“ስኪውድ ጌም” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ለዕይታ በበቃ በ10 ቀናት ውስጥ በ90 ሀገራት ከፍተኛ ተመልካች አግኝቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓለም አቀፋዊ ዝና ተጎናጽፏል። በአሁን ሰዓት በኔትፍሊክስ ከፍተኛ ዕይታ ካላቸው ፊልሞች ቁጥር አንድ ደረጃን ይዟል።
የ“ስኪውድ ጌም” የስኬት ጉዞ የጀመረው ፊልሙ መስከረም 7 ቀን በኔትፍሊክስ ከተለቀቀ ከ4 ቀናት በኋላ ባተረፈው አስገራሚ የተመልካች ብዛት፤ እንዲሁም ከ90 በላይ ሀገራት ላይ በመታየት ያገኘው ሰፊ ተደራሽነት ነበር። አስገራሚው ነገር ገና ወር ሳይሞላው በኔትፍሊክስ ተለቀው ስኬታማ ከሆኑ ፊልሞች 111 ሚሊየን ተመልካች በማግኘት በአንደኝነት ሪከርድ መስበር መቻሉ ነው። የኔትፍሊክስ ተወካይ እንደተናገሩት የፊልሙ ስኬት ድርጅታቸው በህልሙም በእውኑም አስቦት የማያውቀው ተአምር ሆኖበታል።
ከስመ-ጥር የፊልም ተዋንያን እስከ ታዋቂ ስፖርተኞች፣ ከህፃናት እስከ አዋቂ በዓለም ዙርያ ያሉ ሰዎች ፊልሙን መነጋገሪያ አድርገውታል። ከዚህ በፊት እምብዛም እውቅና ያልነበራቸው የፊልሙ ተዋንያን ዝናቸው ናኝቷል። ከፊልሙ መሪ ተዋንያን አንዷ ‘ጁን ሆ የን’ ፊልሙ ከተለቀቀ በኋላ 14 ሚልየን የኢንስታራም ተከታዮች ማግኘት ችላለች።
የፊልሙ ትኩረት ኮርያ ውስጥ በሚገኙ በእዳ ተዘፍቀው ፍዳቸውን በሚያዩ ግለሰቦች ላይ ነው። ሰዎቹ እጅግ ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት እንደሚያስገኝ በተነገራቸው ጨዋታ (game) ላይ እንዲሳተፉ በማግባባት ወደ ድብቁ የጨዋታ ስፍራ ይወሰዳሉ። ችግረኞቹ በጨዋታው ሕግና ደንብ አምነው ጨዋታውን ይቀላቀላሉ። እጅግ ቀላል ሕጎች ያሉት የልጆች ጨዋታ በሚመስለው ውድድር ውስጥ ተሳትፏቸውን ሲጀምሩም አዝናኝ የሚመስለው፣ ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት የሚያስገኘው ጨዋታ አስደንጋጭ ፍጻሜ እንደሚያስከትል ሲያውቁ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ይገባሉ። በጨዋታው ‘መፎረሽ’ (መሸነፍ) በጥይት ተመትቶ ህይወትን ለማጣት ይዳርጋል። በመጀመሪያው ጨዋታ የ’ፎረሹት’ ከግማሽ በላይ ተወዳዳሪዎች ህይወታቸውን ካጡ በኋላ በተወዳዳሪዎቹ ስምምነት መሰረት የተረፉት ሁሉም ጨዋታውን ትተው ወደመጡበት ይመለሳሉ።
አስገራሚው ነገር ወደየቤታቸው የተመለሱት አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች በድጋሚ በቀረበላቸው ግብዣ ስህተት መስራት ወይም ‘መፎረሽ’ ማለት በጥይት ተመትቶ ሞት ወደሆነበት ጨዋታ በፈቃደኝነት ተመልሰው ጨዋታው እንዲቀጥል ይደረጋል። እንደ ተወዳዳሪዎቹ እምነት በአሸናፊነት ቃል የተገባውን ወደ 38 ሚልየን ዶላር የሚሆን ገንዘብ የሚያስገኝ ሌላ ዕድል ማግኘት አስቸጋሪ ነውና። በጨዋታው በመፎረሽ የሚጎነጩት የሞት ፅዋ ወደየቤታቸው ተመልሰው ከሚገፉት የመከራ ኑሮ ተሽሏል።
የፊልሙ ዘውግ በSurvival Drama እና Death Game ዘርፍ የሚመደብ ሲሆን በእነዚህ ዘውጎች የሚቀርቡ ፊልሞች ውስጥ ካሉት እንደ የመኖርያ አካባቢ ውድመት፣ ከአስከፊ ጦርነት በኋላ የሚፈጠር ምስቅልቅልና የምጽአት ቀን ቀውስ ዓይነት ገፊ ሁኔታዎች በተለየ መልኩ “ስኪውድ ጌም” ውስጥ ያለው ገፊ ሁኔታ “እዳ” ነው። ጨዋታው ውስጥ የሚሳተፉት ሰዎች ህልውናቸውን አሳልፈው እስከመስጠት ያደረሳቸው በየትኛውም ዓለም የሚታየው ከኢኮኖሚ ቀውስና ያልተመጣጠነ ማኅበራዊ የሃብት ክፍፍል በዝቅተኛው የሕብረተሰብ መደብ ላይ የሚከመረው የእዳ ጫና ‘ጭንቀት’ (anxiety) ነው። ጨዋታውን የፈጠሩት ዲታ ባለሃብቶችም ካፒታሊዝም የሰጣቸውን የፋይናንስ ከፍታ በመጠቀም ተጫዋቾቹ የቀረበውን ከፍተኛ ሽልማት እንዲያሸንፉ እኩል የውድድር ዕድል ፈጥረናል የሚል የራሳቸው ኣሳማኝ ምክንያት ቢኖራቸውም እውነታው ግን ተጫዋቾቹ በውድድሩ ውስጥ ወደቀጣዩ ደረጃ ለማለፍ የሚያልፉበትን ነፍስ-ውጪ፣ ነፍስ-ግቢ መከራ በመመልከት ሃብታሞቹ የሚዝናኑበት ውርርድ መሆኑ ነው።
ከዚህ ቀደም እንደ The Hunger Games ዓይነት ተመሳሳይ ዘውግ ያላቸውና በከፍተኛ የፕሮዳክሽን ጥራትና ደረጃ፣ በልብ አንጠልጣይ የታሪክ ፍሰትና በልዩ የትወና ብቃት የተሰሩ ፊልሞች ቢኖሩም የስኪውድ ጌም ዓይነት ስኬት ግን ሊቀዳጁ አልቻሉም። ታድያ የኪውድ ጌምስ ተወዳጅነት ምስጢር ምን ይሆን?
የሰው ልጅ ሁኔታ (The Human Condition)
ፊልሙን ከሌሎች እኩዮቹ በመሰረታዊነት የሚለየው ነገር በገፀ ባህርያቱና በታሪኩ ቁልጭ አድርጎ ያሳየን የሰው ልጅ ሁኔታ ነው። የሰው ልጅ ሁኔታ (The Human Condition) ፍልስፍናዊ እሳቤ ነው። ሰው በመሆንና እንደ ሰው ልጅ ህይወትን በመኖር ሂደት ውስጥ ያሉና ለማንኛውም ሰው የጋራ የሆኑ ሁኔታዎችንና ስሜቶችን ያጠቃልላል። ይህ እሳቤ ዘር፣ ቀለምና ሃይማኖት ሳይለይ የሚያግባቡና የሚነኩ የንፁህ ሰብአዊ ማንነቶችና ሁኔታዎች ጥርቅም ሲሆን በህይወት ከመቆየት ባሻገር ያሉ የህይወትንና የመኖርን ትርጉም ጥያቄዎች ለመመለስ ሰው የሚያደርገውን ጥረት የሚገልፅና የሚያብራራ ነው።
በስኪውድ ጌም ገፀ ባህርያት ላይ የምንመለከተው በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች በስልጣኔ፣ በዘር፣ በቀለምም ሆነ በሌሎች ልዩነቶች ውስጥ ቢኖሩም ሊገጥማቸውና ሊኖሩበት የሚችሉት የእዳ ጭንቀት፣ የህይወት ትርጉም ጥያቄ፣ ለህይወት ሳይሳሱ ኑሮን ለማሸነፍ የሚደረግ ትግል፣ በዘመናችን ያለው የሰው ልጅ ክብር መጉደል ወዘተ ሰው የሆነን ማንኛውንም ተመልካች የሚነካ ሆኖ እናገኘዋለን። ራሳችንን በገፀ ባህርያቱ ቦታ ተክተን ስሜታቸውንና ያሉበት ሁኔታን በሚገባ እንረዳለን። የአንድ የስነ-ጥበብ ስራ ተወዳጅነትና ዘመን ተሻጋሪነት ዋነኛው መሰረትም የእውነተኛ ህያው ስሜቶችና ሁኔታዎች ነፀብራቅነቱ ነውና።
አብዘርዲዝም (Absurdism)
ማንኛውም የስነ-ጥበብ ስራ የዘመኑ ዓይነተኛ ነፀብራቅ ነው (Zeitgeist) ይባላል። እንደ ስነ-ጥበብ የዘመኑን እውነት ሰንዶ የሚያስቀምጥ ምንም ዓይነት ስኬታማ መንገድና ዘዴ አልተገኘም። ስኪውድ ጌም ፊልምም እንደ አንድ የዘመኑን ማንነት ዕንደሚያሳይ የስነ-ጥበብ ስራ የሚወክላቸውና የሚያሳያቸው የዘመኑ መልኮች አሉ። በፊልሙ ከተገለፁ የዘመኑ ገፅታዎች አንዱም በሰዎች ስነ ልቦናዊ ማንነት ውስጥ ያለ ግጭት ሲሆን ከሁለተኛው አለም ጦርነት በኋላ በሰፊው የተቀነቀነው የ አብዘርዲዝም ፍልስፍና ይህን ሁኔታ በሚገባ የሚያሳይ እሳቤ ነው።
በአብዘርዲዝም ፍልስፍና አብዘርድ የሚባለው ስነ ልቦናዊ ስሜት የሚመነጨው ግለሰቦች ትርጉም የለሽ በሆነ አለም ውስጥ በሚፈልጉት የህይወት ትርጉም መካከል በሚፈጠረው ተቃርኖ ነው። በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ተንሰራፍተው የሚገኙ ሁለት እርግጠኝነቶች አሉ። የመጀመሪያው ሰዎች በተፈጥሯቸው ውስጥ ባለ መሰረታዊ ግፊት ተነሳስተው የህይወትን ትርጉምና ፋይዳ ለመፈለግና በዚያም ውስጥ ራሳቸውን ለማግኘት የሚያደርጉት ሙከራ ሲሆን ሁለተኛው እርግጠኝነት ደግሞ በዙሪያቸው ያለው አለም ለሰው ህይወት ያለውን ቸልተኝነትና ዝምታ መረዳት ነው። ይህ መረዳታቸው ህይወት ትርጉምና ፋይዳ እንዳለው እርግጠኛ እንዳይሆኑ በማድረግ በውስጣቸው ህልውናዊ ፍራቻ እንዲሰርፅ ያደርጋል። የአብዘርዲዝም ፍልስፍና ዋነኛ አቀንቃኝ አልበርት ካሙ እንደሚለው ይህ በትርጉም ፍለጋና በትርጉም ማጣት መካከል ያለው አብዘርድ የሚባለው ስሜትና ሁኔታ በዚህ ጊዜ ይፈጠራል። ለዚህ የተስፋ መቁረጥና ግራ የመጋባት ስሜት እጅ ላለመስጠት የሰው ልጅ ትግል ሲያደርግ ራስን ማጥፋት፣ ከህይወት በኋላ ተስፋ በሚሰጥ ኃይማኖታዊ እሳቤ ማመን እና ራሱ አብዘርድን መቀበል እንደ መፍትሄ የሚቀርቡ ናቸው። እንደ ፈላስፋው የተሻለ አማራጭ የሆነው አብዘርድን አሜን ብሎ ተቀብሎ በመኖርና ሁኔታው ላይ በማመፅ ቀስ በቀስ ባለው ሂደት የህይወት ትርጉም እየተገለጠ ይመጣል ባይ ነው።
“በስኪውድ ጌም” ውስጥ ያሉ ገፀ ባህርያት ህይወት ውስጥም ከዋናው ገፀ ባህሪ እስከ ሌሎቹ የጨዋታው ተሳታፊዎች ሁሉም በሕብረተሰባቸው ውስጥ ለህይወት ትርጉም ፍለጋ በሚያደርጉት ጥረት በእዳ ሲዘፈቁ፣ ሱሰኛና ቁማርተኛ ሲሆኑ፣ የሚወዷቸውን ሲያጡ፣ ሲከዱ፣ ሲሰደዱ የምንመለከት ሲሆን የሚፈልጉት የህይወት ትርጉም የልምዣት ሆኖባቸዋል። ከቤተሰብ ጀምረው ወደ ሕብረተሰብ ዞረው ሲመለከቱና ለነርሱ ህይወት ግድ የሌለው ዓለም እንደሆነ ሲረዱ የአብዘርድ ማንነት በውስጣቸው ይዘልቃል። ይህን ማንነት ግን አሜን ብለው ላለመቀበል በፍልስፍናው እንደ መፍትሄ በቀረበው መሰረት ህይወትን ከማጥፋት በማይተናነሰው አደገኛ ጨዋታ ውስጥ ለመግባት በመወሰን ያሉበት የአብዘርድ ሁኔታ ላይ ያምፃሉ፤ የቀረችዋን እንጥፍጣፊ የህይወት ትርጉም ፍለጋ። በፊልሙ የመጨረሻ ክፍል ላይም ሁለቱ መሪ ተዋንያን ከርቀት ጎዳና ላይ ወድቆ የሚመለከቱት ሰው በብርድ ላይ ተኝቶ ለሚያሳለፈው ስቃይ አላፊ አግዳሚው ግድ ብሎት ለእርዳታ እጁን ይዘረጋ ይሆን ብለው ሲወራረዱ ዕናያለን። ሆኖም ሁሉም ተስፋ ተሟጦ አያልቅምና ግድ የሚለው የሰው ልጅ አይጠፋም።
ካፒታሊስታዊ ማሕበራዊ መገለል (Theory of Alienation)
ሌላኛው በስኪውድ ጌም የሚገለፀው የዘመኑ መንፈስ የካፒታሊዝም ስርአት የሚፈጥረው ማህበራዊ ቀውስ ነው። ስመ ጥሩ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ፈላስፋ ካርል ማርክስ ካፒታሊዝምን የሚተችበት የመገለል ቲዮሪ (Alienation Theory) ይህን ማህበራዊ ምስቅልቅል አጠቃሎ ያቀርበዋል።
ይህ ቲዮሪ በሃብት ደረጃ በተከፋፈለ ማህበራዊ መደብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከሰብአዊ ማንነታቸው ይነጠላሉ የሚል ሲሆን በካፒታሊስት የምርት ስርዓት ሰራተኛው የራሱን ድርጊቶች ራሱ መወሰን ሰለመቻሉ፣ ከሌሎች ጋር ስላለው ግንኙነት እና በራሱ የሚመረቱትን ምርትና አገልግሎቶች ባለቤት ስለመሆኑ እንዳያሰተውል የማሰብ መብቱን ተገፎ ህይወቱና እጣ ፈንታው ላይ ያለውን ስልጣን ሙሉ በሙሉ ያጣል በሚለው ኃሳብ ላይ የተመሰረተ ነው። ሰራተኛው ራሱን የሚያውቅና የሚገዛ ነፃ ፍጡር ቢሆንም ካፒታሊስቶቹ ውጤታማና የሰራተኛውን አቅምና ጉልበት አሟጦ በመጠቀም ከፍተኛ ትርፍ እናገኝበታለን ብለው በሚያስቡት መንገድ የሰራተኛውን ተግባርና ህይወት ይመሩታል። በዚህም መሰረት የሰራተኛው የእጣፈንታና የህይወቱ ጌቶች ሆነው ይነግሳሉ።
ስኪውድ ጌም በዋነኝነት የሚተርክልንም በዚህ በካፒታሊዝም በሰከረ አለም ገፀ ባህርያቱ የባለፀጎቹ መጫወቻ አሻንጉሊት እንዴት እንደሆኑ ነው። Psychology Today የተባለው እውቅ የስነ-ልቦና መፅሄት የፊልሙ ተወዳጅነት አንደኛው ምስጢር ያነሳው ካፒታሊስታዊ ማህበራዊ ትችት ነው በማለት እንዲህ ይገልፀዋል፣ “የስኪውድ ጌም ተወዳጅነት መሰረቱ ስነ-ልቦናዊ ነው ማለት እንችላለን። የፊልሙ ዋነኛ መነሻ ኃሳብ በውድድር የሰከረ ካፒታሊስታዊ ማህበረሰብ ላይ ትችት መሰንዘር ነው። ድሆቹ የሞት አደጋ ባንዣበበት ጨዋታ ውስጥ ህልውናቸውን ለማስቀጠል ይወዳደራሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው የናጠጡትን ባለፀጎች ለማዝናናት ነው። ብዙ ሰዎች ጭንቀት ውስጥ በተዘፈቁበት፣ በተንሰራፋው ማህበራዊ ኢ-ፍትሃዊነት ባዘኑበት፣ በስኬት ሚዛን እየተዘወረ ያለው ማህበረሰብ እንቆቅልሽ የሆነባቸው ምስኪኖች በበዙበት በዚህ ዘመን ስኪውድ ጌም ያነሳው በካፒታሊዝም ጫካ ውስጥ ያለውን ማህበራዊ ኢ-ፍትሃዊነት የሚሸነቁጥ ጭብጥ በብዙሃኑ ተወዳጅ እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም።”
ፊልሙ ጨዋታ በሚመስለው ታሪኩ የሚያሳየን እነዚህን መራር የህይወታችንን እውነታዎች ነው። ከታች ያለው ድሃ ማህበረሰብ የእጣፈንታው ቁልፍ ያለው በካፒታሊስቶቹ እጅ ነው። ድሃው የካፒታሊስቶቹ መደበሪያ ነው። ካርል ማርክስ በመገለል ቲዮሪው እንደሚያስቀምጠው ሰራተኛው ደሃ መደብ ሰብአዊ ክብሩ የተገፈፈ ዋጋው ወደቁስነት የወረደ እቃ ሆኗል፤ ያለንበት ዘመን ሀቅም ይህ ነው። በፊልሙ መጨረሻ ላይ የጨዋታው ዋና የበላይ ጠባቂ ለአሸናፊው ዋና ተዋናይ እንደሚነግረው የጨዋታው ተሳታፊዎች ውድድሩን ለፈጠሩት ኃብታሞች ውርርድ እንደሚደረግባቸው ፈረሶች ናቸው።
ከላይ በተገለፁት እውነታዎች ውስጥ እየተንሸራሸረ በሚዘልቀው ስኪውድ ጌም ፊልም ውስጥ እንደ ተመልካች መንታ እይታ ይኖረናል። በተወዳዳሪዎቹ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ አብረናቸው እንጨነቃለን፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ልክ እንደ ባለኃብቶቹ ስሜት አልባ ሆነን ጨዋታውን እንመለከታለን። ይህ የስኪውድ ጌም ልዩ የታሪክ ቅንብር ፈጠራ ወደፊትና ወደኋላ እየሄድን በፊልሙ ውስጥ በቀረበው ማህበራዊ ኃሳብ ስሜታችን ተይዞ፣ እንዲሁም በታሪኩ ፍሰት ተወስደን እስከመጨረሻው እንድንጓዝ ያደርገናል።