ጥር 25 ፣ 2014

ያለ እድሜያቸዉ ሥራ ላይ የተሰማሩት የሀዋሳ ህፃናት

City: Hawassaማህበራዊ ጉዳዮች

አሁን ላይ ከ 1ሺህ በላይ በጎዳና ላይ ኑሮአቸውን ያደረጉ ህፃናት አሉ።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ያለ እድሜያቸዉ ሥራ ላይ የተሰማሩት የሀዋሳ ህፃናት
Camera Icon

ፎቶ፡ እያሱ ዘካሪያስ

ማርቆስ ቱራሶ በሀዋሳ ከተማ በአንድ ጎዳና ጥግ የሚኖር የ6ዓመት ህጻን ነዉ። እንደ እኩዮቹ ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ እድል አላገኘም። ከአንድ በእድሜ እኩያ ጓደኛዉ ጋር ሁልጊዜ በሌሊት ተነስተዉ 'ሻሻያሌዉ' ቆሻሻ ያለዉ በማለት በየመንደሩ እየዞሩ ቆሻሻ ይሰበስባሉ። 

"እኛ በብዛት ሆቴሎች አከባቢ ነዉ የምንሄደዉ ምክንያቱም ህፃን ስለሆንን ቅድሚያ ቆሻሻዉን ለእኛ ነዉ የሚሰጡን” ይላል ማርቆስ። “ትምህርት አልማርም ምክንያቱም እድሜዬ ገና ስለሆነ ነዉ ጓደኛዬ ግን ይማራል ህይወታችንን ብቻችንን ነዉ የምንመራዉ ጎዳና ላይ ቁጭ ብሎ ከመለመን ይሻላል ብለን ነው የምንሰራዉ።” ይላል።

በሀዋሳ ከተማ ዘወትር ከማለዳዉ አስራ አንድ ሰአት ጀምሮ እድሜያቸዉ ከ5-15 አመት የሚሆኑ ታዳጊ ህጻናት በአህያ ላይ ትልቅ እና ሰፊ ጣውላ በማዘጋጀት አንድ ወይም ሁለት በመሆን በየመንደሩ በመዞር ከሆቴሎች፣ ከግሮሰሪዎች እንዲሁም ከመኖሪያ ቤቶች ቆሻሻዎችን ሲሰበስቡ ማየት የተለመደ ነዉ። 

እነዚህ ህጻናት በብዛት ከሲዳማ ክልል አጎራባች ከተማዎች ወደ ከተማዋ በተለያዩ ምክንያት የፈለሱ እና የሚረዳቸዉ የሌለ ህፃናት ሲሆኑ አብዛኛዎቹ እድሜያችዉ ለስራ ያልደረሰና የትምህርት እድል እያገኙ አለመሆኑን አዲስ ዘይቤ ከልጆቹ አንደበት ሰምታለች።

ሌሊት ላይ ያለዉ ቅዝቃሴ ብርዱ ሀይለኛ በመሆኑ ከንፈራቸዉን ይሰንጣጥቃል ይህ ብቻ አይደለም አንድ አንድ ሰዎች ቆሻሻ ካስደፉ በኃላ የሚጠየቁትን ብር ስለማይሰጡ ለጥል እንደሚጋበዙም የነገሩን አሉ።

ታዳጊ ሌንደቦ ይባላል አስራ አምስት ዓመቱ ነዉ በየመንደሩ እየዞረ ቆሻሻ መልቀም ከጀመረ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል እሱ እንደሚለዉ አሁን ሰራዉ ቀዝቅዟል በበዓላት ቀናት ላይ ግን በብዛት የምንሰራበት ዕለት ነው። ሌንዴቦ ቆሻሻ የሚሰበስብበትን አህያ ተከራይቶ  በቀን እስከ ሀምሳ ብር  ያገኛል።

በቆሻሻ መሰብሰብ ስራ ላይ የተሰማሩት ህጻናት አብዘሀኛዎቹ በሚባል ደረጃ ለከፋ የጤና ችግር እየተዳረጉ እንደሆነ ያነጋገርናቸዉ ህጻናት ይናገራሉ። ስራዉ ጉልብት የሚጠይቅና ከቦታ ቦታ መዘዋወር የሚፈልግ አድካሚ ስራ በመሆኑ ህጻናቱ ከእድሜያቸዉ በላይ እየሰሩ በመሆኑ የድካም ሰሜት እንደሚሰማቸው ይናገራሉ።

እናቴ እና አባቴ ገጠር ነዉ የሚኖሩት ጠፍቼ ነዉ ወደ ሀዋሳ የመጣሁት ያለን ደግሞ ታዳጊ አዱኛ ነዉ "ከቤተሰቤ ጋር አለመግባባት ሲፈጠር በሰባት ዓመቴ ሀዋሳ መጣሁ አሁን አስር አመቴ ነዉ ቆሻሻ እየሰበሰብኩ በማገኘዉ ገንዘብ ነዉ ራሴን የማስተዳደርዉ። ትምህርቴን በማታው ክፍለጊዜ እየተከታተልኩ  ሦስተኛ ክፍል ደርሻለሁ ለወደፊቱ ኢንጅነር ነዉ መሆን የምፈልገዉ።" 

አብዘሀኛዎቹ ሀጻናት ስራ ሰረተዉ በሚያገኙት ገንዘብ ራሳቸዉን ስለሚያስተዳድሩ አጋጣሚዉን እንደ መልካም አጋጣሚ እንጂ እንደ ጫና ሲቆጥሩት አይታይም። አብዘሀኛዎቹ በሚባል ደረጃ በስራ ላይ በመሆናቸዉ በጣም ደስተኛ ናቸዉ።

በከተማዋ በአንድ አካባቢ ቆሻሻ ሲጥል ያገኘነዉ የሰብለ ግሮሰሪ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ሲሆኑ እሳቸዉም በየቀኑ ቆሻሻ እንደሚጥሉ ይናገራሉ "ግሮሰሪ እንደመሆኑ መጠን በየቀኑ ቆሻሻዎች አይጠፉም የሽንኩርት ልጣጭ፣ ተስተናጋጆች የተጠቀመበት እና የጣላቸዉ የተለያዩ ቆሻሻዎች ፣የፍየል እርድ ለሆቴላችን ስለምናደርግ የእነርሱን ቆዳ ሌሎች መወገድ ያለባቸዉን ለልጆቹ እንሰጣለን ብዛት ስራ ወዳዶች ናቸዉ እነኝህ ልጆች ተለዋጭ ስራ ቢያገኙ ዉጤታማ ይሆናሉ” ይላል።

የህፃናት መብት እና ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር በአለም ደረጃ እና በአህጉር አቀፍ የወጡ የተለያዩ ህግጋት አሉ ይህን ኢትዮጵያ በመቀበል በህገመንግስቷ ላይ አስፍራ ትገኛለች። 

ረ/ፕሮፌሰር ሽመልስ አሻግሬ የሐዋሳ ዮኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ናቸዉ። ህፃናትን ያለ እድሜያቸዉ ስራ ማሰራት የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156 የሚያስቀጣ እና የጉልበት ብዝበዛ እንደሆነ አንስተዉ ተከታዮ ላይ አጽንኦት ሰጥተውታል።

"በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 36  ላይ ህፃናት ጉልበቱን ከሚበዘብዙ ልማዶች መጠበቅ በትምህርት በጤናዉ እና በደህንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ስራዎች እንዲሰራ ያለመገደድ እና ከመስራት የመጠበቅ መብት እንዳለዉ ተቀምጧል ። ከዚህ በተጨማሪም የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156 እንደተቀመጠው እድሜዉ ከ 15 በታች ያለ ህፃን መቅጠር ፣ በስራ ላይ ማሰራት የጉልበት ብዝበዛ እንደሆነ ተቀምጧል ። በአሠሪና ሰራተኛ ህግጋት ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን የማያከብሩ  ከገንዘብ ቅጣት እስከ እስራት ድረስ እንዲቀጡ ይወስናል" 

በሐዋሳ ከተማ ከዕለት ከአጎራባች ወረዳዎች እና በዙሪያ ከሚገኙ አከባቢዎች ወደ ጎዳና ላይ የሚወጡ የህፃናት ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ በተደጋጋሚ ቢነሳም የከተማ አስተዳደሩ የችግሩን አሳሳቢነት የሚመጥን ሥራ እየሰራ አይደለም በሚል ይወቀሳል።

ህፃናት ያለ እድሜያቸው ከአቅማቸው በላይ ስራዎችን እንዲሰሩ መደረጉ ከከተማዋ ባለፈ በክልል ደረጃ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል። በታክሲ ረዳትነት፣ ቆሻሻ በመሰብሰብ እንዲሁም በሌሎች የጉልበት ስራ የተሰማሩ  ህፃናትን ቁጥር ቀላል አይደለም። 

በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ ኑሯቸዉን ያደረጉት ከአምስት መቶ በላይ ህፃናትን ወደ ኤልሻዳይ ተቋም ዉስጥ ገብተዉ የተሃድሶ ስልጠና እየተሰጣቸዉ እንደሆነ ሰምተናል። የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሴቶችና ህፃናት መብት እና ደህንነት ማስጠበቅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አክሊሉ ኤርጎ ስለ ህፃናቱ ያለ እድሜያቸዉ ስራ እንዲሰሩ መደረጉን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳት እንዳለዉ በማንሳት  እንደ ከተማዋ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለአዲስ ዘይቤ ነግረዋል።

"አሁን ላይ ከ 1ሺህ በላይ በጎዳና ላይ ኑሮአቸውን ያደረጉ ህፃናት አሉ። እነኝህን ህፃናት በማንሳት እና የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ትምህርት ገበታቸዉ ፣ ወደ ቤተሰባቸዉ እና እጅሜያቸዉ ከ16 በላይ የሆኑትን ደግሞ በትንሹ ራሳቸዉን የሚችሉበት ስራን በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ። የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅም እንደሚደነግገዉ ህፃናት ወደ ትምህርት ገበታ እንጂ ያለ እድሜያቸዉ ስራ መስራት የለባቸዉም የሚለዉን ድንጋጌ እኛም ተቀብለን ወደ መሬት አዉረደናል ይህም ለዉጥ አምጥቷል።"

አቶ አክሊሉ አክለዉም በተለይ ያለ እድሜያቸዉ ቆሻሻ የሚሰበሰብ ህፃናት እና በታክሲ ላይ ረዳት ሆነዉ እየሰሩ የሚገኙት ትክክል እንዳልሆነ እና እንደ ተቋም ልጆቹን ወደ ቤተሰባቸው የመቀላቀል ስራ መስራት እንደተጀመረ አጫዉተዉናል።

አስተያየት