ማኅበራዊ ሚድያን ትርጉም ላላቸው ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች የሚያውሉ ኢትዮጵያዊያን ተጠቃሚዎች ቁጥር እያሻቀበ ስለመምጣቱ ብዙዎች ይስማማሉ። እንደ ፌስቡክ እና ትዊተር ያሉ ማኅበራዊ ሚድያዎች በእለት ተእለት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ብቻ ሳይሆን በሐሰት ዜናዎች ስርጭት ከፍ ያለ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ እሙን ነው። የወጣት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍተኛ የሆነበት የማኅበራዊ ሚድያው መድረክ አነሳስቷቸው በጎ ተጽእኖ ለማሳደር የበቁት ቁጥር የመጥፎዎቹን ያህል ባይሆንም ጨርሶ የሉም የሚባል ደረጃ ላይ አይገኙም።
በዚህ ጽሑፍ መኖርያቸው ባህርዳር ከተማ የሆነ፣ ማኅበራዊ ሚድያውን ለበጎ ዓለማ በመጠቀም ተጽእኖ ማሳደር የቻሉ ወጣቶችን እንቅስቃሴ እንመለከታለን።
ማኅበራዊ ሚድያውን ተጠቅመው ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ከተወጡት መካከል እንዳልካቸው ጥላሁን አንዱ ነው። ማኅበረሰቡን በማንቃትና በማስተባበር አዎንታዊ እንቅስቃሴዎች ካሏቸው መካከል አንዱ የሆነው እንዳልካቸው የነቃ ማኅበራዊ ተሳትፎ በማድረግ ይታወቃል። ሰናይ ተግባሩን ከደገፉ ሌሎች ጓደኞቹ እና የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮቹ ጋር በመሆን በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እና በሌሎችም ግጭቶች ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ደግፏል።
እንደ ወጣት እንዳልካቻው ገለፃ ማኅበራዊ ሚዲያ አንድ ዓይነት ፍላጎት ያላቸውን የሕበረተሰብ ክፍሎች በአንድ ላይ ለማግኘት ከፍ ያለ እድል ይሰጣል። ይህንን ስብስብ ለጥሩ ዓላማ መጠቀም ደግሞ የተጠቃሚው ኃላፊነት ነው።
"ለመተከል ተፈናቃዮች ከአንድ መቶ ሃምሳ ኩንታል በላይ የዳቦ ዱቄት፣ ፓስታ እና መኮረኒ፣ የህፃናት ምግቦችን፣ ለሴቶች እና ለህጻናት የሚሆኑ የንዕህና መጠበቂያዎች፣ የህፃናትና አዋቂዎች አልባሳትና ጫማዎች፣ ምግብ ለማብሰል እና ለመመገብ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች በጥቅሉ ግምታቸው ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ቁሳቁሶችን ለግሰናል። ይህንን ልናደርግ የቻልነው ማኅበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ነው›› የሚለው ወጣት እንዳልካቸው በዚህ ተግባር የባህር ዳር በጎ አሳቢዎች ማኅበር እና ሌሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ወጣቶች ሚና የጎላ እንደነበር ወጣት አንዳልካቸው አጫውቶናል።
‹‹ሌላው ማኅበራዊ ሚዲያው በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በውጭ የሚኖሩ የባህርዳር ከተማ ተወላጆች በማኅበራዊ ሚዲያ በማስተባበር "85 ኩንታል የህፃናት ምግብ፣ ሴሪፋም፣ ግምቱ ሦስት መቶ ሽህ ብር የሚሆን የእለት ደራሽ ምግብ" ደሴ ከተማ በከፋ ችግር ውስጥ ለሆኑ ህፃናት ማድረስ ተችሏል›› ይላል ወጣት እንዳልካቸው።
በተመሳሳይ መልኩ ይህን ተግባር በማኅበራዊ ሚዲያ ተመልክተው የተማረኩ ኑሯቸው በውጭ ሀገራት የሆነ የባህርደር ተወላጆች ወጣት እንዳልካቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ በማግኘት ገንዘብ በመላክ የሚከተለውን ማድረግ እንደቻሉ አጋርቶናል።
"በውጭ ሀገር ሰባ ሽህ ብር ተልዕኮ ለሰባ "የድሀ ድሀ" ተብለው የተለዩ የሕበረተሰብ ክፍሎች እያንዳዳቸው ዶሮ እና ዶሮን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች" ድጋፍ ማድረግ ተችሏል።
በተመሳሳይ መልኩ በከተማው በቅርቡ ለደሴ ተፈናቃዮች ከተማ አስተዳደሩ ከበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ጋር በመሆን በአዘጋጀው የድጋፍ ዘመቻ የወጣቶቹ እና ማኅበራዊ ሚዲያው ሚና የጎላ ነበር። በዚህም በከተማው በነበሩ የሀብት መሰብሰቢያ ጣቢያዎችን ተከፋፍለው በአካል ተገንቶ አስተባብሯል። በተጨማሪም ሰዎች ወደ መለገሻ ጣቢያዎች እንዲሄዱ በማበረታታት ያደረጉት እንቅስቃሴ ፍሬአማ እንደነበር መታዘብ ይቻላል።
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ጣቢያዎች ድጋፍ እና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል። በዚህ ሰናይ ተግባር ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የከተማውን ማኅበረሰብ በማስተባበር የተለያዩ ድጋፍ የተደረገውም በማኅበራዊ ሚድያ እንቅስቃሴ ነው።
በከተማችን በማኅበራዊ ሚዲያ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ከሚታወቁ ነዋሪዎች መካከል በረታ ተፈራ አንዱ ነው። "ዋርካው" በሚል ቅፅል ስሙ በስፋት ይታወቃል። በረታ በጎልማሳነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በከተማው አጠቃላይ እንቅስቃሴ የነቃ ተሳትፍ በማኅበራዊ ሚዲያ በማድረግ ይታወቃል።
በረታ ተፈራ /ዋርካው/ የባህር ዳር ከነማ እግር ኳስ ደጋፊዎች ማኅበር መስራችና ፕሬዝዳንት ነው። ደጋፊ ማኅበሩን ለማጠናከር በማኅበራዊ ሚድያ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። በዚህም ክለቡ የፕሪሜሊግ ተሳታፊ ሲሆን በከተማ አሰተዳደሩ እና በክለቡ አመራሮች እውቅና ተችሮታል። በተመሳሳይ መልኩ የጣና ስጋት የሆነው እንቦጭ ለማስወገድ በተደረገው ጥረት በማኅበራዊ ሚዲያ በርካቶችን ማስተባበርና ማሳተፍ እንደቻሉ ይናገራል።
በረታ/ዋርካው/ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ በከተማው በጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ደም እዲለግሱ በርካታ ተግባራት በማኅበራዊ ሚዲያ ከማከናወኑ በተጨማሪ በግሉ አስራ አንድ ጊዜ ደም ለግሷል።
በክልሉ በተለያየ ጊዜ በሚከሰት መፈናቅል የከተማዋን ነዋሪዎች በማህበራዊ ሚዲያ በግሉ በማስተባባር አልባሳት እና ምግብ በመሰብሰብ ቦታው ድረስ ወስዶ ማስረከብ መቻሉን በሚከተለው መልኩ ይናገራል።
"ለመተከል ተፈናቃዮች 60 ቦንዳ የአዋቂና የህፃናት አልባሳት፣ ብርድልብስ አንሶላ፣ የተለያዩ በርካታ የህፃናት ምግቦች፤ ሀያ ሰባት ቦንዳ የአዋቂና የህፃናት አልባሳት የተለያዩ የማብሰያና የመመገቢያ ቁሳቅሶች" በራሱ ጥረት በመሰብሰብ ቦታው ድረስ በመሄድ ማድረስ እንደተቻለ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።
በከተማው የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ በችግኝ ተከላ፣ በሀይማኖታዊ በዓላት፣ በከተማዋ በሚደረጉ ትዕይንተ ህዝቦች፣ በከተማዋ በድንገት በተለያየ ምክንያት በሚሰወሩ ህፃናት እና አዋቂዎች ፍለጋ፣ በከተማዋ ሚደረጉ የተለያዩ ሁነቶች ሌሎች ተያያዥ ክስተቶች ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲን በመጠቀም ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የአዲስ ዘይቤ ያገኘችው መረጃ ያስረዳል።
እንደ ባህር ዳር ከተማ ጥቂት ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ማኅባራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ በጎ ወጣቶችን በብዛት እንዲኖሩን መስራት የወቅቱ ተቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ ብዙዎች ይስማማሉ።