ኅዳር 30 ፣ 2014

የሰራተኛ ቅጥርን በምርቃት ዓመት መገደብ ሕጋዊ ነው?

City: Dire Dawaማህበራዊ ጉዳዮች

ሥራ ፈላጊዎች በየዓመቱ የማሻቀባቸውን ያህል ቁጥራቸው የሚጨምር ተመራቂዎችን ወደ ሥራ ለማሰማራት የሚፈጠሩ አዳዲስ የሥራ እድሎች እየበዙ እንዳልሆነ ተደጋግሞ ተነስቷል።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የሰራተኛ ቅጥርን በምርቃት ዓመት መገደብ ሕጋዊ ነው?

ሥራ ፈላጊዎች በየዓመቱ የማሻቀባቸውን ያህል ቁጥራቸው የሚጨምር ተመራቂዎችን ወደ ሥራ ለማሰማራት የሚፈጠሩ አዳዲስ የሥራ እድሎች እየበዙ እንዳልሆነ ተደጋግሞ ተነስቷል። ጉዳዩ የበርካታ ታዳጊ ሐገሮች ራስ ምታት እንደሆነ የሚያትቱ የጥናት ወረቀቶች የችግሩ መነሻ ነው ያሉትን ሲያስቀምጡ ሙስናን፣ ሥራ ፈጣሪ አለመሆንን/ተቀጣሪነትን ብቻ ማለምን፣ የትምህርት ጥራት መጓደልን ያነሳሉ። “መማራችን ትርጉም አጣ”፣ “የያዝነው የዲግሪ ወረቀት ከእንግዲህ አገልግሎት አይሰጥም” እያሉ የሚያማርሩት የቅርብ ጊዜ ተመራቂዎች ደግሞ የቅጥር ሂደቱ ተአማኒ አለመሆኑ፣ የቀጣሪዎች በትምህርት ስርአቱ ላይ እምነት ማጣት፣ አዳዲስ ተመራቂዎችን በሥራ ሂደት ለማሰልጠን አለመፍቀድ፣ ተፈላጊ የሚባሉ የሥራ መደቦች እና ጥሩ ክፍያ ያላቸው ተቋማት በዘመድ ወይም በሕገ-ወጥ ክፍያ መገኘታቸው በቀጣሪዎች በኩል ያሉ ችግሮች ስለመሆናቸው ተመላክቷል። የሥራ ፍላጎትና የክህሎት ማነስ፣ ገንዘብ ላይ ብቻ ማተኮር፣ የሥራ ስነ-ምግባር ጉድለት፣ ሰዓት አለማክበር እና መሰል ሁኔታዎች ደግሞ በአዳዲስ ተመራቂዎች ላይ እንደ ችግር የሚነሱ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቅሷል።

ዮናስ ናሁሰናይ “ከተመረቅኩ ሁለት ዓመት አልፎኛል” ይላል። የመጀመርያ ዲግሪውን በአካውንቲንግ ከጅግጅጋ ዩንቨርሲቲ ከተቀበለ በኋላ በንግድ ሥራ ተሰማርቶ ሁለት ዓመታት ሰርቷል። ንግዱን አቋርጦ በተመረቀበት ሙያ ለመስራት በማሰብ ማስታወቂያዎችን በሚመለከትበት ጊዜ ግን ያልገመተው ነገር እንደገጠመው ነግሮናል “እኔን የሚመለከት ማስታወቂያ ማግኘት አልቻልኩም። ሁሉም ባንኮች ከተመረቀ 2 ዓመት ያላለፈው ይላሉ። ከባንክ ውጭ ያሉትም ልምድ ይጠየቃሉ። ከዚህ የተረዳሁት በማንኛውም አጋጣሚ በተመረቀበት ፊልድ ለ2 ዓመታት ያልሰራ ሰው የመቀጠር እድል እንደሌለው ነው” የሚል ሐሳቡን ሰጥቶናል።  

በልጅነቷ የባንክ ባለሙያ የመሆን ህልም ስለነበራት አካውንቲንግ እንዳጠናች የምትናገረው እድላዊት ማርቆስ “በግልጽ ባይነገርም ዲግሪ ኤክስፓየር እንደሚያደርግ አውቃለሁ” የሚል ሐሳቧን አጋርታናለች። ነዋሪነቷ ድሬዳዋ ከተማ ሲሆን የመጀመርያ ዲግሪ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ነው። “የሁሉንም ባንኮች ማስታወቂያ ተመልከት፤ ማስታወቂያው በወጣበት ዓመት ወይም ከዚያ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ለተመረቁት እንጂ ከዚያ በፊት ላሉት አያወጡም” ትላለች። ከተደጋጋሚ ገጠመኟ ተነስታ ሰዎች በተመረቁበት የትምህርት ዘርፍ ሥራ ሳያገኙ ጥቂት ዓመታት ካለፉ ዲግሪያቸው ከአገልግሎት ውጭ ይሆናል የሚል እምነት ማዳበሯን አልሸሸገችም። “የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት ሊቀጥሩን ፈቃደኛ ካልሆኑ አገልግሎት መስጠት እንደማይችል አምነዋል ማለት አይደለም?” በሚል ጥያቄ ንግግሯን ትቋጫለች።

“የሆነ ጊዜ ‘ፍሬሽ ቦታ የለውም’ ተብለን ከተማርንበት ፊልድ ውጭም ቢሆን ያገኘነውን ሥንሰራ ቆየን። አሁን ደግሞ ‘ከተመረቀ 2 ዓመት ያለፈው ቦታ የለውም’ እየተባልን ነው። በጣም ግራ ያጋባል” የሚለው አሸናፊ ታጠቅ ዲግሪውን ከያዘ 4 ዓመታት አልፈውታል። “የሥራ አጥ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በተመረቁበት ዓመት መገደብ ትክክል አይደለም። ዋናው ነገር መሆን ያለበት ዕውቀት እና ክህሎት ነው” ካለ በኋላ ወጣቱ በትክክለኛው መንገድ ተጉዞ ሥራ ማግኘት እንደማይችል ሲረዳ ሕገወጥ አሰራር ውስጥ እንደሚገባ ያስረዳል፡፡ ለቀጣሪዎች ክፍያ ለመፈጸም፣ ሐሰተኛ የትምህርት እና የሥራ ልምድ ለማሰራት የሚገደቡት በዚህ ምክንያት እንደሆነ ያምናል። “90 በመቶ የኢንጅነሪንግ ተመራቂ ሥራ ፍለጋ ላይ ነው። የፍለጋ ዓመታቱ መራዘም ወረቀቱን ብቻ ሳይሆን የተማረውን ትምህርትም ከጥቅም ውጭ ያደርግበታል” ብሏል።

በተነሳው የሥራ ፈላጊ ተመራቂዎቹ ቅሬታ ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ያገኘናቸው የትምህርት ሚንስቴር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሐረጓ ማሞ “ይህንን ምላሽ መስጠት የሚገባው ትምህርት ሚንስቴር ሳይሆን ሲቪል ሰርቪስ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጋላ ቅርንጫፍ ድሬዳዋ ስትሪክት የደንበኞች አገልግሎት መኮንን አቶ ማስተር ሬድዋን “ለአዳዲስ ተመራቂ ተማሪዎች የስራ እድል ከመፍጠር አንፃር ነው” ብለዋል። “ከሁለት ዓመት በላይ ከሆነ ሌሎች ቦታዎች ላይ በስራ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ለአዳዲስ ተማሪዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ነው” እንደ አቶ ማስተር ገለፃ አዳዲስ ምሩቅ በሚሆኑበት ጊዜ አዳዲስ ጉልበት እናገኛለን፣ የስራ ፍላጎታቸው የተነሳሳ ነው፣ ገና መመረቃቸው ስለሆነም እውቀታቸው ሳይጠፋ ለማግኘት ስለሚረዳን ነው ብሏል።

በአቢሲኒያ ባንክ ድሬዳዋ ድስትሪክት ክሬዲት አናሊስት አቶ ተሻገር እንዳልካቸው በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች አዳዲስ ምሩቃንን እንደሚፈልጉ ይናገራል። “የመጀመሪያው ከሁለት ዓመት በላይም የሚያካትት ከሆነ ሌላ ቦታ ላይ ስራ ላይ ሆነው ለአማራጭ ይወዳደራሉ ተብሎ ይታሰባል። ያደግሞ ሌላ ቦታ የለመዱትን የስራ ባህል ይዘው እንዳይመጡ በማሰብ ነው።ሁለተኛው ደግሞ ምንም ስራ ሳይጀምሩ ከቆዩ ደግሞ ከትምህርቱ በራቁ ቁጥር ስራ ላይ ቶሎ የመቀበሉና ስራውን ቶሎ ለመልመድ ያስቸግራል ሲል ገልጿል። አቶ ተሻገር ባንኮች አገልግሎት ሰጪ ስለሆኑም ቀልጣፋ እና ፈጣን ሰዎች ይፈልጋል። ለዚህ አዳዲስ ምሩቆች እድሜያቸው ከ23- 25 ስለሚሆን ሌላው እንዲመረጡ የሚያደርጋቸው ምክንያት ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም በዕውቀቱ ነገሩን በሕገ-መንግሥቱ እና በአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጁ ከተደነገጉት መብቶች አንጻር ተመልክተውታል።

“የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 41 እንዲሁም የአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጅ 1156/2011 ላይ ያሉትን ድንጋጌዎች ይጥሳል። በሕጎቹ አንድ ኢትዮጵያዊ በማንኛውም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የመሰማራት መብት እንዳለውና በማንኛውም መልኩ አድልዎ ሊደረግበት እንደማይገባ ይደነግጋል” የሚሉት በማንኛውም ፍርድ ቤት የሕግ ጠበቃ እና አማካሪው አቶ አንዷለም “በሥራ ልምድ ካልሆነ በቀር በምርቃት ዓመት እየተደረገ ያለው ገደብ ሕጋዊ መሰረት የለውም” ይላሉ። “የሥራ ልምድ እና ውጤት መጠየቅ አይከለከልም። ሴት ተወዳዳሪዎችን ማበረታታትም የሚፈቀድ ነው። ከዚያ ውጭ የሆነ ማንኛውም መድልዎ ግን ከሕግ አግባብ ውጭ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ስሜ አይጠቀስ ያሉን በአንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በሕግ ክፍል ውስጥ የሚያገለግሉት አስተያየት ሰጪአችንም በሕግ ባለሙያው ሐሳብ ይስማማሉ። “ትክክል አይደለም። ባንኩ ለሥራ የሚያመለክቱ ሰዎች ቁጥር እንዳይበዛበት ከፈለገ ሌሎ አማራጮችን መጠቀም ይችላል። በምርቃት ዓመት ቅጥርን መገደብ ስህተት ነው” ብለዋል።

አስተያየት