በቴሌግራም መልዕክት “የኖርዌይ ቪዛ ሎተሪ መሙያ ቅጽ” የሚል አንድ ማስፈንጠሪያ ሲዘዋወር አስተውለናል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ከ 300 ጊዜ በላይ የታየው ይህ መልዕክት የቪዛ እድሉ በአለም ዙሪያ ላሉ 45,000 ሰዎች የተሰጠ እድል እንደሆነ ይናገራል።።
በልጥፉ የተያያዘው ማስፈንጠሪያ “የኖርዌይ ኢሚግሬሽን ዳይርክቶሬት” ወደሚል ገጽ ይወስደናል። ይህ ድህረ-ገጽ በውስጡ የሚሞላ ቅጽ ያለው ሲሆን ቅጹ የግል መረጃዎችን ከነዚህም ውስጥ አድራሻ ፣ ኢ-ሜይል ፣ የይለፍ ቃል እና ሌሎችንም እንድንሞላ ይጠይቃል።
የአሜሪካ ዲቪ ሎተሪ ፕሮግራም በ1948 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በየአመቱ ለ55,000 ሰዎች የቪዛ እድል ይሰጣል። የ2014ቱ የዲቪ ቪዛ ፕሮግራም(DV-2023) በመስከረም 26 ፣ 2014 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን የሎተሪ ቅጹ በኦንላይን ብቻ የሚሞላ እና የዚህ አመት የሎተሪ መሙያ ጊዜ ደግሞ እስከ ጥቅምት 30 ፣ 2014 ዓ.ም ድረስ ብቻ የሚቆይ ይሆናል።
በጥቅምት 4 ፣ 2014 ዓ.ም በጋና አክራ የሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲ “ወደ አንድ ድህረ ገጽ የሚመራ ማስፈንጠሪያ በመልዕክት መልክ እየተዘዋወረ ስላለ ከዚህ የማጭበርበሪያ መንገድ ተጠንቀቁ። ይህ የጽሁፍ መልዕክት የኖርዌይ ቪዛ ሎተሪ ወደሚል ኦንላይን የሚሞላው የቅጽ ገጽ ይወስደናል። ይህ የሚሞላ ቅጽ፣ የጽሁፍ መልዕክት እና ድህረገጽ ከቪዛ መሙያ ሲስተም ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ማጭበርበሪያ ስለሆነ ከእንደዚህ አይነት የማጭበርበሪያ መንገዶች ተጠንቀቁ።” በተጨማሪም “እንደዚህ አይነት የሎተሪ ፕሮግራም የለንም” በማለት አሳውቆ ነበር።
ሀቅቼክም በአዲስ አበባ የሚገኘውን የኖርዌይ ኤምባሲ በኢሜል ያነጋገረ ሲሆን የኤምባሲው ቆንፅላ ጽህፈት ቤት “ኖርዌይ ምንም አይነት የቪዛ ሎተሪ ፕሮግራም የላትም” በማለት አረጋግጠውልናል። አዲስ አበባ በሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲ ለመኖሪያ እና ለስራ ሲሞላ የነበረው የቪዛ ፕሮግራም ከሃምሌ 25 ፣ 2011 ዓ.ም ጀምሮ የተዘጋ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች የሚስተናገዱት በኬኒያ ናይሮቢ በሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲ ነው።
እንደ አሜሪካ ያሉ በህጋዊ መንገድ ወደሃገራቸው የመሄድን እድል የሚያመቻቹ ሃገራቶች እንዳሉ ሁሉ ኖርዌይ ግን እንደዚህ አይነቱን ዕድል መስጠት አልጀመረችም።
ስለሆነም ይህ የቴሌግራም መልዕክት የግል መረጃዎችን ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ስለሚጠይቅ እና አሳሳች የሆነ መልዕክት በመሆኑ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል።