ከዚራ፡ የድሬዳዋ ፈርጥ

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራውጥቅምት 12 ፣ 2014
City: Dire Dawaታሪክ
ከዚራ፡ የድሬዳዋ ፈርጥ

“ከዚራ” የትላንቷን ድሬዳዋ ከተማ በጉልህ ከሚያሳዩ ህያው የታሪክ አሻራዎች መካከል አንዷ፤ ምናልባትም ቀዳሚዋ ናት። የከተማዋን ምስረታ ተከትሎ በቀዳሚነት ከተቆረቆሩት የመኖርያ መንደሮች መካከል ተጠቃሽ ናት። በከተሞች ልማት ታሪክም የመጀመርያዋ በፕላን የተሰራች መንደር ስለመሆኗ ይነገራል። ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ የውጭ ሐገር ዜጎች መኖርያ እንደነበረችም ከተማዋን አስመልክተው የተጻፉ መዛግብት ያስረዳሉ።

ድሬዳዋን ለሁለት የከፈላት ደቻቱ ወንዝ እግረ መንገዱን የጥቁርና የነጭ ጠረፍ ሆነ። የጥቁር ተፈላጊነት ለከባድ የጉልበት ሥራ ብቻ ሆነ። የመኖርያ እና የመዝናኛ ማዕከል የሆነችው ከዚራ ጥቁር የማይረግጣት ብርቅ መንደር ሆነች። ማለፊያ ወረቀት ሳይዝ የከዚራን ምድር የረገጠ ኢትዮጵያዊ በ“ወንጀል” ይጠየቃል። በጸሐይ የጋለ በርሜል ላይ ተንጋሎ የግርፋት ቅጣቱን ይቀበላል።

በከዚራ ውስጥ ከኖሩ የውጪ ዜጎች መካከል ግሪኮች፣ ዐረቦች፣ ፈረንሳዮች፣ አርመኖች እና እንግሊዛውያን በብዛት እንደሚገኙበት መረጃዎች ያመለክታሉ። የከዚራ የኪነ-ሕንፃ ጥበብ፣ የዛፎችና መንገዶች ሁኔታ በዚያን ዘመን የኖሩባት የውጭ ሀገራት ዜጎች ውጤት ነው። 

ከዚራ “ኮንቲኔንታል ሆቴል”፣ “መኮንን ባር”፣ “ብሔራዊ ሆቴል”፣ “የአርመኖች ቤተ-ክርስቲያን”፣ “የግሪኮች ቤተ-ክርስቲያን” መገኛ ነች። የግሪኮች ትምህርት ቤትን ጨምሮ “ምስራቅ ጀግኖች”፣ “አቡነ እንድሪያስ”፣ “ብስራተ ገብርኤል”፣ “የእመቤታችን” የሚሰኙ ትምህርት ቤቶች ይገኙባታል። ጥንታዊዎቹ ባለ ታሪኮች ሲኒማ ኦምፓየር እና ሲኒማ መጂስቲክ መገኛቸው ከዚራ ነው።

በርካታ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችም ከዚራ ውስጥ አሉ። በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተገነባው የድሬዳዋ ቤተመንግሥት፣ የድሬዳዋ ካቶሊክ ካቴድራል፣ የአሊያንስ ኢትዮ-ፍራንስ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እና ሌሎች ዘመናዊ ሕንጻዎችም ይገኙባታል። ማራኪ የኪነ-ሕንጻ ጥበቦችም ለከዚራ ተጨማሪ ውበት ከሆኑ ድምቀቶቿ መካከል ናቸው። የነጋድራስ ሀሲብ ያ ዲልቢ መኖሪያ ቤት (የአሁኑ የድሬደዋ ሙዝየም)፣ የእስራኤሎች ቤት ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው።

ድሬደዋ ከባቡር መስመር ዝርጋታ ጋር የተመሰረተች ከተማ ነች። የከተማ መልክ ሳይኖራት የባቡር መተላለፊያ ብቻ ሆና ለአንድ ዓመት ቆይታለች።

የባቡር ሀዲዱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከጅቡቲ የተነሳው የመጀመሪያው ጉዞ በርካታ የምድር ባቡር ኩባንያና የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ሰራተኞችን ጭኖ ነበር። ታህሳስ 14 ቀን 1895 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ዛሬ ድሬደዋ የምድር ባቡር ኩባንያ እና ጽ/ቤት ያለበት አካባቢ ደረሰ። በዕለቱ በርካታ ድንኳኖች ተተክለው የኩባንያው ሰራተኞችና ኃላፊዎች ከተሙ። ያቺ ቀን ከተማዋ የተቆረቆረችበት ተደርጎ ይወሰዳል።

የባቡር አገልግሎቱ የሚጠበቅበትን ያህል እንዲሆን የድሬደዋን ከተማ መሆን ግድ አለ። ሥፍራው የከተማ መልክ እንዲይዝ የግንባታ ባለሙያዎች በባቡር ጣቢያው አካባቢ አረፉ። መሃንዲሶችን ጨምሮ ሌሎቹ የግንባታ ባለሙያዎች ያረፉበት ስፍራ “ገዚራ” ወይም በአሁን አጠራር “ከዚራ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነበር። ስያሜው “ቀፊራ” እንደነበር የሚናገሩም አሉ። የግንባታ ሥራዎቹን የሚያግዙት የጉልበት ሰራተኞች ከደቻቱ ወንዝ ባሻገር ሠፈሩ። በእጅ ጥበብና በሌላም የሙያ መስክ ልዩ እውቀት ያላቸው ፈረንጆች ብቻ ከዚራ ይኖሩ ነበር። አውሮፓዊ ያልሆነ ሌላው ህዝብ ግን ነዋሪነቱ መጋላ ሆነ።

ከዚራ በፈረንሳይ መሐንዲሶች ተቀየሰች (ጣልያናውያን የሚሉ ምሁራንም አሉ)። ሰፋፊ መንገዶች ያሏት ለመኖርያ እና ለንግድ የምትመች የማድረግ ዓላማ ያላቸው ቀያሾቿ ግንባታዎችን ያካሄዱት የከተማዋን ቀጣይ እድገት ታሳቢ ባደረገ በጥንቃቄ ነበር። ኩባንያው በተመሰረተ በጥቂት ወራት ውስጥ ከጣቢያው ሕንጻ በተጨማሪ የጉምሩክ ቢሮዎች፣ የመኖሪያ ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ግንባታዎች ተፈጠሩ።

አቶ መላኩ ይፍሩ ከዚራ መኖር ከጀመረ ከ30 ዓመት በላይ እንደሆነው ይናገራል። አቶ መላኩ ስለከዚራ ሲናገር “እርግጥ የድሬ ሰፈሮች በሙሉ ውብ ናቸው። የከዚራ ውበት ግን እጅግ የተለየ ነው።” ይላል። ከዚራ የድሬዳዋ ዓይን ነው።  ከዚራ የድሬዳዋ ህይወት ነው። አንድ ሰው በተሟላ ሁኔታ ድሬዳዋን መጎብኘቱ የሚታወቅለት ስለ“ከዚራ” ሰፋ ያለ መግለጫ መስጠት የቻለ እንደሆነ ነው። ድሬዳዋን በሚዘክሩ ትረካዎችም ሆነ የከተማዋን ትሩፋቶች በሚያስቃኙ ዘጋቢ ፊልሞች ውስጥ ጎላ ብሎ የሚታየው ከዚራ ነው። ከዚራ ግርማ ሞገስ ያለው ሰፈር ነው። የግርማ ሞገሱ አክሊሎች ደግሞ በሰፋፊ ጎዳናዎቹ ዳርቻ የተሰደሩት ትዝተኛ ጥላዎች ናቸው” ይላል።

በመንገዱ ግራና ቀኝ የተተከሉት ዠርጋጋ ዛፎች መንገደኛን ከኃይለኛው ጸሐይ አስጥለው መረጋጋትን ያድላሉ። በፍቅር ውስጥ ያሉ ወጣቶች ለእግር ሽርሽር (ወክ) እንዲመርጡት ያስገደደው እውነታም ይህ ነው።

የሳቢያን ሰፈር ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ዓባይ ይሁኔ በተለይ ቀደም ባለው ግዜ ስለነበረው የከዚራ ጥላ ተናግው አይጠግቡም። የከዚራ ጥላ ውበት ብቻ አይደለም፤ ህይወትም ነው። የቆላ ጸሐይ ከአናቷ በሚያነዳት ከተማ እስትንፋስ የሚዘሩት እነርሱ ናቸው። በተናፋቂዋ ከተማ ነፍሰው ህይወትን ይዘምራሉ። በቀድሞ ጊዜያት የጎረቤት ሀገራት መሪዎች (ጅቡቲ፣ የመን ወዘተ…) ድሬዳዋን እየደጋገሙ የሚጎበኙበት አንዱ ምክንያት በከዚራ ጥላዎች የቀዘቀዘው የድሬ አየር ሱስ ስለሚያስይዛቸው ይመስለኛል።” የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል።

የስያሜዋ አሰጣጥ

አሁን ላይ ከዚራ በሚል ስያሜዋ የምትታወቀው የድሬዳዋ አንድ መንደር ስያሜዋን ያገኘችው ቀድመው ከኖሩባት የውጭ ዜጎች ነው። ኢትኖግራፈር አፈንዲ ሙተቂ “ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ድሬ ዳዋ” በተሰኘ መጽሐፉ እንዲህ አብራርቶታል።

“አንዳንዶች ትክክለኛው አጠራር “ገዚራ” እንጂ “ከዚራ” አይደለም ይሉናል፤ ፍቺውንም “ገዚራ” በሚለው አቅጣጫ እንድንፈልገውም ያመላክቱናል። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት “ገዚራ” በዐረብኛ “ደሴት” ማለት ነው፤ ይህም ሰፈሩ ከከተማዋ ዋነኛ ክፍል እንደ ደሴት ተለይቶ የተቀመጠ በመሆኑ የወጣለት ስያሜ ነው።

በሌላ በኩል“ገዚራ” የሚባል ሰፈር በአንዳንድ የዐረብ ከተሞች ውስጥ መኖሩ እርግጥ ነው። ዐረቦች በዚህ ስያሜ የሚጠሩት ግን ማንኛውንም ሰፈር ሳይሆን ከተሞቹን እያጋመሱ በሚያልፉ ወንዞች መሀል ባሉ ደሴቶች ላይ የተቆረቆሩ ሰፈሮችን ናቸው። ይህንን አባባል በሙሉ ልቤ እንዳልቀበል ያደረገኝ ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ይኸውላችሁ! በድሬዳዋ ይኖሩ ከነበሩት ዐረቦች መካከል ከመቶ ዘጠና እጅ የሚሆኑት የመኒዎች ነበሩ። ስለዚህ ለሰፈሩ ስያሜውን የሰጡትም እነርሱ መሆናቸው አይካድም።  ስለዚህ ትክክለኛው አጠራር “ገዚራ” ነው የሚለው አገላለጽ አልተዋጠልኝም።

 ከዚህ የተለዩት ወገኖች ደግሞ ትክክለኛው ስያሜ “ቀሲራ” ነው ይላሉ። ይህም በሰፈሩ የተገነቡትን ውብ ቤቶች ለማመልከት የተሰጠ ስም ነው በማለትም ያስረዳሉ። በርግጥም ላቅ ባለ የግንባታ ጥበብ የተገነባ ቤትን በዐረብኛ “ቀስር” ብሎ መጥራት ይቻላል። በርካታ ቤቶችንም “ቀሲራ” ማለት ይቻላል።

 ከመደምደሚያ ላይ ለመድረስ ግን ሰፋ ያለ ጥናት ማድረግን ይጠይቃል። የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ “ከዚራ” የተገኘው “ኸዲራ” ከሚለው የዐረብኛ ቃል ነው” ይላሉ። ይህም ሰፈሩን ያሳመሩትን ጥላዎች የሚያመለክት መጠሪያ እንደሆነም ይገልጻሉ (“ኸዲራ” በዐረብኛ “አረንጓዴ የሆነ” ወይንም “አረንጓዴ መልክ ያለው” ማለት ነው)። ይህንን ዕይታ ከቋንቋው አገባብ አንጻር መቀበል ይቻላል። የከዚራን ታሪካዊ ዳራ ስናይ ግን አንድ ሊታለፍ የማይቻል አጥር አለ። ከዚራን የመሰረቱት የኢጣሊያ ወራሪዎች መሆናቸው ከብዙ ምንጮች የተረጋገጠ ነው (ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ግን በስህተት “የፈረንሳይ ዜጎች ናቸው የመሰረቱት” ይላል)። “ከዚራ” የሚለው ቃል በዚያ የኢጣሊያ ወራሪዎች ዘመንም ይታወቅ ነበር። የከዚራ ጥላዎች የመጡት ግን በእንግሊዝ ወራሪዎች ዘመን ነው። “ከዚራ” የሚለው ስም ከጥላዎቹ እንኳ የቀደመ መሆኑ ሰፈሩ በጥላዎቹ ምክንያት እንዲያ ተብሎ እንዳልተጠራ ሊያስረዳ ይችላል። ጥላዎቹ በጣሊያኖች ዘመን ከነበሩ ግን “ከዚራ” የተገኘው “ኸዲራ” ከሚለው የዐረብኛ ቃል ነው የሚለውን መላምት መቀበል ይቻላል። ታዲያ የከዚራ ትክክለኛ ፍቺ ምንድነው? ለጊዜው የተቆረጠ መልስ የለኝም።” ሲል መላ ምቶቹን በዚህ መልኩ አስቀምጧል።

አፈንዲ በ"ኡመተ ፈናን- ኡመተ ቀሽቲ ዲሬ ደዋ” መጽሐፍ ላይ ሰፋ ያሉ መላምቶችን የሰጠ ሲሆን ሐሳቡ ሲጠቀለል “ከዚራ” በጥንቱ ዘመን የውጪ ሰዎች መኖሪያ ነበረች። ግሪኮች፣ ዐረቦች፣ አርመኖችና ጣሊያናዊያን በብዛት ይኖሩበት ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ እንግሊዛዊያን የሰፈሩ ዋነኛ መንደርተኞች ሆኑ። ታዲያ የከዚራ ጥላዎች መነሻም እነዚያ የውጪ ዜጎች ኃይለኛውን የድሬዳዋ ሙቀት ለመቀነስ የተከሏቸው ዛፎችና ጥላ በከተማዋ ብቻ አይወሰንም።

በከዚራ ውስጥ የኖሩት የውጪ ዜጎች ይህንን እና መሰል የራሳቸውን አሻራዎች አሳርፈዋል። ስለዚህም የከዚራን ስያሜ ረዘም ላለ ጊዜ የኖሩባቸው ሰዎች እንዳወጡላትም ይገመታል። የመጀመርያው አውጪ ማን እንደሆነ ባይታወቅም የወቅቱን ኗሪዎች ቋንቋ በመመርመር መላምት የማስቀመጡ ሂደት አሁንም አልተቋረጠም።

ከዚራ እና ኪነ-ጥበብ

የድሬዳዋን ምድር ያልረገጡ፣ በአካል ያልተገኙ ሩቅ ተመልካቾች ሳይቀሩ ከዚራን ያውቃሉ። ይህ እንዲሆን ያስቻለው ከዚራ የበርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ቀልብ በመሳቧ ነው። ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ድምጻውያን ስለ ከዚራ ጥላ አዚመዋል፣ ከዚራ ስላሳለፉት ውብ ጊዜ ዘፍነዋል፣ የከዚራ ሽርሽር ያለውን ምቾት አቀንቅነዋል። በአጠቃላይ ስለ ድሬዳዋ እንዲሁም ስለ ከዚራ ከዘፈኑ ድምጻውያን መካከል አስቴር አወቀ፣ ላፎንቴኖች፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ጸጋዬ እሸቱ፣ ምኒልክ ወስናቸው፣ አሊ ብራ፣ ሀይማኖት ግርማ፣ ነዋይ ደበበ እና ሌሎችም ወጣት እና አንጋፋ ድምጻውያን ይገኙበታል። የተስፋዬ ገሰሰ “ሽልንጌን” የተሰኘው አጭር ልብ ወለድ መሰረታቸውን የድሬዳዋ ባቡር ጣቢያን ካደረጉ ልብ ወለዶች መካከል ተጠቃሽ ነው።

አንጋፋው ገጣሚ ጸጋዬ ገብረ መድኅን (ሎሬት) “እሳት ወይ አበባ” ከተሰኘ መድብሉ ባገኘሁት ግጥም ልሰናበት።

ድሬ ዳዋ ውስጠ ደማቅ

ሽፍንፍን እንደ አባድር ጨርቅ

ብልጭልጭ እንደ ሩቅ ምስራቅ

ያውራ ጎዳናሽ ዛፍ ጥላ

ጋርዶሽ ከንዳድሽ ብራቅ

Author: undefined undefined
ጦማሪዝናሽ ሽፈራው

Zinash is Addis Zeybe's correspondent in Dire Dawa.