አዲሱ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ፈተናዎች

Avatar: Ayele Addis
አየለ አዲስጥቅምት 11 ፣ 2014
City: Bahir Darማህበራዊ ጉዳዮች
አዲሱ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ፈተናዎች

ዜጎች በማንነታቸው መፈናቀል እና መገደል፣ በዩኒቨርሲቲዎች በሚነሱ ዘር ተኮር አለመግባባቶችና ግጭቶች ሳቢያ ተማሪዎች ለሞትና ለአካል ጉዳት መዳረግ እና በመሳሰሉት ሁኔታዎች ያለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ፈተናዎች ሆነው ቆይተዋል። ጦርነት፣ የጎሳ ግጭት፣  የዘር ጥቃት፣ በታጠቁ ኃይሎች ጥቃቶችና ግድያዎች ተፈጽመዋል። የመብት ረገጣ፣ ረሐብ፣ ግዞት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሥርዓተ-አልበኝነት የቀውሱ መገለጫዎች ነበሩ።

እንደ ሪልፍ ሳምንታዊ ዘገባ መሰረት ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ በአማራ እና አፋር፣ ትግራይ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ በኒ ሻንጉል ጉሙዝን ባወደመና በሚያወድመው ጦርነት፣ ግጭት፣ የጎሳ ጥቃት ከሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ተፈናቃይ፣ እጅ ጠባቂ ሆኗል። በየስፍራው የሞተ፣ የቆሰለ፣ ሐብት ንብረቱ የጠፋበትን፣ የተሰደደውን እና የወደመውን ንብረት ቤት ይቁጠረው እንጅ ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ አይቻልም።  ምክንያቱም በጥናት ላይ ተመስርቶ የጠፋውን የሰውና የሐብት መጠን እስካሁን በትክክል የዘገበ የለም።

ኢትዮጵያ እንደ ሐገር አማራ ክልል እንደ ክልል ከገጠሙ ፈተናዎች መካከል የኑሮ ውድነት፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ የአንበጣ መንጋ፣ የኮሮና ወረርሽኝ የገደለና ያከሰረው ሰው ብዙ ነው። ከሱዳን ጋር በድንበር ግዛት ይገባኛል ሰበብ፣ ከሱዳንና ግብፅ ጋር ደግሞ በግድብ ግንባታ ምክንያት ያሉት ውዝግቦች፣ መንግሥት እንደሚለው የድንበር ግዛቷ በተለይም ሰፊ የአማራ ክልል መሬት በሱዳኖች ኢትዮጵያ ተያዞባታል።

በእነዚህ የለውጡ ፈተናዎች ውስጥ በርካታ የቤት ስራዎች ያለፈው የአማራ ክልል አዲስ መንግሥት መሰርቷል። የአዲሱ መንግሥት ምስረታ የክልሉ ነዋሪዎች እንዴት ይረዱታል? የክልሉ መንግሥት በቀጣይ አምስት ዓመታት ምን እንዲሆንላቸው ይፈልጋሉ? ለሚለው ጥያቄ የአዲስ ዘይቤ የባህርዳር ሪፖርተር አስተያየቶች ሰብስቧል።

ከጊዜ እና ከንጉሥ የተጣላች ሐገር

“ኢትዮጵያ ከንጉሷ እና ከጊዜ ጋር የተጣላች ሃገር ናት” የሚል አደገኛ አሰተያየት ይሰነዘርባታል። ይህንን የሚሉን አሳቢያን ህዝቡ በታሪኩ፡- የቀደመውን መንግሥት እያመሰገነ የአሁኑን እንደወቀሰ፤ መንግሥት፡- ራሱን እያሞገስ፤ ያለፈውን እንዳንኳሰሰ አለ። በጊዜ፣ በንጉሥ እና በህዝብ መካከል ያለው ቅራኔ ላለመታረቁ አንዱ ሰበብ የሀገሪቱ ገፅታ ነው። የአማራ ክልልን በቀድሞው አሰተሳሰብ ከፈረሰው ብአዴን፣ ከተለወጠው አዴፓ እና ከአሁኑ ብልፅግና ጋር ለውጡን በጥርጣሬ የሚያዩት በርካታ ናቸው። የለውጡን አሸናፊነት አሁንም በተለወጠ መሪ ቦታ እንኳን ቁሞ ኢህአዴግ በአዲስ ብራንድ ነው የሚሉ አልታጡም።

ሳራ ብዙ በሰጠቸው አሰተያየት “ሐገሪቱ ላይ ያለው ቀውስ በመሪዎቹ ድክመት የመጣ ነው። ዐቢይ አህመድ የጦርነቱን ከትግራይ አውጥቶ አማራ ክልል ሲያደርገው ለምን የሚል መሪ አለመኖሩ ነው አማራ ክልልን እና አዲሱን መንግሥት ፈተና ውስጥ የጣለው” ትላለች።

ምንይችል አዘዘ በበኩሉ “መታወቂያ በዝምድና፣ ቤት በዝምድና፣ የስራ ቅጥር በዝምድና አንዳችም ነገር ያለ አድሎ የሚከወን ተግባር የለም። አሁንማ ህዝቡም ለምዶታል። ጉዳይ ለማስፈፀም ሲታሰብ "ሰው አለህ?" ትባላለህ የለኝም ከሆነ “አርፈህ ተቀመጥ” የሚል ምላሽ ታገኛለህ።

የክልሉ ፈተናዎችን በተመለከተ ከአማራ ሕብረት አሰተያየታቸውን ሲሰነዝሩ ለውጡን ከፖለቲካ ውጥረት ጋር ይመስሉታል። አማራ ክልል እንደ ሀገር በአንድ ኢትዮጵያ ቢያምም ጤና የሚነሱ ጎረቤት ክልሎች ግን የፖለቲካው ውጥረት የሀገር ግንባታው ሂደት ቀን ተባባሪ ያልሆኑ እና የሽኩቻ መንስኤ ናቸው ይሏቸዋል። ለዚህም ማሳያ የሚሉት “የአማራ ክልል አጎራባች ክልሎች ትግራይ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከ250 በላይ ልዩ ኃይልና ከ150 ሺህ በላይ ሚሊሻ አሰልጥኖ በዘመናዊ ጦር ሲያስታጥቅ ኦሮምያ ከ49 ዙር በላይ በመደበኛ ልዩ ኃይልና ከ20 ዙር በላይ ኢ-መደበኛ ሚሊሻዎችን አሰልጥኖ (ይህ ቁጥር ክልሉ ያሰለጠነውን የኦነግ ሰረዊት አይጨምርም) ሲያስመርቅ አማራ ክልል በአቶ አሳምነው የሥልጣን ዘመን ጊዜ በሁለት ዙር ሰልጥነው የተመረቁ ልዩ ኃይሎችን እያሳደዱ በማሰር፣ በመግደልና በማባረር የተጠመደ ክልል ነው። ከየትኛውም ክልል በላይ ክልሉ የጦርነት ቀጠና፣ የኦነግና የህወሃት መፈንጫ የሆነን ክልል ታቅፎ እስከ ወራት ድረስ አንድም የአማራ ልጅ ወታደራዊ ስልጠናም ሆነ ትጥቅ እንደይሰጠው የተገደበ ነበር። 

የፖለቲካ ውጥረት በአጎራባች ክልሎች የሚካሄደው የጦር መሳሪያ ሽቅድድም፣ የማዕከላዊ መንግሥት የሥልጣን ሚዛን እንቅልፍ አያስከድንም። አንዱ ክልል አሸባሪ የተባሉ ኃይሎችን አቅፎ በሚስምበት ሌላው ላይ ጥቃት በሚሰነዘረብት ማስተባበያው የማይወረድ ፖለቲካ በሆኑበት ሁኔታ አማራ ክልል እንደሀገር ለመቆም ለሚደረገው ትግል የሚገዳደረው የፖለቲካ ወቅት ነው።

በባህር ዳር ዩቨርሲቲ ፕሮፌሰር አበበ ዘገየ እንደሚሉት የክልሉ ፈተናዎችን ወደ አምስት ይጠቀልሏዋል። ያልጠራው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሀገር ግንባታ ጉዞ እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ ከሚሉ ብሄር ተኮር ግጭቶችና የሚያስከትሉት የህዝብ መፈናቀል አንፃር በክልሎች መካከል ያለው አለመናበብ እና የማዕከላዊ መንግሥት ክልሎችን የሰጣቸው የጡንቻ ፉክክር አንዱ ነው። በሁለተኛነት የሚጠቅሱት አሁን ያለውን ጽንፈኛ ብሄርተኝነት ኢትዮጵያ ትቅደም ብሎ ለመመስረት ከሚታለመው ሂደት ጋር የአስተሳሰብ ለውጥ አብዮት ማምጣት ካልተቻለ እንቅፋት ነው። አገሪቱ ከውስጣዊ የፖለቲካ ውጥረትና የደህንነት ስጋቶች በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ መሰናክሎችም ያሉባት መሆኑ ለክልሉ ከወጣቱ ስራ አጥነት እና ከግጭቶች በኋላ ህዝብን የማደራጀት እና ኢኮኖሚውን የማሳደግ ስራ ፈታኝ እውነታዎች ናቸው” ሲሉ ያጠቃልላሉ።

ያልተመለሱ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች

አወቀ ማርሴ የተባሉ አሰተያየት ሰጭ እንደሚናገሩት “እጅግ በጣም የሚያሳስቡን በርካታ ነገሮች መካከል በጥቂቱ በህወሃት ኃይል ወረራ ውስጥ ያሉትን አካባቢወች ነጻ በማውጣት ሰቆቃ ውስጥ ያለ ወገናችንን ማላቀቅ እና መልሶ ማቋቋም አንዱ ነው። በጀትም እንዲያዝለት ፌደራል መንግሥቱ ላይ ጫና መፍጠር። በየሜዳው የተበተነውን ህዝብ ከመሰብሰብ የቀደመ ስራ የለም” ይላሉ።

አቶ ያሬድ አማረ በበኩላቸው “በመጀመሪያ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የወንበር ሽኩቻ ሳያሳስባችሁ የበታችነት ስሜትም ሳይጠናወታችሁ ተባብሮና ተደጋግፎ ለመስራት ቁርጠኛ ይሁኑ” ሲሉ አሰተያየታቸውን ይጀምራሉ። ልዩ ኃይልና ፋኖ የምትሉትን አደረጃጀት ለዘለቄታው ትርጉም በሚሰጥ ብሄራዊ አንድነታችንን ሊፈታተን በማይችል አደረጃጀት ወደ ፌደራል ፖሊስ አልያም ወደ መከላከያ የሚጠቃልለበት በሂደት ሁሉም ክልልሎች ከዚህ አደረጃጀት ነጻ ሆነው በባለሥልጣናት ሪሞት የሚታዘዙና የሚደጎሙ ኃይሎችን ማጥራት እንደሚገባም ያሳስባሉ። ይህም ለብሄራዊ ክብር ለአንድ ሀገር ዘብ የሚቆምን ኃይል ለመገንባት ወሳኝ ሚና ይጫወታል በማለት አፅንኦታቸውን ይገልፃሉ። “ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለመቅረጽ የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነውና በየዞን እና ወረዳ ላይ ይህን የሚቆጣጠር በቅርብ ዓመታት ማጥፋት ባይቻል ቢያንስ በአመርቂ ሁኔታ መቀነስ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት።የስርቆት ዓይነቶቹ ውስብስብና ረቂቅ ሊሆን ይችላል። በዚያው ልክ ጸረ ሙስና አሰራርን መንደፍ እና በዚያው አቅም ለመጓዝ ጥረት ማድረግ ይገባል ሲሉ አቶ ያሬድ ይገልፃሉ።

ሌላው እሳቸው በአዲሱ መንግሥት ውስጥ ትውልዱን በጥበብና በቴክኖሎጂ ከማሳደግ ባሻገር በግብረ ገብነት የታነጸ እንዲሆን መስራት። በተለይ አብዛኛው የሀገራችን ክልሎች ውስጥ የሚያድጉና የሚኖሩ ዜጎች ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በቀር ሌላውን እንደራስ አደርጎ ለመመልከት በመከባበርና እርስ በእርስ ለመረዳዳትና ተከባብሮ ለመኖር የሚያስችል ክህሎትን በእለት ተእለት ግብራቸው ውስጥ እንዲያስቡት የሚያግዙ አዋጭ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ሊተገበር የሚችልበትን ትልም መቀየስ የጥላቻውን ትርክት ሊሰብር ስለሚችል ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ጠንካራ አለት ላይ ማረፍ ጉልህ ሚና ስለሚኖረው በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

አቶ አበጀ ደጀን በአቶ ያሬድ ሃሳብ አንድ ነጥብ “ኦነግ ይህን ሁሉ አሰልጥኖ አማራ ፋኖን ያፍርስ” የሚለውን ሃሳ አይደግፉትም።   የቀድሞው የአማራ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌትነት ይርሳው በበኩላቸው ፋኖ ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቶት እና ግልፅ ርዕዩን ይፋ አድርጎ በክልል እና በየደረጃው እንዲደራጅ ይፈልጋሉ።

ሸህ ሐሚድ አበደላ በበኩላቸው አዲሱ መንግሥት ከሀይማኖት አና ከብሄር ጎጠኝነት የፀዳ እንዲሆን እንፈልጋለን የክልሉ መንግሥት ሲያስተዳድርጎጃሜውን ጎንደሬውን ወሎየውን አጋውን ቅማንቴውን በጌምድሬው ወልቃይቴውን አርጎባውን ኬሚሴውን ራያውን ዋግምራውን ሌሎችንም ያልጠቀስኳቸውን አካባቢዎች ያለ ልዮነት እንዲስተዳድር እንፈልጋለን። ሲሉ ልዮነት ማጥፋት ላይ እንዲሰራ ይጠይቃሉ።

ዮሐንስ ስንታየሁ እና ሌሎች ወጣቶች የሚያነሷው መሰሪታዊ የመለወጥ ጥያቄዎች በተለይም በወያኔ ስር የተያዙትን ቦታዎች ማስለቀቅ፣ የዞን እና የወረዳ አመራሮች ላይ ሪፎርም ቢሰራ፣ ሕገ-መንግሥቱን ማሻሻል፣ ጠንካራ የሆኑ ተቋሞች መገንባት በተለይም የፀጥታ እና ደህንነት ተቋሙ፣ የኑሮ ውድነት ማስተካከል፣ የዜጎች የመኖርያ ቤት/ የተደራጁ ማኅበራትን እልባት መስጠት በእነዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ ይስራ የሚሉ ናቸው።

አመራሮች ከህዝቡ አስተያየት በቅርብ እየተቀበሉ ከታች ወርደው ያሉትን ችግሮች ቢፈቱ ወደ ላይ እንዲወጡ የፈቀድንላቸውን ያህል በአመፅ መውረድም ስለሚኖር መሪዎች እራሳቸውን ህዝባዊ አድርገው እንዲኖሩ ይመክራሉ።

አቶ ጌትነት ስማቸው የተባሉ አሰተያየት ሰጭ በበኩላቸው በተለይ የተለያዩ አካላትን ያካተተ ውይይት ቢደረግ መልካም ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ የክልሉ መንግሥት የክልሉን ህዝብ ጥቅም ሊያስቀድምና ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ ሊሰራ ይገባል፣ ህዝቡን ለህልውና ዘመቻ ብቻ ሳይሆን ለልማት ማደራጀትና ማትጋት፣ መደገፍ ያስፈልጋል። ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የጋራ ውይይት፣ በጋራ መስራት። ወጣቶችን በልማት አደረጃጀቶች ማቀፍ፣ በተለያዩ የመንግሥት የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትና የመንግሥት አመራር ውስጥ እንደየችሎታቸው ወደፊት በማምጣት ማካተትና የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማድረግ፣ የሰላምና ፀጥታ ክፍል በሰውና በሎጅስቲክ ማጠንከር፣ በክልሉ የሚስተዋለውን ብሉሹ አሰራርና ቢሮክራሲ በማሻሻል የኢንቨስትመንትና ልማት ማዕከል እንዲሆን መሥራት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳልጥና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን አሰራርን እስከታች ድረስ መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ። የአማራን ህዝብ ባህል የሚያጎለብት ሥራ በተለይ በሚዲያው በኩል መሥራት (አሁን የሚበረታታ ሥራም ዕያየን ነው)። ከዚህ ሁሉ በፊት ግን ክልሉ ከወራሪ ነፃ መውጣት፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ማድረግና ማቋቋም፣ የወደሙ መሠረተ ልማቶች ወደሥራ ማስገባትና ታይዞ የመጣውን የኑሮ ወድነት ለማስታገስ የክልሉ መንግሥት ከህዝቡና ከፌደራል መንግሥት ጋራ በመሆን ቅድሚያ ሰጥቶ ቢሰራ መልካም ነው የሚል አስተያየት አለኝ ብለዋል።

Author: undefined undefined
ጦማሪአየለ አዲስ

Ayele Addis is an award winner Journalist, Journalism, Trainer, Researcher, and Media & Communication Development Consultancy for Thomson Reuters' Foundation, Africa News Channel, Amhara Media, and Journalists Association. Ethiopian Mass Media Action (EMMA News), ARMA Media Production.Woldia University and Bahir Dar University and founder of Journal of Ethiopian Media and Communications.