በ5መቶ 30 ካ.ሜ. ላይ ያረፈው፣ 17.5 ሜትር ርዝማኔ ያለው፣ ከመሬት በታች 4.5 ሜትር የተቆፈረው፣ ከ45.5 ሚልዮን ብር በላይ የወጣበት የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ሐውልት በዛሬው ዕለት ጥር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ተመርቋል። በሐዲያ ዞን ሆሳህና ከተማ የተገነባው ሃውልቱ ከሆሳህና ከተማ መናኸሪያ ወደ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በሚወስደው ዋና መንገድ መገንጠያ ላይ በሚገኘው አደባባይ ሲመረቅ በርካታ ሰዎች ተገኝተዋል። የኢፌዲሪ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናንት ጀነራል ይልማ መርዳሳ፣ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳውን ጨምሮ የኮሎኔል በዛብህ ቤተሰቦች፣ የቀድሞ የሥራ ባልደረቦች፣ አድናቂዎች ተገኝተዋል። በተጨማሪም የዞን፣ የክልልና የፌደራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዞኑ እና የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች የምርቃት ሥነ-ስርአቱ ተሳታፊ ሆነዋል።
ከሀዲያ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ዕንደሚያሳው የኮኖሎኔል በዛብህ ሐውልት ተፈጥሯዊ አደጋን መቋቋም እንዲችል ታስቦ ንፋስ ማስተላለፊያ ቀዳዳዎች ተሰርተውለታል።አስር ወራት የፈጀውን የሐውልቱን ግንባታ ወጪ የሸፈነው የሐዲያ ልማት ማኅበር (ሀልማ) ሲሆን የግንባታ ሥራው በጌታቸው ኮንስትራክሽን ተቋራጭ ተከናውኗል።
ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ማነው?
“ፎጊ” በሚል የበረራ ኮድ ስሙ፣ “የሰማዩ ጀግና” በሚል ቅጥያ ስሙ የሚታወቀው ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ የቤተሰቡ ሦስተኛ ልጅ ነው። ሐምሌ 13 ቀን 1943 ዓ.ም. ከአባቱ አቶ ጴጥሮስ ሎዳሞ እና ከእናቱ ከወይዘሮ ሸዋዬ አብርሃም በአሁኑ አጠራር ደቡብ ክልል ሀዲያ ዞን ምስራቅ ባዳዋቾ ወረዳ አንደኛ አምቡርሴ ቀበሌ ተወለደ።
ከልጅነቱ ጀምሮ በመልካም ፀባዩ የሚታወቅ፣ ደፋር፣ ቁጡ ግን ደግሞ ይቅር ባይና ተግባቢ ባህሪይ ነበረው። በትምህርት አቀባበሉ ንቁና ጎበዝ እንደነበር ይነገርለታል። ከልጅነቱ ጀምሮ ወታደር የመሆን ዝንባሌም ነበረው። እስከ አስራ አንደኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ያለውን ድረስ ትምህርቱን በሆሳዕና ከተማ በቀድሞው አጠራር ራስ አባተ ቦያለው ተከታትሏል፡፡ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳለ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድሮ የተሰጠውን ምዘና በብቃት በመወጣት ጥር 26 ቀን 1961 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር ኃይልን እንደተቀላቀሉ ስለ ኮሎኔሉ የተጻፈው መረጃ ያመለክታል።
በወጣትነት እድሜው የኢትዮጵያ አየር ኃይልን የተቀላቀለው ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ የተቋሙን ሥልጠናዎች በብቃት መከታተል ችሏል። በወቅቱ ከተከታተሏቸው የሥልጠና ዘርፎች መካከል መሠረታዊ የውትድርና ኮርስ፣ መሠረታዊ የበረራ ኮርስ፣ የመጀመሪያ ደረጃ የበረራ ሥልጠና ኮርስ፣ የአውሮፕላን አብራሪነት ዲፕሎማ እንዲሁም ከፍተኛ የተዋጊ አውሮፕላን ሥልጠና ኮርስ በሀገር ውስጥ ሰልጥኗል። ከሀገር ውጭ በሀገረ አሜሪካ እና በቀድሞ ሶቭየት ሕብረት የሚሰጠውን የበረራ ትምህርት ስልጠና ተከታትሎ አጠናቋል።
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት በወሰዳቸው የሥልጠና ኮርሶች ባገኘው ዕውቀት እና ክህሎት እንዲሁም ባዳበረው ልምድ በአየር ኃይል ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ለረዥም ጊዜ ተዛዋውሮ አገልግሏል።
ኮሎኔል በዛብህ አገልግሎት ከሰጠባቸው የተለያዩ ቦታዎች ውስጥ በተዋጊ አውሮፕላን አብራሪነት፣ በበረራ አስተማሪነት፣ በስኳድሮን ምክትል አዛዥነት፣ በተዋጊ ስኳድሮን የበረራ አስተማሪነት፣ በበረራ ትምህርት ቤት የትምህርት መኮንን በመሆን (በተደራብነት)፣ በበረራ ትምህርት ቤት አዛዥነት በተደራቢ፣ በሰሜን አየር ምድብ ጥገና አዛዥነት፣ በኤል-39 አውሮፕላን በረራ አስተማሪነት፣ በበረራ ትምህርት ቤት ምክትል አዛዥነት፣ በበረራ ማሰልጠኛ ት/ቤት የሥርዓተ ትምህርት ደረጃ እና ምዘና ኃላፊነት፣ በበረራ ት/ቤት የዕቅድና ስርዓተ ትምህርት ኃላፊነት፣ በኤል-39 አውሮፕላን ስኳድሮን አዛዥነት እንዲሁም በምስራቅ አየር ምድብ አዛዥ ተደራቢ በመሆን የሰራባቸው ቦታዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሠራዊት አባል ሆኖ በተሰማራባቸው አውደ ውጊያ ግንባሮች ከፍተኛ ጀብድ እየፈፀመ የኖረ የሀገር ኩራት የሆነ ጀግና ነው። ጀግናው ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ከወይዘሮ ወይንሸት ኃይሌ ጋር ትዳር መሥርተው ሦስት ወንድና ሁለት ሴት በድምሩ አምስት ልጆችን አፍርተዋል።
በ1943 ዓ.ም. የተወለደው ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያን ዘንድ እንዲታወስ ያደረገው እና ታላቅ ገድል ከፈፀመባቸው የውጊያ ውሎዎቹ መሃል የሐምሌ 27 ቀን 1969 ዓ.ም. ሕብረቱ ቀዳሚ ነው። በዚያ ወቅት ትምክህተኛው የዚያድባሬ መንግስት በምስራቅ ኢትዮጵያ ግዙፍ ወታደራዊ ወረራ ፈፅሞ ነበር። ይህንን ወረራ ለመመከት ከተሰማሩት የአየር ኃይል (አሜሪካ ሰራሽ ኤፍ 5 ኢ) ተዋጊ ጀቶች መሃል አንዱን የያዘው እሱ ነው። እናም በኦጋዴን ሐረዋ፣ አይሻ፣ በእነኖሜጢ እና በሌሎችም ቦታዎች የሮኬት ናዳ በማውረድ ወራሪውን የሶማሊያ ጦር ባለበት እንዲገታ ከማድረግ ባሻገር፣ 8 የጠላት ታንኮችን ከእነ ምድብተኛው እንዳወደመ ከፈጸማቸው ገድሎች መካከል ይጠቀስለታል፡፡
ጥቅምት 7 ቀን 1970 የኢትዮጵያ ሠራዊት በጅጅጋ ካራማራ ላይ ከፍተኛ ትንቅንቅ ላይ ይገኛል። ያኔ እሱ ከላይ ከሰማይ በሚያወረደው ቦንብ የሶማሊያን ወራሪ ጦር ብትንትኑን ማውጣት ተያያዘ። በዚህ ጊዜ ከጠላት ወገን በተኮሰ አየር መቃወሚያ የሚቀዝፈው ኤፍ 5 ኢ-ተዋጊ ጀት ተመታ። ይኼኔ እሱ በዥንጥላ ወርዶ ህይወቱን ማትረፍ ነበረበት። ነገር ግን የሚያበረውንም ጀት ጭምር እንጂ የራሱን ህይወት ብቻ ማትረፍ አልፈቀደም። እናም የሚያበረውን ጀት በቆራጥነት እየቀዘፈ ወደ ደብረዘይት አየር ማረፊያ ገስግሶ በሰላም አረፈ። የተመታውም ጀት ተጠግኖ እንደገና ለግዳጅ ተሰማራ።
ሐምሌ 30 ቀን 1969 ዓ.ም. በነገሌ ቦረና ግንባር የተሰማራውን የሶማሊያ ጦር የቦንብ ናዳ በማውረድ ጠላትን ብትንትኑን ማውጣቱን ቀጠለ። ይህ ብቻ አይደለም፤ ሁለት የሶማሊያ ጦር ጀቶችን በአየር ላይ አጋይቶ ጣለ። የሚገርመው አንዱን የሶማሊያ ጦር ጀት ያጋየው ሶማሊያ ግዛት ውስጥ ዘልቆ ገብቶ መሆኑ ነው።
ጥቅምት ወር 1970 ዓ.ም. የሶማሊያ ጦር ጀቶች ድሬደዋ ከተማ ላይ ጥቃት ፈፀሙ። ይኼኔ ለጥቃቱ የአፀፋ መልስ እንዲሰጡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊዎች ታዘዙ። ከታዘዙት ተዋጊዎች መሃከል አንዱ እሱ ነበር። እናም ጀቱን እየቀዘፈ የአየር ላይ ትርዒት ጭምር በማሳየት ጀግናው ገድሉን ቀጠለ። እናም የሶማሊያን ሚግ 21 ተዋጊ ጀት ከነአብራሪው በአየር ላይ አጋይቶ በሰላም ወደ ደብረዘይት ተመለሰ።
ሕዳር 3 ቀን 1970 ዓ.ም. የሶማሊያ ተዋጊ አውሮፕላኖች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ጥቃት ፈጽመው ተመለሱ። ይኼኔ ሁለት የኢትዮጵያ ተዋጊዎች (ሻለቃ በዛብህ ጴጥሮስ እና ኮሎኔል ለገሰ ተፈራ) ተከትለዋቸው ገሰገሱ እስከ ሞቃዲሾ ድረስ። የሶማሊያ አውሮፕላኖች ሞቃድሾ አየር ማረፊያ ደርሰው ለማረፍ ዝቅ ሲሉ፤ ጀግኖቹ ሻለቃ በዛብህና ኮሎኔል ለገሰ ተፈራ እዚያው እንዳጋዩአቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከዚህ ሁሉ ድል በኋላ ሚያዝያ ወር 1970 ጀምሮ ኤርትራ ወደሚገኘው 2ኛው አየር ምድብ እንዲዛወር ተደረገ። ሻለቃ በዛብህ ጴጥሮስ ህዳር 21 ቀን 1972 ዓ.ም. ለንባብ በበቃው “ታጠቅ” የተሰኘ የሰራዊቱ ጋዜጣ ላይ ከሰጠው ቃለ-ምልልስ የሚከተለውን መጥቀስ ብሏል።
"እኛ ብንሞት ሌላ ሰው ይተካናል፤ መተኪያ የሌላት ኢትዮጵያ ከሞተች ግን ተተኪው ትውልድ ስለሚሞት ዋጋ አይኖረውም። የሀገርን ሉአላዊነት በአስተማማኝነት መጠበቅ ቆራጥነት እና ልበ ሙሉነት ይጠይቃል። እኛ በሕይወት ቆመን ዕያየን ጠላት አንዲት ስንዝር መሬት ቆርሶ መሄድ ቀርቶ በአንድ እግሩ እንኳ ሊቆምባት ዓይችልም። ከሀገር ወዲያ ሌላ መኖሪያ ዋሻ ስለሌለ በሃገር እና በነፃነት ጉዳይ ምንም ቀልድ ሊኖር አይችልም”
ከሶማልያ ወረራ በኋላ ወደ ኤርትራ ዘምቶ እስከ 1977 ድረስ ግዳጁን በአግባቡ የተወጣ አርበኛ ነው። በ1977 ዓ.ም. ግን ከሻዕቢያ ጋር እየተዋጋ ሳለ አውሮፕላኑ ተመታ። ወደ ተነሳበት ቦታ መመለስ አልቻለም፤ በሻዕቢያ እጅ ወደቀ። እስረኛ ሆነ። በ1983 ዓ.ም. ከእስር ተለቆ ከቤተሰቡ ጋ መቀላቀልም ችሎ ነበር።
ከ7 ዓመት በኋላ በ1990 ዓ.ም. የኢህአዴግ ወዳጅ የነበረው ሻዕቢያ ጠላት ሆኖ መምጣቱ የ3 ወንዶች እና የ2 ሴቶች አባት ለሆነው ኮሎኔል በዛብህ ቁጣን መቀስቀሱ እና ሻዕቢያን ለመደምሰስ ዳግም መዝመቱ የታሪክ ማህደሩ ያሳያል።
ግንቦት 5 ቀን 1990 ዓ.ም. ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ወደኤርትራ ምድር ዘልቀው ከገቡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊዎች አንዱ ነበር። የሚያበረውን አውሮፕላን ዝቅ፤… እጅግ ዝቅ… አድርጎ የሻዕቢያን ጦር “አፈር ድሜ እያስጋጠ›› ሳለ ተመታ፤ እንደገና በሻዕቢያ እጅ ወደቀ። ተማረከ። የሻዕቢያ እስረኛ ሆነ። በሻዕቢያ እጅ የወደቀው ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ እስካሁን በሕይወት ይኑር አይኑር በይፋ የታወቀ ወይም የተነገረ ነገር ባይኖርም። አቦይ ስብሃት ለ“አውራምባ ታይምስ” ድረገፅ ኦክቶበር 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ቃለ ምልልስ ኮሎኔሉ ሳይገደል እንዳልቀረ ተናግረዋል።