የገቢዎች ቢሮ አዲስ አሰራር በግብር ከፋዮች ዘንድ ቅሬታ አስነሳ

Addis Zeybeጥቅምት 15 ፣ 2014
City: Addis AbabaNews
የገቢዎች ቢሮ አዲስ አሰራር በግብር ከፋዮች ዘንድ ቅሬታ አስነሳ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በገቢ ማሳወቂያ ወቅት የንግድ ድርጅታችንን የባንክ ሂሳብ እንድናያይዝ የሚያዝ መመርያ ማውጣቱ አግባብ አይደለም ሲሉ በተለያየ ንግድ ላይ የተሰማሩ የከተማዋ ግብር ከፋዮች ቅሬታቸውን አሰሙ።

ቅሬታ ያስነሳው የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ለሰራተኞቹ ባስተላለፈው የ2014 ዓ.ም የግብር ማሳወቂያ ወቅት ለሚቀርቡ የሂሳብ መዝገቦች የሚውል የቅድመ-ኦዲት አሰራር ሥርዓት ላይ ከተጠቀሰው የታክስ ኦዲተር በገቢ ማሳወቂያ ወቅት መሟላት ከሚገባቸው መመርያዎች መካከል ከዚህ ቀደም ሲተገበር አልነበረም የተባለ መመርያ ማካተቱ ሲሆን እሱም የደረጃ “ሀ” እና “ለ” የግብር ከፋዮች በገቢ ማሳወቂያ ወቅት ለማመሳከርያ እንዲያገለግል የባንክ ሂሳብ መዝገብ ይዘው እንዲቀርቡ ያስገድዳል።

በመሆኑም በ2013 እና ከዛም በፊት ባሉት በጀት ዓመቶች በቅድመ-ኦዲት ወቅት በአጠቃላይ በግብር ከፋዮች በኩል የተስተዋሉ የህግ ተገዢነት ጉድለቶች መካከል የደረጃ “ሀ” እና “ለ” የግብር ከፋዮች ደረጃ ተመዝግበው የሚገኙት ግብር ከፋዮች በገቢ ማሳወቂያ ወቅት የሂሳብ መዝገብ ይዘው የሚቀርቡት ከ50% በታች መሆናቸውን በመጥቀስ እና ሁኔታውን በሚመለከት ከዚህ ቀደም አስገዳጅ ሁኔታ ስላልተቀመጠ የተለመደ በሚመስል መልኩ ያለሂሳብ መዝገብ በባለስልጣን መስርያቤቱ ግምት አወሳሰን እየተስተናገዱ የነበረ ቢሆንም አሁን ካለንበት በጀት አመት ጀምሮ ግን ማንኛውም ግብር ከፋይ የዘመኑን ሂሳብ መዝገብ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ ባለስልጣኑ ማስገደድ እንዳለበት ያትታል።

ስድስት ኪሎ አካባቢ በተለምዶው ሚኒ ማርኬት ተብሎ የሚጠራውን መለስተኛ ሱቅ ከፍታ በባለቤትነት የምትመራው ኮከብ በቀለ ከቅሬታ አሰሚዎቹ አንዷ ናት። ሂሳቧ ላይ የተንቀሳቀሰውን ገንዘብ ከንግድ ገቢዋ ጋር በማስተያየት ኦዲት መሰራቱ ተገቢ አይደለም ትላለች።

“እኔ ባንክ አካውንት ስጠቀም ለሱቄ ለብቻ ለግል ጉዳዬ ለብቻ አድርጌ የማንቀሳቀስ ልምድ የለኝም። በመሆኑም የሂሳብ መዝገቤ እና የንግድ ስራዬ እኩል ሊሆን አይችልም” 

ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ ደግሞ አቶ ሰዒድ ሁሴን ይባላሉ፣ መርካቶ አካባቢ ፍራሽ፣ ምንጣፍ እና ተያያዥ እቃዎችን የሚሸጡበት አነስተኛ ሱቅ አላቸው። ገቢዎች ያቀረበውን አሰራር እንደማያውቁት እና ድንገተኛ መሆኑ ግርታ እና በሂሳብ አያያዝ ላይ መዛባት እንዳመጣባቸው ይናገራሉ። “መንግስት የሰራህበት ነው ብሎ ከሂሳብ መዝገቤ ላይ የሚያስተያየው ገንዘብ ከንግድ ስራዉ ዉጭ የተገኝ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ይህ አሰራር አስፈላጊነቱ ከታመነበትም ቀድሞ ለነጋዴዎች ማሳወቅ ይኖርበት ነበር” ሲሉም ስሞታቸውን አቅርበዋል።

ይህን እና መሰል ስሞታዎችን የሰማችው አዲስ ዘይቤም የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ከደንበኞች ወደ መስርያ ቤቱ የሚመጡት ቅሬታዎች ምን እንደሚመስሉ እና የመስርያ ቤቱ ሰራተኞችስ በምን መልኩ እያስተናገዱ ነው ስትል ጠይቃለች።  

በገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መካከል በአንዱ ኦዲተር ሆኖ የሚሰራ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ባለሙያ እንደገለጸልን ለደንበኞች ይህ አሰራር በአስገዳጅ መልኩ እንደሚጀመር ቀድሞ መረጃ ሳይሰጣቸው ግብር ለማሳወቅ ሲመጡ ስለመመሪያው ሲነገራቸው ብዙ ቁጣ ያነሳሉ። “እንደኔ አመለካከት ልክ ናቸው ምክንያቱም እንዲህ ያለው አሰራር ሲተገበር ቀዳሚው ተደራሽ የሚሆኑት ደንበኞች በመሆናቸው በአግባቡ ቀድመው እንዲያውቁ ሊደረግ ይገባ ነበር። እኛም ግልጽ ማብራሪያ መስጠት ስላልቻልን ትዕዛዙ ከላይ መሆኑን ከመንገር ውጪ ምንም ማድረግ አልቻልንም” ሲል አስተያየቱን ሰጥቶናል።

በመሆኑም ከነዚህ ቅሬታዎች ጋር በተገናኘ ስለአዲሱ መመርያ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጥያቄ ያቀረብንላቸው የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈሪ ይህ ጉዳይ በትክክል ተግባራዊ አለመደረጉ ነው ጥያቄ መሆን ያለበት እንጂ የታክስ አስተዳደር ህጉ ከበፊት ጀምሮ ይህ እንዲደረግ ያዛል ሲሉ ያስረዳሉ።

“ላለፉት ጥቂት የማይባሉ አመታት በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 26(5) መሰረት ባለስልጣኑ የዓመቱን ግብር በግምት የሚወሰን ቢሆንም እንደህግ ደግሞ ግብር ከፋዩ በሂሳብ መዝገብ መሰረት የግብር ማሳወቅ ግዴታ ስላለበት የዘመኑ ግብር በግምት ስሌት መሰረት የደረሰው ማንኛውም ግብር ከፋይ የዘመኑን ሂሳብ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ ይገደዳል” በማለት ግብር ከፋዩ የተጣለበትን ግዴታ መወጣት ካልቻለ በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 45(1)(ሀ) መሰረት እርምጃ እንደሚወሰድበት ገልጸዋል።

“ታዲያ ይህ አይነት መመርያ ተግባራዊ ሳይደረግ በመቆየቱ በተለይ አዳዲስ ነጋዴዎች ላይ ግርታን ሊፈጥር ስለመቻሉ ታስቦበታል ወይ?” ስንል ላነሳልናቸው ጥያቄ ሲመልሱም “ተግባራዊ ሳይደረግ በመቆየቱ ከዚህ ቀደም በዚህ ልክ የሂሳብ መዝገብ የማይዙ ግብር ከፋዮች የተስተናገዱበት አኳኋን ስህተት እንደነበር ስለታመነ በአዲሱ አሰራር መሰረት ይህን ስር የሰደደ ችግር በዝርዝር በመፈተሽ ቀጣይ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ነው እየሰራን የምንገኘው ” ብለዋል።

አክለውም መመርያው የማያውቁት ነጋዴዎችን በተመለከተ “ለደንበኞች ግልፅ በሚሆንበት መንገድ ለመስራት እየተሞከረ ነው፣ ቅሬታዎችን በሚመለከትም የባንክ ሂሳብ መዝገብ ላይ ያሉ የገንዘብ ምንጮችን ለመለየት አስቸጋሪ ስለማይሆን ደንበኞች ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ ነው የሚሰራው” ሲሉ አክለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ይህ አሰራር የወቅቱን ግብር ታክስን ለመሰወር እና ትክክለኛ ግብር ላለመክፈል እንዲሁም በቀጣይ የታክስ ማሳወቂያቸው ወቅት ለኦዲት ምርመራ እንዳይመረጥና እንዳይመረመር ለማስደረግ ሲባል የታክስ ህጉን በመጣስ የሚንቀሳቀሱ ግብር ከፋዮችን ለመቆጣጠር አመቺ ይሆናል።

በተያያዘም በሂሳብ መዝገብ መሰረት ግብር የመክፈል ኃላፊነት የተጣለባቸው ግብር ከፋዮች ከባለፉት አመታት የግብር ማሳወቂያ ወቅት እንደተገመገመው በሚያቀርቡት የሂሳብ መዛግብትና የታክስ ማስታወቂያዎች አብዛኞቹ አጥጋቢ ያልሆነ የገቢ ማሳወቂያ እያቀረቡ በበርካታ ቢሊዮን የሚገመት ገቢ አሳንሶ በማሳወቅ ጉልህ መጠን ያለው ግብር ገቢ እያሳጡ መገኘታቸውን በመጥቀስ የሂሳብ መዝገብን በመጠቀም ግብር ከፋዮች ግብርን ላለመክፈል የሚያደርጉትን ጥረት በመለየት ለማስተካከል የቅድመ ኦዲት አሰራሩን አስተካክሎ ማቅረቡ አስፈላጊ መሆኑን ቢሮው አሳውቋል።