጉን የከተማ አስተዳደሩ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል፡፡
( በሊድያ ፍቅሩ እና ሙሉነህ ካሳ)