ጥር 26 ፣ 2014

ሀሰት: ምስሉ በበራህሌ ግንባር በአፋር ህዝባዊ ሰራዊት የተያዘን የጦር መሳሪያ አያሳይም

HAQCHECK

ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት መርምሮ ሀሰት ብሎታል።

Avatar: Kirubel Tesfaye
ኪሩቤል ተስፋዬ

Kirubel works as a fact-checker at Addis Zeybe for HaqCheck. He is interested in learning and expanding his writing and journalistic skills.

ሀሰት: ምስሉ በበራህሌ ግንባር በአፋር ህዝባዊ ሰራዊት የተያዘን የጦር መሳሪያ አያሳይም

ከአንድ ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የቴሌግራም ቻናል በጥር 23 ፤ 2014 ዓ.ም “የአፋር ህዝባዊ ሰራዊት በዛሬው ዕለት በበራህሌ ግንባር ገቢ ያደረገው የጦር መሳርያ” የሚል ጽሁፍ በማያያዝ አንድ ምስል አጋርቶ ነበር። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የቴሌግራሙ ፖስት  ከ12000 ጊዜ በላይ መታየት የቻለ ሲሆን ሌሎች ከ46 ሺህ በላይ ተከታይ ያላቸው የቴሌግራም ቻናሎችም አጋርተውታል።

ይሁን እንጂ ሀቅቼክ የምስሉን ትክክለኛነት መርምሮ ሀሰት ብሎታል። 

በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሓት) እና በፌደራሉ መንግስት መካከል የተከሰተው ግጭት ከአንድ አመት በላይ አሳልፏል።

በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የፌደራል መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን በማድረግ የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከትግራይ ክልል በማስወጣት በአፋር እና አማራ ድንበር አካባቢዎች ላይ እንዲቆዩ አድርጓል።    

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጦር ግንባር በመገኘት ጦሩን ለመምራት መወሰናቸውን እስካስታወቁበት ጊዜ ድረስ የህወሓት ሃይሎች ከአዲስ አበባ 183 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኘው የደብረሲና ከተማ ድረስ ገፍተው መጠጋት ችለው ነበር። 

የፌዴራል እና የክልል ልዩ ሃይሎች የመልሶ ማጥቃት እርምጃ መውሰድ ከጀመሩ በኋላም የህወሓት ሃይሎች ወደ ትግራይ ክልል አፈግፍገዋል። ይህን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ወታደሮቹ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው እንደማይገቡና በአማራ እና አፋር ክልል ድንበሮች ላይ እንደሚቆዩ አስታውቋል። ይሁን እንጂ ህወሓት የአማራ እና አፋር ሚሊሽያዎች በተደጋጋሚ ትንኮሳ እያደረጉብኝ ነው ሲል ወቀሳውን አቅርቦ ነበር።

በጥር 16 2014 ዓ.ም የአፋር ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳስታወቀው “የህወሓት ሃይል በአፋር ክልል የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል በሚያስብል ሁኔታ በኪልባቲ እና ራሱ ዞን ፤ በአብ አላ እና መጋሌ ወረዳዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አስታውቋል።

ይህ የቴሌግራም ፖስትም ይህን ወቅታዊ ሁኔታ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው። 

ሀቅቼክ የፖስቱን ትክክለኛነት ለማጣራት የጉግል ግልባጭ ምስል ፍለጋን ተጠቅሞ ያደረገው የፍለጋ ውጤት እንደሚያሳየው ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በነሃሴ 30 ፤ 2013 ዓ.ም ጎልጉል (Goolgule) በተባለ ድረገጽ ላይ “ባጠናቀቅነው የሰኔ ወር በቁጥጥር ስር የዋሉ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች” በሚል ርዕስ ከቀረበ ፅሁፍ ጋር የተያያዘ ነበር።  

በአፋር ድንበር አካባቢ ግጭቶች እንዳሉ የሚሰማ ቢሆንም ምስሉ በአፋር ሚሊሻዎች አማካኝነት በበራህሌ ግንባር የተማረኩ የጦር መሳሪያዎችን አያሳይም። 

በዚህም መሰረት መረጃውን ለመደገፍ ከፓስቱ ጋር የተያያዘውን ምስል ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።  

አስተያየት