ከ436ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት አንድ የፌስቡክ ገጽ በሕዳር 23 ፤ 2014 ዓ.ም “1287 የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ሀይል አባላት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) ተቀላቀሉ።” በማለት አንድ ምስልን በማያያዝ አጋርቶ ነበር። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ልጥፉ ከ300 ጊዜ በላይ የተጋራ ሲሆን ከ1000 በላይ ግብረ መልስን ማግኘት ችሏል። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ምስሉን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ወታደራዊ ክንፍ የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በሚያዝያ 23 ፤ 2013 ዓ.ም እራሱን ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ማግለሉን ያሳወቀ ሲሆን በሃገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ‘ሸኔ’ አሸባሪ ድርጅት በመባል ተፈርጇል። በመንግስት ‘ሸኔ’ እየተባለ የሚታወቅ ራሱን ደግሞ ‘የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት’ ብሎ የሚጠራ ወታደራዊ ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ባሉ ቦታዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲሁም ብሄርን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዳደረሰ የሚያሳዩ የተለያዩ ክሶች ይቀርቡበታል። ወታደራዊ ቡድኑ በአሁኑ ሰዓት ከፌደራሉ መንግስት ጋር ጦርነትን በማድረግ ላይ ከሚገኘው ህወሓት ጋር ከህዳር ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ በጋራ ለመስራት መስማማቱን አሳውቋል። የክልሉ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ “የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር የጸጥታ ሃይሉን በአዲስ መልክ እያደራጀ እንደሚገኝ አሳውቀዋል።”
በፌደራል መንግስቱ ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተጨማሪ የጸጥታ ሃይሉ በክልሉ ዞን ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ለመቆጣጠር እንዲያግዛቸው በሚል ከህዳር 6 ፤ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የሰዓት እላፊ ታውጇል። በኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይሎች እና በ’ኦነግ ሸኔ’ መካከል ያለው ግጭት እየቀጠለ ቢሆንም አንዳንድ የክልል ልዩ ፖሊስ ሃይል አባላቶች ወደ ‘ሸኔ’ ጦር ተቀላቅለዋል የሚሉ ወሬዎች ይሰማሉ።
የኦነግ ‘ሸኔ’ ጦር ቃል አቀባይ የሆኑት ኦዳ ተርቢ በጥቅምት 25 ፤ 2014 ዓ.ም “በዛሬው ዕለት 1165 የሚሆኑ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይል አባላት መንግስትን ክደው የ‘ሸኔ’ን ጦር የተቀላቀሉ ሲሆን ከነሱ መካከል 400 የሚሆኑት ከለገጣፎ እና አካባቢው የመጡ ናቸው። ጦራችን በሁሉም አቅጣጫ እየገፋ በመጠጋት ላይ ሲሆን ይህን ጨቋኝ እና አምባገነን ስርዓት ማብቂያው ጊዜ ቅርብ ነው” በማለት አጋርቶ የነበረ ሲሆን ፣ ይህ የፌስቡክ ልጥፍም በዚህ ሁኔታ ላይ መሰረት አድርጎ የተጋራ ነው። ይሁን እንጂ በየካቲት 29 ፤ 2012 ዓ.ም ተመሳሳይ ምስል በአንድ የትዊተር አካውንት ላይ “አብይ አህመድ 20 ሚልዮን የሚደርሱ ነፍጠኛ እና ጎበናዎችን ቢያሰልፍ እንኳን አያድኑትም” በሚል ተጋርቶ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ምስሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለ30ኛ ዙር ያስመረቃቸውን የልዩ ፖሊስ ሃይል አባላት የምርቃት ስነ-ስርዓት ቪዲዮ ላይ የተወሰደ ምስል ነው። አንዳንድ የክልሉ ልዩ ፖሊስ አባላት ወደ ‘ኦነግ ሸኔ’ ተቀላቅለዋል የሚል ያልተረጋገጡ ወሬዎች ይኑሩ እንጂ ምስሉ የኦነግ ሸኔን ጦር ለመቀላቀል ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይል የተመለመሉ ወታደሮችን አያሳይም። ስለዚህ ሀቅቼክ የፌስቡክ ልጥፉን አጣርቶ ሀሰት ብሎታል።