ታህሳስ 13 2013 ዓ.ም 🌡#𝐒𝐓𝐎𝐏_𝐀𝐌𝐇𝐀𝐑𝐀_𝐆𝐄𝐍𝐎𝐂𝐈𝐃𝐄 በተባለ ከ3500 በላይ ተከታዮች ባሉት የትዊተር ገፅ አንድ የሰው ምስል እና ሁለት የተለያዩ ባህላዊ መሳሪያዎችን የሚያሳይ ምስል ተለቆ ነበር። ከምስሉ ጋር ተያይዞም መሳሪያዎቹ የተገኙት በዲባቴ ወረዳ (በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን) አስተዳዳሪ ቤት ውስጥ ሲሆን በአካባቢው ያሉ አማራዎችን ለማጥቃት በሚል በቤታቸው ውስጥ መከማቸቱን የሚገልፅ ሀሳብ ያለው ፅሁፍ አለ፡፡ ፅሁፉም “ደበሊ በልጋፎ ይባላል፤ የቤጉ ድባጤ ወረዳ አስተዳዳሪ ሆኖ ብዙዎችን በማስጨፍጨፉ ወደ መተከል ዞን ሹመት አግኝቶ የመጣ ባለስልጣን ነው፤ ቤቱ ሲፈተሽ ይህ ሁሉ አማራን ማስጨፍጨፊያ ተገኝቷል” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መሰረት በምስሉ ላይ የሚታዩት የስለት መሳሪያዎች በድባቴ ወረዳ አስተዳዳሪ ቤት ውስጥ የተገኙ አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል። ስለዚህም የሀሰት መረጃ በማለት ፈርጆታል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት በመተከል ዞን ግጭቶች እና መፈናቀሎች ተከስተዋል ፡፡ በዞኑ እና በአከባቢው ያሉ የእርስ በእርስ ግጭቶች እየተባባሱ በመሆናቸው የቤኒሻንጉል እና የአማራ ክልል መንግስታት እርስ በርሳቸው እየተወነጃጀሉ ነው፡፡ ታህሳስ 13 2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ፒኤችዲ) ፣ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ፣ የጦሩ ዋና አዛዥ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት አሻድሊ ሀሰን አካባቢውን የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ከመተከል ዞን ነዋሪዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል ፡፡ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት እንደዘገበው በታህሳስ 14 2013 ዓ.ም በቡለን ወረዳ በቢኩጂ ቀበሌ ላይ ከባድ ብሄርን መሰረት ያደረገ የጅምላ ግድያ ተከስቷል እንዲሁም ቤቶች ተቃጥለዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት መተከል ዞን በተፈጠረው የጎሳ ግጭት እና የፀጥታ ችግር መካከል በምስሉ ላይ የሚታዩት መሳሪያዎች በአማራዎች ላይ ጭፍጨፋ ለማድረግ በዲባቴ ወረዳ አስተዳዳሪ ቤት ውስጥ ተከማችተው ተገኝተዋል ብማለት በትዊተር ላይ ተሰራጭቷል። ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ በተባለ የምስል ማጣሪያ ለማጣራት እንደተቻለው የተለያዩ ስለታም መሳሪያዎችን የሚያሳየው አንደኛው ምስል ለመጀመሪያው ጊዜ የተለቀቀው መስከረም 10 2012 ዓ.ም በኢትዮጰያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የፌስቡክ ገፅ ላይ ሲሆን በቁጥር 2,765 የሚሆኑት መሳሪያዎች ከደሴ ወደ አዲስ አበባ በአይሱዙ ሲጓዙ በደብረ ብርሃን ከተማ መያዛቸውም ተያይዞ ተገልፁአል። ሁለተኛው ምስል ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ህዳር 17 2013 ዓ.ም ደብረማርቆስ ዴንማርክ በተባለ የፌስቡክ ገፅ ላይ መሳሪያዎቹ በቻግኒ በጅምላ ግድያ ከተሳተፉ መካከል አንዱ በሆነ አንድ ሀብታም ሰው ቤት ውስጥ ተገኝቷል በማለት ነበር የተለቀቀው።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን የፀጥታ ችግር እና የእርስ በእርስ ግጭቶች መኖራቸው እውነት ነው። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መሰረት በትዊተር ገፁ የተሰራጨውን መረጃ ለመደገፍ ጥቅም ላይ የዋሉት ምስሎች አሁን ላይ ያለውን ሁኔታ የሚያሳዩ ባለመሆናቸው ምክንያት ሀሰት በማለት ፈርጆታል።
አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ
ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው
አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ
ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው።