በጥር ወር አጋማሽ ምሽት በድሬዳዋ ራስ ሆቴል የተዘጋጀው እራት ዓላማ ብዙዎችን ያስደሰተ ነበር። የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር አመራሮችን፣ የድሬደዋ ተወላጆችን እና ወዳጆችን በአንድ መአድ ያሰባሰበው ድግስ ዓላማ በከተማዋ በሚገኙ የመንግሥት ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት ማከናወኛ ማሽን ለመግዛት የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰብ ነው።
ወደ 500 ሺህ የሚገመት ህዝብ የሚኖርባት ድሬዳዋ ያላት የኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) ማከናወኛ ማሽን በቂ እንዲሆን፣ ታማሚዎቿ ከእንግልት እንዲድኑ የወጠነው ግብዣ ከ4 ሚልዮን ብር በላይ ማሰባሰብ ችሏል።
“በድሬዳዋ ከተማ በሚገኙ የግልም ሆነ የመንግሥት ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት የሚያስፈልጋቸውን ህመምተኞች የሚረዳው ማሽን አንድ ብቻ መሆኑ በርካቶችን ለእንግልት ዳርጓል” የሚሉት የሐሳቡ ጠንሳሾች “ድሬ ትጣራለች” በሚል መሪ ቃል የእራት ግብዣ ሰአናዱ። የሐሳቡ ባለቤቶች የአንድ እራት ዋጋ 10ሺህ ብር እንዲሆን ከወሰኑ በኋላ መኅበራዊ ሚድያን ተጠቅመው ውጥናቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዟቸውን እንግዶች ጋበዙ።
ሐሳቡ እውን እንዲሆን የማኅበራዊ ሚድያ ወዳጆቻቸውን እና ተከታዮቻቸውን ከቀሰቀሱት ግለሰቦች መካከል አቶ ይትባረክ አስፋው ይገኝበታል። አቶ ይትባረክ የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን የመግዛቱ ሐሳብ ከአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሀር መሆኑን ነግሮናል። “ሐሳቡ በከንቲባው ቢነሳም በሐገር ውስጥ እና በውጭ ሐገራት የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ደግሞ በማስተዋወቅና ግብዣው ላይ በመገኘት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክተዋል” ብሎናል።
ከማኅበራዊ ሚድያ ንቅናቄው በተጨማሪ በሁሉም የድሬዳዋ ከተማ መንደሮች እየተዘዋወሩ ቅስቀሳ ያካሄዱና ማስታወቂያ የሰሩ ወጣቶችም ከፍ ያለ ሚና ስለመጫወታቸው ነግሮናል።
ከአስተባባሪዎቹ መካከል አንዱ የሆነው አቶ ይትባረክ አንዷለም በማስተባበር ሂደቱ ወቅት ከድሬደዋ አስተዳደር የዲያስፖራ ማኅበር ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ አቤል አሸብር ጋር በቅንጅት ስለመስራታቸው ነግሮናል።
በእራት ግብዣው ላይ 4 ሚልዮን 300 ሺህ ብር ገደማ መሰብሰብ እንደተቻለና ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ጎፈንድሚ በመክፈት በዚያም የገቢ ማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ ይትባረክ ተናግረዋል።
500 ሺህ የሚጠጋ ነዋሪ የሚገኙባት የድሬደዋ ከተማ የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን በአንድ የማሪያም ወርቅ በሚባል የግል የህክምና ተቋም ብቻ መገኘቱ ታማሚዎችን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደሚከት እሙን ነው። በከተማዋ ውስጥ ከአስተዳደሩ አልፎ ለአጎራባች ክልሎችና ከጎረቤት ሀገር ለሚመጡ ተገልጋዮች ጭምር አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት (ዲያለሲስ) አገልግሎት መስጫ ማሽን አለመኖሩ ሌላ ጥያቄ የሚፈጥር ጉዳይ ነው።
የድሬደዋ አስተዳደር ድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙና ኢብራሂም
“የድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል እንደ ሪፈራልነቱ የዲያሊሲስ አገልግሎት መስጫ ማሽን ሊኖረው ይገባ ነበር። በተለይ ከውስጥ ደዌ ህክምና ማሻሻል ጋር ተያይዞ በጣም አስፈላጊ አገልግሎት ነው። ሆኖም ግን በተለያዩ ችግሮች አገልግሎቱን አልጀመርንም። አገልግሎቱን አለመጀመራችን በሆስፒታላችንም በኩል ይሁን በማኅበረሰባችን ወይም በታካሚዎች በኩል በጣም ብዙ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን አሳድሯል” ይላሉ።
ወ/ሮ ሙና የችግሩን አሳሳቢነት ሲያስረዱ “እንደ ሆስፒታል ስናየው አንድ ታካሚ ሊገለገል መጥቶ የዳያለሲሱ ማሽን እኛ ጋር ባለመኖሩ አገልግሎቱን ሳያገኝ በሆስፒታሉ አምቡላንስ አገልግሎቱን ወደሚያገኙበት ቦታ ማዟዟሩ፤ ዲያለሲሳቸውን ሲጨርሱ ደሞ ከነበሩበት ቦታ ወደ ሆስፒታሉ መመለሱ ብዙ ብክነትን የሚያስከትል ነው። ከታካሚው አንፃር ስናየው ደግሞ ታማሚውም ይሁን አስታማሚዎች ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸዋል። በሆስፒታላችን ክትትል እየተደረገላቸው አራቴና አምስቴ የሚመላለሱ ህሙማን አሉ። ከእንግልቱ ባሻገር ግን በዋናነት ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ የሚያስገባ ጉዳይ ነው”
ወ/ሮ ሙና በድልጮራ ሆስፒታል ለሚታከሙ የኩላሊት ህመምተኞች የሚደረገው አልጋ መስጠትና አስተኝቶ ክትትል ማድረግ እንዲሁም የዲያሊሲስ አገልግሎት ወደ ግል ሆስፒታል ሄደው አግልግሎቱን እንዲያገኙ ማመቻቸት ብቻ እንደሆነ ገልፀዋል።
በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ያገኘነው አቶ አዲሱ የ35 ዓመት ወጣት ነው። የአንድ ልጅ አባት የሆነው አዲሱ ሁለቱም ኩላሊቶቹ መስራት አቋርጠዋል። ወንድሟን በማስታመም ላይ የነበረችው እህቱ እታለማሁ አዲሱ ከእንግልቱ በላይ እራስ ምታት የሆነባትን ስታስረዳ
“ድል ጮራ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጥ ማሽን አለመኖሩ ስቃያችንን አብዝቶታል። እኔ ከነበርኩበት ወሎ ወንድሜን ለማስታመም ስመጣ ጓደኞቹ በዚህም በዚያም ብለው ገንዘብ በማሰባሰብ የኩላሊት እጥበቱን ባያስጀምሩት በህይወት ላይኖር እንደሚችል ትናገራለች። ክትትሉና ተያያዥ ህክምናዎች ድል ጮራ የሚደረግለት ሲሆን ትልቁ ችግር ግን መድኃኒቶቹን ሳይጨምር በሳምንት ለሁለት ቀናት 2ሺህ 5መቶ ብር እየተከፈለ በግል ሆስፒታል የሚደረገው የኩላሊት እጥበት ነው። ለእጥበቱ የሚያስፈልገው ወጪ ሲጨመር ደግሞ ዋጋው እስከ 4ሺህ ብር ድረስ ይጠጋል። በዚያ ላይ በሳምንት ሦስቴና ሁለቴ መታጠብ ይኖርበታል ስለዚህም በወር ለመታጠብ እስከ 48ሺህ ብር ድረስ ያስፈልጋል” ስትል ስላለው ሁኔታ አስረድታለች።
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምልም በዛብህ እስካሁን ድረስ በአስተዳደሩ የኩላሊት እጥበት መስጫ ማሽን በመንግስት የጤና ተቋም ሊኖር ያልቻለበትን ምክንያት ሲያብራሩ፣ “ቴክኖሎጂው በራሱ አዲስ በመሆኑና በዋጋ ደረጃ ውድ በመሆኑ፤ የአስተዳደሩ የገቢ መጠንም ይህን ያክል እንደልብ እንዲህ ያሉ ውድ ማሽኖችን እንድንገዛ የሚያበረታታ አለመሆኑ አንዱ ምክኒያት ነው። ሌላው እንደ ድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ትኩረት አድርገን ሥንሰራ የነበረው በተላላፊ በሽታዎች ላይ በመሆኑና እንደ ኩላሊት ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከቱና በሕብረተሰቡ ዘንድ ዕየታዩ የመጡ በመሆናቸው ነው።
ይህን የኩላሊት እጥበቱን ለማካሄድ ቀድሞ ህሙማኑ አዲስ አበባ ይሄዱ የነበረ ሲሆን እዚህ ድሬዳዋም ማሽኑን የግል ሆስፒታል ካስመጣ በኋላ በውድ ዋጋ አገልግሎቱን ቢያገኙም ያለው እንግልትና ዋጋው ህሙማኑን በልመና እስከመሰማራት በማድረሱ ለቢሯችን ይህ ትልቅ እራስ ምታት ነው። ታዲያ ለዚህ መፍትሄ ይሆናል በማለት አንዳንድ እንቅሳቀሴዎችን ጀምረናል ከነዚህም መካከል ይህንን ማሽን ለማግኘት ውጭ ሀገር ካሉ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ጋር በጋራ እየተሠራ ነው” ብለዋል።
“እ.ኤ.አ በ2017 በዓለም አቀፍ ደረጃ 697 ሚሊዮን (ሁሉም ዓይነት) የኩላሊት ህመምተኞች ተመዝግበዋል። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች የበሽታዉን ስርጭት 9.1% ያደርገዋል” ሲሉ የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል ባለሞያ አቶ አቤል ሽፈራው ገልፀዋል። እንደ አቶ አቤል ገለፃ እ.ኤ.አ በ2017 በአለም አቀፍ ደረጃ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች ስር በሰደደ የኩላሊት በሽታ ሞተዋል። በ2018 በወጣው አለም አቀፍ የጤና መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ 6426 ሰዎች ስር በሰደደ የኩላሊት ህመም ህይወታቸውን አጥተዋል።ይህም በጠቅላላው በሀገሪቱ ከሚከሰተው ሞት 1.5% ነው። በድሬደዋ አስተዳደር ምንም እነኳን የተሰራ ጥናት ባይኖርም ከሆስፒታሎች የሚገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከ6 መቶ በላይ ሰዎች በዓመት የኩላሊት እጥበት እንደሚያስፈልጋቸው አቶ አቤል ተናግረዋል።
የኩለሊት እጥበት በኩላሊት መድከም ምክንያት ሰውነት ውስጥ የሚጠራቀሙ መወገድ ያለባቸውን ቆሻሻ ምርቶች እና ከመጠን በላይ የሆን ውሀ ከሰውነት በሰው ሰራሽ መንገድ የሚያስወግድ ሂደት ነው። ለመጨረሻ ደረጃ የኩላሊት ህመም ወይም ለአጣዳፊ የኩላሊት በሽታ ተጠቂዎች የሚጠቅም የህይወት አድን ዘዴ ነው።