ጣና ሀይቅ በአንቦጭ አረም እንደተወረረ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በ2004 ዓ.ም. ነው። የስርጭቱ ፍጥነት የሁሉም ስጋት ሆኖ ትኩረት መሳብ ችሎ ነበር። በሐገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ግለሰቦችና ተቋማት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የአቅማቸውን ለማድረግ እየተረባረቡ እንደሚገኝ ሚድያዎች ዘግበዋል። ከጉልበትና ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ አረሙን ለመንቀል የሚያግዙ ግዙፍ ማሽኖች በተለያዩ አካላት ስለመበርከታቸው በስፋት ተነግሯል። የችግሩን አሳሳቢነት የተገነዘበው የአማራ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ጉዳዩን የሚከታተልና የሚያስፈጽም ራሱን የቻለ ተቋም በአዋጅ አቋቁሟል።
በፍጥነት የሚስፋፋው፣ ቀስ በቀስ የሐይቁን ዳርቻ እያሰፋ ውሃውን የሚያደርቀው የእምቦጭ አረም 9መቶ ሄክታር የሚያህለውን የሐይቁን ክፍል እስከ መሸፈን ደርሶ የነበረ ቢሆንም ከ2013 ዓ.ም. መጀመርያ በፊት በተካሄደ ርብርብ ወደ 4ሺህ ሄክታር ወርዷል። ባሳለፍነው ዓመት በአካባቢው አርሶ አደሮች በዘመቻ በተደረገ ጥረት 90 በመቶ የሚሆነውን የአረሙን ክፍል ማስወገድ ተችሏል። የጣና ሀይቅና ሌሎች ወሃ አካላት ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አያሌው ክንዴ (ዶ/ር) እንዳብራሩት እምቦጭ ራሱን በፍጥነት የመተካት ባህርይ ስላለው በአሁን ሰዓት 2ሺህ 8መቶ ሄክታር የሚሆነው የውሃው ክፍል በአረሙ ተወሯል።
በሀይቁ መግቢያና መውጫ አካባቢዎች ዙሪያ በስፋት የሚገኘው እምቦጭ በተለይ በሰሜንና ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በሚገኙት የፎገራ፣ ሊቦከምከም፣ ጎንደር ዙሪያና ደምቢያ ወረዳዎች በሚገኙ የሀይቁ አዋሳኝ ቀበሌዎች ተበራክቶ ይስተዋላል። በዚህም አካባቢ ሀይቁ በብዛት ከመጎዳቱ በተጨማሪ የአካባቢው ነዋሪዎች ኑሮ ከሀይቁ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ለችግር እየተጋለጡ እንደሆነ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
በወቅቱ የተነገሩ የመገናኛ ብዙኃን ዜናዎች እንደሚናገሩት "ዓለም አቀፉ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማኅበር" ሁለት ማሽኖችን ገዝቶ አበርክቷል። በተመሳሳይ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንድ ማሽን ለክልሉ መንግስት አስርክቧል። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባባር አንድ ማሽን ገዝቶ አስረክቧል። በጥቅሉ በሐይቁ ከአንድ ሌላ ማሽን ጋር አምስት ማሽኖች እንቦጩን ለማጨድ ተሰማርተዋል።
"ዓለም ዓቀፍ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማኅበር" በተለያየ ጊዜ የገዛቸው ሀሉት ማሽኖች ከ237,270 ሽህ ዶላር እንደወጣባቸው ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ማሽኖቹ የሚፈለግባቸውን አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን እና ለብልሽት ሊጋለጡ በሚችሉበት አቀማመጥ እንደሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
ንጉሥ ደምለው በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው እንቦጭን የማጽዳት ዘመቻ ከአንድ የመንግስት ተቋም በፈቃደኝነት ተሳትፏል። እንደ ንጉሡ ደምለው ገለፃ በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች በቀን እየተከፈላቸው ይሰሩ እንደነበር ገልፆ። ስራውን ለማስተባበር በቦታው ከ45 ቀናት በላይ ቢቆይም "ማሽኖች አገልግሎት ሲሰጡ አለማስተዋሉን" ነግሮናል።
ማሽኖች አገልግሎት መስጠት ማቋረጣቸውን አስመልክቶ የጣና ሀይቅና ሌሎች ወሃ አካላት ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት ማሽኖች ብልሽት ሲገጥማቸው ለመጠገን የጋራጅ ችግር፣ ማሽኖችን ለማንቀሳቀስ እራሱን የቻለ ወደብ አለመኖሩ፣ የማሽኖች የነዳጅ ወጭ እና የማሽኖች መለዋወጫ በሀገር ወስጥ አለመገኘቱ በሚልዮን የሚገምት ገንዘብ ለወጣባቸው እና በዙ ተስፋ ለተጣለባቸው ማሽኖች አገልግሎት አለመስጠት በምክንያትነት ይገልፃሉ።
እንደ ዶ/ር አያሌው ወንዴ ገለጻ “ማሽኖችን የማስተዳደር ስራ ለኤጀንሲው አስቸጋሪ ሆኖብናል” ይላሉ። ለዚህም የኤጀኒሲው ሰራተኞች የግብርና ባለሙያ እንጂ የዘርፉ ባለሙያ አለመሆናቸውን በመግለፅ እንደ ዶ/ር አያሌው ማሽኖች በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ለማድረግ የማሽኖች አስተዳዳሩን ሥራ ሌላ አካል እንዲያስተዳድረው ቢደረግ የተሻለ ነው ይላሉ። ለዚህም በዘርፉ የተሰማሩ የክልሉ የልማት ድርጅቶች ቢሰሩት የተሻለ እንደሚሆንና ይህን ለማደረግ ከሚመለከተው አካል ጋር ለመነጋገር እንዳቀዱ ነገረውናል።
ዶ/ር ሰለሞን ክብረት ዓለም ዓቀፍ የጣናን መልሶ ማቋቋም ማኅበር ሊቀመንበር ናቸው። ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ማኅበሩ ሁለት የእንቦጭ ማጨጃ ማሽኖችን በ2010 እና በ2012 ዓ.ም. ገዝቶ ለክልሉ መንግስት በስጦታ ማበርከቱን አስታውሰው። ይህም ማሽኖች ተገዝተው መላካቸውን የወጭ ምንዛሬ እጥረቱን የቀረፈ ነበር” ይላሉ። ማሽኖቹ ከእነሙሉ መለዋወጫቸው ከመገዛታቸው በተጨማሪ ስለማሽኑ አጠቃቀም አስፈላጊው የሰው ኃይል ስልጠና በባለሙያ መሰጠቱን ገልፃዋል።
ሦስተኛውን ማሽን በ160,980 ዶላር ገዝቶ ለመላክ ዝግጀጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት እንደሚላክ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
ማሸኖቹ ያለ አገልግሎት መቆማቸውን በተመለከተ ዶ/ር ሰለሞን ሲያብራሩ ከክልሉ መንግስት ጋር በተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን አስታውሰዋል። “የክልሉ መንግስት በስጦታ የተሰጡትን ማሽኖች በደንብ የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር። ችግሩን ለመቅረፍ የፌደራል እና የክልሉ መንግስት በጋራ አቅደው እና በጀት መድበው ሊሰሩ ይገባል” ይላሉ። በዚህም ለማሽኑ ስራ የሚያስፈልጉ ወጭዎችን በመሸፈንና ህዝቡንም በማስተባበር አሁን ያለውን ክፍተት መሸፈን እንደሚቻል ያምናሉ።
በተጨማሪም እንደ ዶ/ር ሰለሞን ገለፃ "የፌደራል መንግስት ለጣና የሰጠው ትኩረት እጅግ አነስተኛ ነው" የሚል አስተያየት አላቸው። "የክልሉ መንግስትም ያለአጋዥ ብቻውን የጣናን ጉዳይ ለመፍታት እንዲባዝን ሆኗል። ጣና በዩኔስኮ የተመዘገበ ዓለም አቀፍ ቅርስ ስለሆነ ዓለማቀፍ ማኅበረሰብ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል” ይላሉ።
ሚልዮን ብሮች በወጣባቸው ግዙፍ ማሽኖች ያልተሳካው የጣና ሐይቅን እምቦጭ የማስወገድ ስራ በያዝነው ሳምንት ከ120 ሺህ ሰዎችን በማሳተፍ በሰው ኃይል ተጀምሯል። ዘመቻው የሚደረገውን ሐይቅ በሚያዋስኑት በማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ ከ30 በላይ በሆኑ ቀበሌዎች ነው። ለዚህ ተግባር የክልሉ መንገሥት 20 ሚልዮን ብር መድቧል። የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አያሌው ወንዴ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት በአሁኑ ዘመቻ ከ2ሺህ 8መቶ ሄክታር በላይ የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ታቅዷል። በእንቦጭ ነቀላ ዘመቻው ከሰው ኃይል በተጨማሪ በስዓት የሚከፈላቸው "እስካባተር" ማሽኖች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። በተጨማሪ ትልልቅ የጭነት መኪኖች በመጠቀም የተወገደውን እንቦጭ የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ መሆኑን የኤጀንሲው ስራ አስኪያጅ ገልፀዋል። ስራቸውን በሙሉ አቅማቸው ለመፈፀም የበጀት ዕጥረት እንደነበረበት ገለፀው “በተለይ በያዝነው ዓመት ክልሉ በነበረው ጦርነት የበጀት እጥረቱ ተባብሷል” ብለዋል። ስለሆነም የበጀት እጥረቱን ለመቅረፍ ሀሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።