ጥቅምት 16 ፣ 2014

ሀሰት፡ ምስሉ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባለው ግጭት ምክንያት የተቃጠለ መኪናን አያሳይም

HAQCHECK

አሁን በሰሜኑ ካለው ግጭት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ስለሌለው ምስሉ ሀሰት ነው።  

Avatar: Kirubel Tesfaye
ኪሩቤል ተስፋዬ

Kirubel works as a fact-checker at Addis Zeybe for HaqCheck. He is interested in learning and expanding his writing and journalistic skills.

ሀሰት፡ ምስሉ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባለው ግጭት ምክንያት የተቃጠለ መኪናን አያሳይም

ከ140,000 በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገጽ “የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ድሮኖችን በመጠቀም የአየር ላይ ጥቃቶችን አካሄደ” በማለት አንድ ልጥፍ አጋርቷል።  ይህን ጽሁፉ በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል ያለውን ግጭት የሚያሳይ በማለት የሚቃጠል መኪናን አያይዞ ለጥፏል። ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ ልጥፍ ከ 55 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። ነገር ግን ይህ ምስል በሰሜኑ የሃገሪቷ ክፍል በመከላከያ ሰራዊት የተወሰደን የአየር ላይ የድሮን ጥቃት ስለማያሳይ ሀሰት ነው።

የሕውሃት ሃይሎች በሰሜን ዕዝ የሚገኘውን ሰራዊት ካጠቁ በኋላ በፌደራሉ መንግስት እና በሕውሃት ሀይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ጥቅምት 24 ፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከአሁን እንደቀጠለ ነው።

በሰኔ 2013 ዓ.ም መጨረሻ የፌደራሉ መንግስት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከክልሉ ሙሉ በሙሉ አስወጣ። የፌደራሉ መንግስት ከክልሉ ለቆ ከወጣ በኋላ የሕውሃት ሃይሎች ራሳቸውን በማጠናከር እና ወደ አማራ እና አፋር ክልል አጎራባች አካባቢዎች ጥቃት በመፈጸም ግጭቱ እየተስፋፋ ሄዷል። ይህን ተከትሎም በፌደራል መንግስቱ የሚካሄዱ አዳዲስ የወታደራዊ እርምጃዎች እና የመልሶ ማጥቃት ሪፖርቶች በብዛት እየወጡ ይገኛሉ። የሕውሃት ቃል አቀባይ የሆነው አቶ ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከአማራ እና አፋር ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር በመሆን የአየር እና የምድር ጥቃቶች እያደረጉባቸው እንደሆነ አረጋግጧል

ሆኖም በጉግል ሪቨርስ ኢሜጅ የተገላቢጦሽ የምስል ፍለጋ ከላይ የተያያዘው ምስል በሰሜኑ የሃገሪቷ ክፍል የደረሰውን የመኪና ቃጠሎ እንደማያሳይ ለማረጋገጥ ተችሏል። ምስሉ ከዚህ ቀደም africanews.com በሚባል አንድ አፍሪካዊ እና አለማአቀፋዊ የሆኑ ዜናዎችን በሚያቀርብ የሚዲያ ተቋም “ለተቃውሞ በወጡ ሰዎች የዳንጎቴ ፋብሪካ ጥቃት ደረሰበት” በማለት ከአንድ ዜና ጋር ተያይዞ ተለቆ ነበር። መስከረም 24 ፣ 2009 ዓ.ም በኢሬቻ ክብረ በዓል ወቅት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በደረሰው ግጭት ላይ ባለቤትነታቸው የዳንጎቴ ሲሚንቶ የሆኑ የተለያዩ መኪኖች እና ማሽነሪዎች አዳ በርጋ የሚባል አከባቢ ሲቃጠሉ ውድ የሆነው የሰው ህይወት እና ብዙ የህዝብ መገልገያ የሆኑ ተቋማት ወድመዋል። 

ናይጀሪያዊው የቢዝነስ ሰው አሊኮ ዳንጎቴ በስፋት በሲሚንቶ ኢንደስትሪው ዘርፍ ላይ ኢንቨስት በማድረግ የሚታወቅ ሲሆን ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በአፍሪካ ከሚገኙ ትልልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አንዱ ነው። ፋብሪካዎቹም ኢትዮጵያን ጨምሮ በናይጄሪያ ፣ ሴኔጋል ፣ ጋና ፣ ካሜሮን ፣ ዛምቢያ ፣ ታንዛኒያ እና ሳውዝ አፍሪካ ውስጥ ይገኛሉ። 

በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል በትግራይ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ ብዙ ምስሎች እየወጡ ቢሆንም በልጥፉ ላይ ለማሳየት የተሞከረው ምስል ግን አሁን በሰሜኑ ካለው ግጭት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ስለሌለው ምስሉ ሀሰት ነው።   

አስተያየት