በውሃ አምራች ፋብሪካዎች ተከባ የምትጠማው ዓለምገና

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታጥቅምት 12 ፣ 2014
City: Addis Ababaኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮች
በውሃ አምራች ፋብሪካዎች ተከባ የምትጠማው ዓለምገና

“እኛ ሰፈር ውሃ ትጠፋለች ሳይሆን ውሃ ኖራ አታውቅም ነው የሚባለው”

ይህ የአንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ድምጽ ነው። በኢትዮጵያ መዲና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ተስፋ መቁረጥ የተጫነው የቅሬታ ድምጽ።

“የቧንቧ ውሃ የምናየው በትንሹ በስድስት ወር አንዴ ነው” በተለምዶ አጠራሩ ዓለምገና በመባል የሚታወቀው የመኖርያ መንደር ነዋሪዎች “ውሃ መጥፋቱን ስለለመድነው ውሃ መምጣቱ ያስደነግጠናል” ይላሉ።

ነዋሪዎቿ በውሃ እጥረት የሚሰቃዩባት ዓለምገና፤ በንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ችግር ተደጋጋሚ ወቀሳ የምታስተናግደው ዓለምገና፤ ከስድስት ወራት ለሚበልጥ ጊዜ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በቧንቧዎቿ የማይፈሰው ዓለምገና የውሃ ሐብታም ናት። ከርሰ ምድሯ ለመጠጥ ተስማሚ የሆኑ ማዕድናትን በያዘ ፈሳሽ የተሞላ ነው። በገጸ ምድሯ የሚመላለሱ ድሃ ነዋሪዎቿን እያስጠማች። ከርሰ ምድሯን ለቆፈሩ ኢንቨስተሮች እርካታ ትለግሳለች።

የአካባቢው ነዋሪ የሆነው ዳግም ተስፋዬ “አቅም ያለው የማዕድን ውሃ እየገዛ አቅም የሌለው ከከተማዋ ወጣ ብለው ከሚገኙ የውሃ ጉድጓዶች እና ምንጮች እየቀዳ ነው ህይወቱን የሚገፋው” ሲል በምሬት ይናገራል። “ችግራችን እንዲፈታ ከቀበሌ እስከ ክፍለ ከተማ፣ ከክፍለ ከተማ እስከ ከተማ አቤት ብንልም ሰሚ አላገኘንም” ይላል። በቤት ውስጥም ሆነ በሰፈሩ አካባቢ በቂ የመስመር ውሃ አቅርቦት አለመኖሩ እርሱን እና ቤተሰቡን ለዘርፈ ብዙ ችግር ስለመዳረጉ ይናገራል። ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎችም በዳግም ሐሳብ ይስማማሉ። ውሃ እንደልብ አለመገኘቱ ለተጨማሪ ወጪ፣ ለተላላፊ በሽታ፣ ለእንግልት፣ ለጊዜ ብክነት እንደዳረጋቸው ለአዲዝ ዘይቤ ተናግረዋል።

ወይዘሮ እመቤት ቶሎሳ እድሜያቸው በሀምሳዎቹ አጋማሽ የሚገመት እናት ናቸው። ንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር ክፉኛ ከጎዳቸው መሃከል ይጠቀሳሉ። ውሃ ለማግኘት ከመኖርያ ሰፈራቸው ርቀው ረዥም መንገድ ይጓዛሉ። ብዙ ተጉዘው፣ የተጋነነ ክፍያ ፈጽመው የሚያገኙት ውሃ ለጤና ተስማሚ ባለመሆኑ ለጤና ችግር ተዳርገዋል። ከበዛ ድካም በኋላ የሚያገኙት ውሃ ከቤተሰባቸው ተርፎ ለሚያሳድጓቸው እንስሳት (ከብቶች እና የወተት ላሞች) ሊተርፍ ባለመቻሉ ኑሯቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል። በውሃ ጥም የሚሰቃዩት እንስሳት የሚጠበቅባቸውን ጥቅም ባለመስጠታቸው የቤተሰባቸው ገቢ ቀንሷል።

ዓለምገና “የስ ውሃ”፣ “ዋን ውሃ” እና “ሸገር ውሃ”ን ጨምሮ ወደ 6 የሚጠጉ የመጠጥ ውሃ አምራች ኢንዱስትሪዎች መገኛ መሆኗ ነገሩን የበለጠ አስገራሚ ያደርገዋል። በፕላስቲክ ኮዳ የታሸገ ውሃ ለገበያ የሚያቀርቡ ስኬታማ ፋብሪካዎች ናቸው።

በአካባቢው ከሚገኙት ከውሃ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የስ ውሃ ለአካባቢው ነዋሪዎች በአነስተኛ ዋጋ ውሃ ያቀርባል። (በ20 ሊትር ጀርካን 2 ብር) መቀመጫው በዚያው አካባቢ የሆነው የቀለም፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ሮቶ እና መሰል ምርቶችን ለገበያ ሚያቀርበው ሱፐር ደብል ቲ የተባለው ኩባንያ በበኩሉ የአካባቢው ሰው በነጻ ውሃ ማግኘት ሚችልበትን መንገድ እንዳመቻቸ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

ይሁን እንጂ ከእነዚህ እና መሰል ድርጅቶች በተለያየ መልኩ የሚገኘው የውሃ አቅርቦት እና የአካባቢው ነዋሪ ቁጥር እንዲሁም የውሃ ፍላጎት ስለማይመጣጠን የውሃ እጦቱ ለነዋሪው ችግር መሆኑን ቀጥሏል። 

እንደ ዳግም ገለጻ ከሆነ ደግሞ በአካባቢው እንደ ጀሪካን ያሉ የውሃ ማጠራቀሚያ እና መቅጃዎች በማይገባቸው ዋጋ እንደሚሸጡ ሲያስረዳ “20 ሊትር ባዶ ጀሪካን ከ150 ብር እስከ 200 ብር ነው ሚሸጠው” ሲል በምሬት ይናገራል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በመዲናችን እና በክልል ከተሞች የውሃ አቅርቦት ችግር የእለት ተእለት ገጠመኝ መሆኑ ሀቅ ነው። በአንዳንድ ገጠራማ የሀገሪቱ ክፍል ደግሞ ከነአካቴው የውሃ መስመር ዝርጋታ አለመኖሩም ይታወቃል። ይሁንና የታሸገ ውሃን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ኢንዱስትሪዎች  በሚንቀሳቀሱባት ዓለምገና ይሄን ያህል ጊዜ ውሃ ጠፍቶ መቆየቱ ከምን የመነጨ ነው? መንግስትስ የነዋሪውን አቤቱታ እንዴት ይመለከተዋል? ስንል ጠየቅን።

የአዲስ አበባ የውሃና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰይፈዲን መሃዲ ስለጉዳዩ ሲያብራሩ አካባቢው በተደጋጋሚ ውሃ ከሚቋረጥባቸው ሰፈሮች መካከል መሆኑን ተናግረዋል። ለችግሩ ምክንያት ሲሉ የጠቀሱትም አካባቢው ለኢንዱስትሪ አመቺ በመሆኑ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የልማት ስራዎች በሚሰሩበት ወቅት የመስመሮች መሰበርና መቆረጥ፣ የመብራት መቆራረጥ ይጠቀሳሉ።

“ዓለምገና ሰፋፊ ፋብሪካዎችን መያዟ ይታወቃል። በዚህም ብዙ ነዋሪዎች ላይ የከርሰ ምድር ውሃ ችግር ከሌለ ውሃ ለምን ይቋረጣል የሚል ጥያቄ ሊፈጥር ይችላል። ነገር ግን ኢንዱስትሪዎቹ የሚመሰረቱበት ቦታ አቀማመጥ እና እና የዓለምገናን መልክዓ ምድራዊ አቀማማመጥ ስንመለከት ለውሃ ስርጭት አመቺ ያልሆኑ ችግሮችን ማስተዋል ይቻላል”

ሲሉም አብራርተዋል።  አክለውም ውሃ ጠፍቶ የሚቆይበትን የጊዜ ርዝማኔ በሚመለከት ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ቅሬታውን ለመፍታት ከአካባቢው የልማት አስተባባሪዎች ጋር እየሰሩ መሆኑን በመጥቀስ ችግሮቹን በማጥበብም ሆነ ከዚያም አልፎ በመቅረፍ ዘላቂ እልባት ለመስጠት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን አስረድተዋል።

ሌላው የተገለፀው ችግር ደግሞ የከርሰ ምድር ውሃ ላይ የሚያጋጥመው የውሃ መሳቢያ ፓምፕ መበላሸት እየፈጠረ ያለው ችግር ነው። ፓምፑ ሲበላሽ ጉድጓዶቹ ጥልቅ በመሆናቸው ለማስተካከል ከሰባት ያላነሰ ቀናትን ይፈጃል፤ ይህም በአቅርቦቱ ላይ ችግር እየፈጠረ ነው።

በአካባቢው ላይ ማኅበራዊ ኃላፊነቴን ነጻ ውሃ በማቅረብ በመወጣት ላይ እገኛለሁ የሚለው የሱፐር ደብል ቲ ፋብሪካ ዋና መስራች እና ባለቤት አቶ ፀጋዬ ስማው “የውሃ ችግሩ በልማት ምክንያት መምጣቱ ይነገራል። ልማቱንም አንቃወምም ነገር ግን ሕብረተሰቡ እንዳይቸገር አማራጭ የውሃ መስመር በበቂ ሁኔታ መዘርጋት ነበረበት” ይላሉ። ድርጅታቸው ለማኅበረሰቡ የሚያቀርበውን የውሃ አማራጭ በተመለከተም በውሃ እጦቱ በርካቶች እየተቸገሩ መሆኑን በመግለጽ ድርጅታቸው ቢያንስ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ህፃናት አዛውንትና ነፍሰጡሮችን ቅድሚያ በመስጠት ለማገዝ እንደሚሞክሩ ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪያችን ደግሞ በዓለምገና የሚሰራው የመንገድ ግንባታ አስተባባሪና የየሐ የተቀናጀ የተፈጥሮ እርሻ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እጸገነት ኃይሉ ሲሆኑ የውሃ ችግርን ለመቅረፍ አዳዲስ የውሃ መስመሮችን በመዘርጋት ሕብረተሰቡ ውሃ እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ።

“ይህንም በቀጣይ አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው በማለት ከዚህ ቀደም ሕብረተሰቡ በመንገድ ከፍተኛ ችግር የነበረበት ሲሆን አሁን እሱን ለማስተካከል በሚሰራው ስራ ለሚፈጠሩ አንዳንድ ችግሮች በትዕግስት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል። የዚህ ልማት ተጠቃሚ ሕብረተሰቡ ነውና” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።

እንደ እፀገነት ገለፃ በመላው አዲስ አበባ ዓለምገናን ጨምሮ ተደጋጋሚ የውሃ እጥረት የሚከሰትባቸውን ሥፍራዎች በመለየት ዘላቂ እልባት እስከሚሰጥበት ድረስ የአጭር ጊዜ መፍትሄ ለመስጠት በየአካባቢዎቹ የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ ስራዎችን እየተፋጠኑ መሆኑን ገልጸው ችግሩ በአጭር ጊዜ የሚቃለል በመሆኑ ሕብረተሰቡ በትእግስት እንዲጠባበቅ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ ጋር አያይዘውም ለነዋሪዎች በመንግሥት በኩልም የቦቴ ውሃ እንደሚቀርብ ቢነግሩንም ከነዋሪዎቹ ባገኘነው መረጃ መሰረት የሚቀርበው የቦቴ  ውሃ በወራት አንዴ የሚመጣ መሆኑን በማንሳት ከስንት አንዴ ቦቴው በሚመጣበት ጊዜ ደግሞ በአካባቢው የሌሉ ሥራ የሚውሉ ሰዎች ውሃ ስለማያገኙ ከጊዜያዊ ይልቅ ዘላቂ መፍትሄ የሚበጅበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል ይላሉ።

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist works at Addis Zeybe as a reporter while exploring her passion for storytelling and content creation.