ከ1970ዎቹ ጀምሮ እስከ ቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ ራድዮ ዘወትር ማለዳ የተደመጠው “ቡና ቡና” የተሰኘ መዝሙር በብዙዎች የማይረሳ ነው።
“የኢኮሚ ዋልታ ቡና ቡና የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና
የእድገታችን ገንቢ ቡና ቡና አውታር ነው ቡናችን ቡና ቡና
በዓለም ገበያ የውጭ ምንዛሪ ላገር የሚያስገኘው ቡና ቡና
በጥራት በጣ’ሙ ተደንቆ ተወዶ በጣም የታወቀው ቡና ቡና”
ለእለታዊ የቡና ዋጋ መግለጫ ማጀቢያ ሆኖ ለረዥም ዓመታት ያገለገለው መዝሙር ግጥምና ዜማ ደራሲ መምህር ታረቀኝ ወንድሙ ይባላሉ። ሙዚቃውን የተጫወቱት በወቅቱ በጅማ ከተማ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ተወዳጅነት እና እውቅና ያተረፈው “የጅማ ቦሣ” የኪነት ቡድን አባላት ናቸው። የኪነት ቡድኑ መስራችና የግጥምና ዜማ ደራሲ መምህር ታረቀኝ ስለ ቡድኑ አመሰራረት ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ “የማስተማር ስራዬን እንዳጠናቀቅኩ ከትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ወደሚገኘው ‘ኪቶ ሜዳ’ የመሄድ ልምድ ነበረኝ። ፀሐይ ወደ መጥለቂያዋ ስታዘቀዝቅ በነፋሻው አየር፣ በዝግታ እርምጃ ወደ ኪቶ ሜዳ መጓዝ ያስደስተኛል። ከእለታት በአንዱ መስከረም 2 ቀን የሚከበረውን የአብዮት በዓል ለማድመቅ በሜዳው ላይ ወታደራዊ ሰልፍ ይለማምዱ የነበሩ ህፃናትን በተመለከትኩ ጊዜ አንድ የጎደለ ነበር እንዳለ ተሰማኝ” ይላሉ። ክፍተቱን መሙላት ስለሚያስችላቸው ሁኔታ ሲያሰላስሉ ከቆዩ በኋላ የሰልፉን አሰልጣኝ “ከወታደራዊ ሰልፉ በተጨማሪ መዝሙር ቢታከልበትስ” የሚል ሐሳብ አቀረቡ። ህጻናቱ በዚህ መልኩ ከተሰባሰቡ በኋላ የ“ጅማ ቦሣ” በሚል ስያሜ ታዳጊ ሕጻናት ኪነት ቡድን ተመሰረተ። ጊዜው 1969 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ነበር። ቡድኑ ጅማ 04 የሚለውን መጠሪያ አብዛኛዎቹ ሕጻናት ቀበሌ 04 የሚኖሩ በመሆናቸው የተሰጠ ሲሆን “ቦሣ” ደግሞ በጅማ ካሉ 27 ቀበሌዎች የአንዱ መጠሪያ ነው። የመጀመሪያዎቹ የቡድኑ አባላት ከ7 እስከ 13 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት 30 ህፃናት ነበሩ።
መምህር ታረቀኝ በ1970 ዓ.ም. ለተከበረው የመስከረም ሁለቱ የአብዮት በዓል “ለአብዮቴ” የተሰኘውን መዝሙር ግጥም ጽፈው፣ ዜማ አዘጋጅተው፣ በህጻናቱ አስጠንተው ለዕይታ አቅረቡ። መዝሙሩ የኪነት ቡድኑ የመጀመርያ ስራ ነበር።
“ለአብዮቴ ለአብዮቴ
ይፍሰስ ደሜ ይከስከስ አጥንቴ”
ለአብዮቴ በሚለው ግጥምና ዜማ እውቅናን ያተረፈው ቡድኑ ከጅማ ከተማ አልፎ እንደ ናዝሬት፣ አምቦ ፣በደብረዘይትና በመሳሰሉት አውራጃ እና ወረዳዎች እና በሌሎችም የኢትዮጵያ ከተሞች እየተጋበዘ ሥራዎቹን ማቅርብ ጀመረ።
የተለያዩ ስብሰባዎችና ክብረ በዓላትን ለማድመቅ፣ ትርጉም ያላቸው ማኅበራዊ መልእክቶችን ለማስተላፍ ተመራጭ ለመሆን በቃ። በ1971 ዓ.ም. የጅማ ቦሣ 04 ታዳጊ የሕጻናት የኪነት ቡድን ከቡና እና ሻይ ባለ ሥልጣን ጥሪ ቀረበለት። መምህር ታረቀኝ ወቅቱን ሲያስታውሱ “ጥያቄውን እስከተቀበልኩበት ጊዜ ድረስ ስለ ቡና ግጥም እና ዜማ የማዘጋጀት ሐሳብ አልነበረኝም” ይላሉ። የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱን ትዕዛዝ በመቀበል የተዘጋጀው ዜማ ተቀባይነቱ ሲጨምር፣ በመላው ኢትዮጵያ በሚሰራጨው ብቸኛ ራድዮ ጣቢያ በየዕለቱ ሲደመጥ የቡድኑ መጠሪያ እስከመሆን ደረሰ። ዋናውን ስያሜ በልጦ “ቡና ቡናዎች” የሚለው ቅጥያ በመላ ኢትዮጵያ ናኘ።
ለ25 ዓመታት ተቋሙን እና ምርቱን ላስተዋወቀበት መዝሙር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምንም ዓይነት ክፍያ አልፈጸመም። መምህር ታረቀኝ “ብዕር እንኳን አልገዛልኝም። ለእኔም ሆነ ለዘማሪዎቹ ካኪ ዩኒፎርም ከማሰፋት ባለፈ ለአገልግሎታችን አልተከፈለንም” ይላሉ።
“የኪነት ቡድኑ የራሱ የሆነ የገቢ ምንጭ አልነበረውም። ጊዜውም ለገንዘብ የሚሰራበት አልነበረም። ለሐገር ፍቅር፣ ለእድገት እንጂ ለእኔ አይባልም። የገንዘብ ክፍያ መጠየቅ ሀገርን እና ወገንን እንደመክዳት ይቆጠር ነበር። አስተሳሰቡም በሰው አዕምሮ የለም። ዋነኛው ክፍያ ህዝብ ፊት መቅረቡ፣ በህዝብ ተወዳጅነት ማግኘቱ እና በዚያ የሚገኘው ደስታ ነበር” ብለውናል።
ከብዙ ኢትዮጵያውያን አዕምሮ የማይጠፋው “ቡና ቡና” መዝሙር ግጥምና ዜማ ድራሲ ከ”ቡና ቡና” በተጨማሪ ከ60 በላይ ግጥምና ዜማዎች መስራታቸውን ይናገራሉ። “ዕውቅናዬ የሥራዬን ያህል አይደለም” የሚሉት መምህሩ “ግጥምና ዜማዎቹ አብዮቱን የሚደግፉ፣ ሴቶችን የሚያበረታቱ፣ ሥራ ወዳድነትን የሚሰብኩ” እንደነበሩ ይናገራሉ።
በወቅቱ ታዋቂ እና ተወዳጅ ከነበሩት መካከል “ለአብዮቴ”፣ “ጥቁር እንቁ”፣ “ለዓለም ሰላም”፣ “ዋሻው ተጣሰ”፣ “እንሂድ ዘመቻ”፣ “ሥራ”፣ “ሴቷም ቆማለች በንቃት”፣ “ጤንነት መብት”፣ “አለ ገና” እና የመሳሰሉ ይገኙበታል። ሥራዎቹ ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቨዥን የድምጽ ክምችት ውስጥ ቢገኙም አዲሱ ትውልድ የሚሰማበት እድል አለማግኘቱ ቅር እንደሚያሰኛቸው ደራሲው መምህር ነግረውናል።
መምህር ታረቀኝ ካዘጋጇቸው መዝሙሮች በልዩነት የሚያስታውሱት “ጥቁር እንቁ”ን ነው። “ኢትዮጵያን የሚያወድሰው “ጥቁር እንቁ” የተሰኘ ስራዬ አሁንም በዓይነ ህሊናዬ ይመላለሳል። ህጻናቱ መድረክ ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም የለበሰችውን ሴት እየዞሩ፣ እየተንበረከኩ፣ እየቃኙ ነበር የሚዘምሩት። የመድረክ እንቅስቃሴው ልዩ ነበር። የሀገር ፍቅር ያለውን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ታዳሚ በእንባ ያጠምቃል” በማለት ከ44 ዓመት በላይ ወደኋላ ተጉዘው ትውስታቸውን ያጋራሉ።
ከግጥም እና ዜማው በተጨማሪ የመድረክ ላይ እንቅስቃሴውን (ኬሪዮግራፊ) በጥሩ ሁኔታ ያዘጋጁት መምህር ታረቀኝ ከሙዚቃ መሳሪያ ክራር ይሞክራሉ። “በወቅቱ ከጅማ ቦሣ በተጨማሪ “ጅሬን” የሚባል የታዳጊ ኪነት ቡድን ቢኖርም ስኬታማ አልነበረም። በግጥምና ዜማ ጥራት ብቻ ሳይሆን በአቀራረብም የወቅቱ ተመራጭ ቡድን ጅማ ቦሣ ሆኖ አልፏል” ይላሉ። በወቅቱ በጅማ ከተማ የነበረውን ኪነ-ጥበባዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ እንዲህ ይናገራሉ። በጅማ ከተማ 27 ቀበሌዎች ውሰጥ እያንዳንዱ ቀበሌ የወጣቶች የህፃናት እና የሴቶች ኪነት ቡድን የነበረ ሲሆን በየዓመቱ በሚካሂደው ውድድር በወጣቶች የቦሳ 02 የወጣቶች ኪነት ቡድን ቀዳሚ ሲሆን፤ የቦሳ 04 የታዳጊ ህፃናት ኪነት ቡድን ደግሞ በህጻናት ቀዳሚ ነበር ይላሉ።
መምህር ታረቀኝ “ክለባችን ግጥም እና ዜማ ከሌላ ሰው ተቀብሎ አያውቅም። ሁሉንም ራሴ ነኝ የሰራኋቸው። ግጥም ብቻ ወይም ዜማ ብቻም አልሰራም። እኔ ጋር ግማሽ የለም ሙሉውን ነው የምሰራው” ብለውናል። የግጥምና ዜማ ድረሰት ሲያዘጋጁ ዜማውን ያስቀድማሉ። በናሽናል ሶኒ ቴፓቸው ካሴት ላይ በድምጻቸው በማንጎራጎር ይቀርጹታል። ደጋግመው ካደመጡት በኋላ ለዜማው የተስማማ ግጥም ይጽፋሉ።
በዚህ ሁኔታ የመጀመርያው ሂደት የተጠናቀቀው ግጥምና ዜማ ቀበሌ 04 አዳራሽ ይጠናል። የመድረክ እንቅስቃሴው እና ቅንብሩም እዚያው አዳራሽ ውስጥ ተጠንቶ የዝግጅት ሂደቱ መጠናቀቁ ሲረጋገጥ ለሕዝብ ዕይታ ይቀርባል።
በዚህ መልኩ እስከ 1975 ዓ.ም. የቆየው የጅማ ቦሣ 04 ታዳጊ ሕጻናት የኪነት ቡድን ከ“አብዮታዊ ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር (አእወማ)” ጋር እንዲቀላቀል ተደረገ። ይህ የሆነው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ በተጠቀሰው ዓመት መምህር ታረቀኝ በበሥራ ምክንያት ወደ ወደ ሶቭየት ዩኒየን መጓዛቸው የመጀመርያው ምክንያት ሲሆን ዘማሪዎቹ ከህጻንነት እድሜ ስላለፉ ወደ ወጣቶች ቡድን እንዲቀላቀሉ መወሰኑ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ የአብዮታዊ ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር ውሳኔ ለታዳጊዎቹ የማይመች ሁኔታን በመፍጠሩ ቡድኑ ሊበተን እንደቻለ ነግረውናል።
የቡድኑ መስራች “መዝሙሮቹን የአሁኑ ትውልድ እንዲያውቃቸው አልተፈቀደለትም” የሚል ሐሳብ አላቸው። ወቅቱ በሚፈቅደው መሳሪያ በጥሩ ሁኔታ ቢቀረጹም ለትውስታ እንኳን እንዲደመጡ አለመደረጉ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው አልሸሸጉም። ያለ ምንም ክፍያ በሀገር ፍቅር ስሜት ብቻ ብዙ ቢከፉም የአበርክቷቸውን ያህል እንዳልተጠቀሙ ይሰማቸዋል።መስከረም 17 ቀን 1944 ዓ.ም. በካፋ ክፍለ ሀገር በአሁኑ ቤንች ማጅ ጎልዴያ ከተማ የተወለዱት መምህር ታረቀኝ በአሁን ሰዓት የ70 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ናቸው። የከቀድሞ ትዳራቸው አምስት ልጆች አፍርተዋል። በደርግ ዘመን በተሰጣቸው አነስተኛ የቀበሌ ቤት፣ ለኑሮ በማትበቃ ጡረታ በብቸኝነት መኖር ከጀመሩ ሃያ ዓመታትን እንዳስቆጠሩ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።