ጥር 24 ፣ 2014

ለኢንቨስትመንት እንቅፋት የሆነው የከተማ መሬት አቅርቦት

City: Addis Ababaኢኮኖሚ

ኢንቨስትመንቱን የሚያስተዳድሩ ቢሮዎችና ኮሚሽኖች የኢንቨስትመንት መሬትን መቆጣጠር ይገባቸዋል።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ለኢንቨስትመንት እንቅፋት የሆነው የከተማ መሬት አቅርቦት
Camera Icon

Credit: Emad Aljumah/Getty Images

‘አንድ ሚልየን ዲያስፖራ ወደ ሀገር ቤት’ ጥሪን ተከትሎ በተለያዩ ዘፎች የኢንቨስትመንት እድሎችን የማስተዋወቅ መርሃ ግብሮች በርካታ ናቸው። ከእነዚህ መርሃ ግብሮች አንዱ የነበረው በጥር ወር መጀመሪያ የተካሄደው ‘የዲያስፖራ ኢንቨስትመንት ፎረም’ ይገኝበታል።

በመድረኩ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ውስጥ ብዙዎቹ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ የተሳለጠ እንዲሆን ብዙ ስራዎች ይቀራሉ ሲሉ ይሞግታሉ። ነዋሪነታቸውን በዳላስ ቴክሳስ ያደረጉት ፀሀይፅድቅ ቤተማርያም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ እንቅስቃሴ ከጀመሩ 3 ዓመት እንደሆናቸው ይናገራሉ።

ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በአሜሪካ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት ፀሀይፅድቅ ቤተማርያም፤ በደብረብርሃን ከተማ ባለ5 ኮከብ ሆቴል ለመገንባት የሚያስችላቸዉን መሬት ለመጠየቅ በዳላስ ቴክሳስ ከሚገኙ ጓደኞቻቸው ጋር ወደ ደብረብርሃን ተጉዘዋል።

እንደ ፀሀይፅድቅ ገለፃ ከሆነ በከተማዋ ለሆቴል የሚሆናቸውን መሬት በ10 በመቶ የሊዝ ክፍያ ከፍለው ተረክበዋል። ይሁን እንጂ “የዲዛይን ስራዎች ከጨረስን በኋላ መሬቱ የተገዛበት ገንዘብ የሚመጥነው አይደለም፤ ገንዘብ ትጨምራላችሁ” ተብለን ስራችንን አቆምን ፀሀይፅድቅ ቤተማርያም ይገልፃሉ።

“ለኢንቨስትመንት መሬት ማግኘትን የሚያከብደው መሬቱን የሚፈቅዱት አካላት የማዘጋጀት ቤትና ካቢኔ አባላት መሆናቸው ይመስለኛል። ይህ ሁኔታ ለፈለጉት የመስጠት፣ ዝምድና እና ሙስናን መሰረት አድርጎ እንዲሰጡ የተመቻቸ እድል ይሆናል” ብለዋል ባለሀብቱ።

በእኔ ምልከታ ከሆነ “ኢንቨስትመንቱን የሚያስተዳድሩ ቢሮዎችና ኮሚሽኖች የኢንቨስትመንት መሬትን መቆጣጠር ይገባቸዋል። ቢሮዎቹ ለኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት በሚጠይቋቸው መስፈርቶች የተሟሉ ሆነው ሲያገኟቸው ከፈቃዱ ጋር መሬቱን ቢያስረክቡ የተሻለ ይመስለኛል” ይላሉ።

መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ የሚመጡ ባለሀብቶችም ሙስናን ማጋለጥ አለባቸው የሚሉት ፀሀይፅድቅ፤ መንግስትም እነዚህን ባለመታገስ እንዲሁም ሙያና አቅም ያላቸው ባለሙያዎችን በመመደብ ችግሮችን ሊያቃልል ይገባል ይላሉ።

የሌሎች ሀገራት ተሞክሮን ማምጣት በተደጋጋሚ እንደመፍትሔ ሲቀመጥ እንሰማለን የሚሉት ባለሀበቱ “የሌላ ሀገር ተሞክሮ ቀጥታ መገልበጥ አስፈላጊ ባይሆንም፤ አሰራሮችን መውሰድ ግን ያስፈልጋል ይሉና እርሳቸው በሚኖሩባት ሀገር አሜሪካ የኢንቨስትመንት አገልግሎት ለማግኝት በአካል ወደ ቢሮ መሄድ አይታሰብም። ሁሉም ጉዳይ በበይነመረብ የሚያልቅ መሆኑ ሀላፊዎች ማንነትን መሰረት እንዳያደርጉና ሙስና ለመከላከል አግዟቸዋል” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በ2014 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው 'የዲያስፖራ ኢንቨስትመንት ፎረም' ላይ የተገኙ እንደ ፀሀይፅድቅ ቤተማርያም ያሉ ሌሎች መዋዕለ ነዋያቸውን በኢትዮጵያ ፈሰስ ማድረግ የሚፈልጉ ባለሀብቶችም በመሬት አስተዳደር እና በሙስና ላይ ያላቸውን ስጋት እና ጥያቄዎች በመድረኩ አንፀባርቀዋል። 

ኢትዮጵያ የመሬት ሀብትን ለማስተዳደር ያወጣችው አዋጅ ቁጥር 721/ 2004 ‘የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ' የወጣው አዋጅ አንዱ ነው። በእዚህ አዋጅ መሰረታዊ የሊዝ ድንጋጌዎች ስር የተጠቀሰው “ማንኛውም ክልል ወይም የከተማ አስተዳደር በዚህ አዋጅ ከተደነገገው ውጪ የከተማ መሬትን መፍቀድ ወይም ማስተላለፍ አይችልም” ሲል ይደነግጋል። በተጨማሪም “የከተማ ቦታ አሰጣጥ ስርዓቱ የህዝቡንና የከተሞችን ጥቅም በቀዳሚነት በማስከበር የከተማ ልማትን በማፋጠንና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የሀገሪቱን ልማት ቀጣይነት የሚያረጋግጥ መሆን አለበት” የሚል ድንጋጌን አካቷል።

አዋጁ ላይ እንደሚጠቅሰው ከሆነ በሊዝ የተያዘ መሬትም ቢሆን “የክልሎች ካቢኔዎች ይህ አዋጅ ለተወሰነ ጊዜ ተፈጻሚ ሳይሆን እንዲቆይ የሚደረግባቸውን ከተሞች ሊወስኑ ይችላሉ” ይላል።

የምጣኔ ሀብት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት አማካሪና ባለሙያ የሆኑት አማንይሁን ረዳ፤ “መሬትን ለማልማትና ለማግኘት ውስብስብ እና ለሙስና የተጋለጠ ያደረገው መንግስት ብቸኛው የመሬት አቅራቢ መሆኑ ነው” ብለው “መሬት በማንኛውም ሁኔታ እንደቁስ ሊሸጥና ሊለወጥ ይገባዋል” ብለዋል።

በመሬት ዘርፍ “የተሳሳተ ፖሊሲ፣ ደካማ አመራር እንዲሁም ከህዝብ ደህንነት ስልጣንን ማስቀደም” ዋነኛ የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን የንግድና ኢንቨስትመንት አማካሪው ያስረዳሉ።

በተጨማሪም “ኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለው ፖለቲካዊ ስሪት ለመሬትም ጭምር ማንነት የሰጠ ነው። በእኔ መሬት አንተ አትሰራም የሚባሉና በረጅም ጊዜ ልፋት እና ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ የተደረገበት የመሬት ሀብት የእገሌ ብሔር መሬት ነው እየትባሉ ለመልቀቅና ምንም ላልለፉ ሰዎች የመተላለፍ አዝማሚያ መኖሩ ለባለሀብቶች ስጋት ሆኗል” ሲሉ አማንይሁን ረዳ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

ግለሰቦች በእጃቸው የሚገኝ መሬትን ሀብት ካላቸው ሰዎች ጋር በጋራ ማልማት እንዲችሉ እንዲሁም የመሬት ዋጋን መተመን በህገ መንግስትም የተፈቀዱ አለመሆናቸውን ባለሙያው ይገልፃሉ።

ለመሬት በአግባቡ አለመተዳደር ሌላኛው ምክኒያት “መሬት የፖለቲካ መሳሪያ ሆኖ ከማገልገል በስተቀር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ዋጋ አልተሰጠውም” የሚሉት አማንይሁን ረዳ፤ “በተለይ የሀገሪቱ 70 በመቶ የሚሆን ዜጋ በገጠር አካባቢ የሚኖር መሆኑ የለማ መሬትን እንዲሁም የግብርና ግብዓቶችን እከለክላለሁ በሚል ማስፈራሪያ የሚታሰሩ ከመሆናቸውም ባለፈ በምርጫ ወቅት ቀብድ መያዣ ሲሆን ተመልክተናል” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

መንግስት ወይም ዜጎቹን ማስቀደም አልያም ከስልጣኑ መምረጥ ይገባዋል የሚሉት የኢንቨስትመንት አማካሪዉ፤ “ሀገርን በእዚህ ሁኔታ ከድኅነት ማውጣት አይቻልም፣ የመሬት ምርታማነትን በተገቢዉ ልክ መጠቀም አይቻልም፣ በተጨማሪም ግብርናን ማሳደግና ባለሀብቶችን መሳብና ማሳመን አይቻልም” ብለዋል።

ሀገር በድኅነት ውስጥ የመቀጠሏ ዋነኛው ምክኒያት ያሉትን ሀብቶች በአግባቡ አለመጠቀም ነው። ኢትዮጵያ ያላትን መሬት እና ከዓመት ዓመት የሚፈሱ ወንዞችን ተጠቅማ በሙሉ አቅም ማምረት መጀመር የግድ እንደሚላት ባለሙያው ገልፀዋል።

እንደ አማንይሁን ረዳ ማብራሪያ “ባለሀብቶች ለአስርም ለመቶም ለሺዎችም የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል ገንዘብና አቅም ይዘው መጥተው የመሬት አሰራር ብልሹ ሲሆን አንድ ፎቅ ገንብቶ ማከራየትን ይመርጣል” በተጨማሪም የመሬት አስተዳደር ችግር መኖር ኢትዮጵያን ምርታማነት እንዳይኖር፣ ለኑሮ ውድነት እንዲሁም ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ዳርጓል ይሏሉ።

እንደ ባለሙያው ገለፃ “የፖለቲካ ስርዓቱ በፈጠረው ችግር የተነሳ መሬት ብሔር አለው። የፀጥታ አካላትም ሳይቀሩ የብሔር ሽፋን ይላበሳሉ። በእዚህም የተነሳ ብዙ ባለሀብቶች የለፉበት ንብረት ዋጋ ሳይሰጠው ከክልላችን ውጡ፣ ለወጣቶች አካፍሉ የመሳሰሉ ወሬዎች የሚመነጩት ከእዛ ነው”

እንደዚህ አይነት አሰራሮች ባለሀብቱን ቢወረስስ፣ ቢቀማስ፣ ቢጎዳ እንዴት እካሳለሁ የሚሉ ስጋቶች ውስጥ ይከታሉ።

መፍትሔዎቹ ምንድን ናቸው?

የንግድና ኢንቨስትመንት አማካሪው አማንይሁን ረዳ የሚያስቀምጡት የመጀመሪያው መፍትሔ፤ ፖለቲካችን ከዘር አስተሳሰብ መፅዳት ይገባዋል።

ሌላኛው ደግሞ መንግስት ብቸኛው የመሬት አቅራቢ መሆን የለበትም። በተጨማሪም መሬት የፖለቲካ መጠቀሚያ መሳሪያነቱ መቅረት አለበት። “መሬት ወደ ስልጣን መወጣጫ እና ስልጣን ላይ የመቆያ አማራጭ መሆን የለበትም” ሲሉ ባለሙያው ያክላሉ።

መንግስት የመሬት ባለቤትነት መብትን ማክበር እንዲሁም በቡድን መብት ስም የግለሰቦች መብት የማይጨፈለቅበት ስርዓት መፍጠር የግድ ይላል።

በተጨማሪም መንግስት 21ኛው ክፍለ ዘመንን የሚመጥን የኢኮኖሚ ስርዓት ለመፍጠር መወሰን አለበት። በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ የምጣኔ ሀብት ስርዓት ያላቸው ሀገራትም ሆኑ ግለሰብ ባለሀብቶች የፋይናንስ ምንጫቸው ዲጂታል ኢኮኖሚ ሆኗል።

“መሬት በዋነኛነት የኢኮኖሚ መሰረት የነበረበት ጊዜ 18ተኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነው በምሳሌነተ የምናየው የቅኝ ግዛት ስርዐት ለመሬት ከነበረ ፍላጎት የመነጨ ነበር” ይላሉ ባለሙያው።

በቅኝ ግዛት ያልተገዛችው ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር ኢትዮጵያ ደግሞ አሁንም የመሬት ሀብቷን በአግባቡ አለመጠቀሟ ለድኅነቷ መንሳኤ ሆኗት ለዘመናት ቀጥሏል ሲሉ አማንይሁን ረዳ ይገልፃሉ።

አስተያየት