በኢትዮጵያ ደረጃ የተማሪ እና የመጽሐፍ ጥመርታ አንድ መጽሐፍ ለሁለት ተማሪ መድረሱን ከምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሁኔታው በግል ትምህርት ቤቶች ያለው አካሄድ የተለየ ነው። ባለድርሻ አካላቱ እንደሚናገሩት መንግሥት መጽሐፍቱን ስለማያቀርብ ከፍተኛ ጫና በዘርፉ ተዋንያን ላይ እየደረሰ ነው።
የትምህርት ጥራትን እንደሚያስጠብቁ በዩኔስኮ ከተቀመጡ 5 ነጥቦች መካከል የትምህርት ግብአቶችን ማሟላት አንዱ ነው። ከግብአቶቹ መካከል የመማርያ መጻሕፍት ይገኛሉ።
ረቂቅ መስፍን የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት። ያገኘናት ከጎሮ መሰናድኦ ት/ቤት ስትወጣ ነው። ለቂቅ እስከ 10ኛ ክፍል ያለውን የትምህርት ጊዜ የተማረችው በግል ት/ቤት ውስጥ ነው። በግል ትምህርት ቤቶች በመማር ላይ በነበረችበት ጊዜ እና አሁን በመንግሥት ት/ቤት ውስጥ ስትማር ያለውን ልዩነት ስታነጻጽር “አሁን ሁሉም መጸሕፍት አሉኝ። ምንም አልቸገርም። በፊት የቤት ስራ ሲሰጥ በየጎረቤቱ ልመና ነበር” ትላለች።
ተማሪዎች ካለው የመጽሐፍ ውድነት እና የቤተሰብን አቅም በማገናዘብ የተለያዩ አማራጮች እንደሚጠቀሙ ትናገራለች። ለአብነትም የሶፍት ኮፒ መጻሕፍት ትጠቀም እንደነበር ትናገራለች። "የራሴ ስልክ ስላልነበረኝ የምጠቀመው በእናቴ ስልክ ነበር። በሶፍት ኮፒውም መምህራን ገጽ እና መልመጃ ቁጥር ነግረው የሚሰጠው የቤት ስራ እና ያለው መረጃ ስለሚጣረስ ብዙ ጊዜ ያሳስተኝ ነበር።" የምትለው ረቂቅ መስፍን ለመጨረሻ ጊዜ የገዛቻቸው ሦስት መጽሐፍት ከዋጋ ተመናቸው ውድ የሚባል ባይሆንም ማግኘት አዳጋች እንደነበር አስታውሳለች።
"ት/ቤቱ በአንድ ወቅት መጻሕፍቱን ፎቶ ኮፒ አንስቶ በመጠረዝ ለሽያጭ ያቀርብ ነበር። ከቆይታዎች በኋላ ግን ሽያጩ ቀርቶ ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ ብቻ እንዲቀመጥ ተደረገ” የምትለው ተማሪዋ የመማሪያ መጻሕፍቱ እንደልብ አለመገኘታቸው ተማሪው ላይ የስነ-ልቦና ጫና እንደሚያሳድር ትናገራለች።
ጎያስ አጠቃላይ የተባለ የግል ትምህርት ቤት በመማር ላይ የምትገኘው ፌኔት ደጀኔ በበኩሏ “ምንም ዓይነት ቴክስት ቡክ የለኝም። ትምህርት ቤታችንም አይሰጠንም። የምንጠቀመው በሶፍት ኮፒ ነው” ትላለች። ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዞ ወደ ትምህርት ቤት ግቢ መግባት ስለማይፈቀድ የክፍል ስራ መስራት ተቸግራለች። የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ፌኔት "ስልክ የሌላቸው ተማሪዎች ከሰፈር ጓደኞቻቸው ለመጠየቅ ይገደዳሉ አልያም ይገዛሉ። ገበያ ላይ ዋጋቸው ውድ ነው አምና አማርኛ መጽሐፍ 150ብር ብር ጓደኛዬ ገዝታለች" ብላለች። ፌኔት በመጽሐፍ እጥረቱ ምክንያት መምህራኑ በቋሚነት ማስታወሻ እንደሚያጽፏቸው ትናገራለች።
ከፌኔት ደጀኔ ወላጅ ጋር ባደረግነው ቆይታ “ከመደበኛ መማሪያ መጽሐፍት ተጨማሪ የፈተና ጥያቄዎችን እና ሌሎች ማብራሪያዎችን የያዙ መጻሕፍት ለተማሪዎቹ ያስፈልጋሉ። እንደኔ ሦስት ልጅ ለሚያስተምር ወላጅ ከባድ ነው” ብለውናል።
ልጇን በቬራ ት/ቤት የምታስተምረው መኪያ ኑሪ ባለፈው ዓመት ሁለተኛ ክፍል ለሚማር ልጇ 4 መጽሐፍት በ300 ብር መግዛቷን ታስታውሳለች። "ልጅህ ደስተኛ ሆኖ እንዲማር ብለህ ትከፍላለህ እንጂ ዋጋው ውድ ነው።" የምትለው መኪያ ትምህርት ቤቱ ቢያመጣውም በመጻሕፍት መደብር ከሚሸጥበት ዋጋ ምንም ለውጥ እንደሌለውና ከመንከራተት ብዬ ነው የምገዛው ትላለች።
መምህር ለሜሳ በላይ በአዳማ ናፍያድ ት/ቤት የቴክኒካል ድሮዊንግ መምህር ነው። በግል ት/ቤቶች ውስጥ የመጻሕፍት አለመኖር ወይም እጥረት በተማሪዎቹ እና በመምህራን ተነሳሽነት ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ይናገራል። "መጽሐፍ አለመኖር ከሚጎዳቸው መሃከል መምህራንም እንገኝበታለን። መጽሐፉ ቢኖር በቀላሉ ማስረዳት፣ ጊዜ መቆጠብ እና ተማሪዎችን ለመጠየቅ የሚውለውን ጊዜ ሰሌዳ ላይ እየጻፍን እንድናሳልፍ ያደርገናል።" የሚለው መምህሩ የሚያስተምረው ትምህርት በብዛት ንድፎች እና የምስል መግለጫዎች ስለሚበዙበት በቀላሉ ለማስረዳት አዳጋች እንዳደረገበት ይናገራል። ብዙዎቹ የመማርያ መጽሐፍ ስለማይኖራቸው ኮፒ ቤት አጫጭር ኖቶች እና የቤት ሥራዎች እናስቀምጣለን። ይህ ደግሞ ከፍለው የሚማሩ ተማሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ት/ቤቱ ብዙ የክፍያ ወጪያቸውን ሸፍኖ ሚያስተምራቸው ተማሪዎችንም ይጎዳል።
"አንድ ባልደረባ ነበረችኝ። አርብ የኖት ቀን ነው ብላ በጠዋት መጥታ ሁለት ሰሌዳ ሞልታ ጽፋ ኖት ታሶስዳለች። ከዛን ከሰኞ እስከ ሐሙስ ደግሞ ታብራራለች የችግሩ ጥልቀት ምን ያክል መምህራኑን እንዳስቸገረ ይናገራል። በተለይም የማኅበራዊ ሳይንስ እና ቋንቋ ትምህርቶች ላይ እንደሚከፋ ይናገራል። በዚህ ሁኔታ ተማሪዎች ኖት በመውሰድ ስለሚደክሙ ለጥናት ይሰላቻሉ።
በመጽሐፍ አቅርቦት ጉዳይ ያነጋገርናቸው የኤክሴል አካዳሚ ርዕሰ መምህር ሰለሞን ጎንፋ "ቤተሰብ ወደ ግል ትምህርት ቤት ሲመጣ መጽሐፍ ማሟላት እንዳለበት አምኖ ነው። ተማሪዎች መጽሐፍ አሟልተው ይገኛሉ።" የሚሉት ርዕሰ መምህሩ የመጽሐፍት መወደድ መኖሩን እንደሚያውቁ አንስተው ለግል ተማሪዎችም መጽሐፍ የማግኘት እድላቸውን ቢያሰፉ እንደማንኛውም ሀገር ተረካቢ ዜጎች ትርፉ የሁሉም ነው ይላሉ።
"በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፈን እንደተቋም የተሻለ ውጤት እያመጣነው። ከእነኚህ አንዱ የመማሪያ መጽሐፍት በቀላሉ አለመገኘት ነው።" የሚሉት ርዕሰ መምህሩ ከዚህ ቀደም በት/ቤቶች እንቅስቃሴ ተጀምሮ ሳይሳካ እንደቀረ መስማታቸውን ነገግረውናል።
የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት የትምህርት ባለሙያ አቶ ሀብታሙ መግራ በግል ትምህርት ቤቶች የመጻሕፍ አቅርቦት ጉዳይ ላቀርብልናቸው ጥያቄ "የዞኑ የስራ ኃላፊነት የመማር ማስተማር ስነ-ስርዓትን መቆጣጠር፣ የትምህርት ደረጃዎችን መቆጣጠር ነው። በመማሪያ መጻሕፍት ጉዳይ እኛ ከማስተባበር የፍላጎት መጠን መግለጫ ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ከመላክ ውጪ ሥልጣን የለንም።” የሚሉት ባለሞያው ችግሩ ባስ ሲል ለግል ትምህርት ቤቶቹ መምህራን ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ መጽሐፍ ልናውስ እንችላለን እንጂ ከዚህ የበለጠ ማድረግ አንችልም” ብለዋል። የመጻሕፍትም ሆነ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮቾን እንዲያስፈጽም የተቋቋመ ማኅበር አላቸው። ማሳተምም ሆነ መንቀሳቀስ ያለበት በዚህ ማኅበር ነው።" የሚሉት ባለሞያው በመንግሥትም ሆነ ለግል ት/ቤቶች መጽሐፍ አቅርቡ የሚል አቅጣጫ እንደሌለ ገልጸዋል።
የሆሊኤንጅልስ ት/ቤት ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት ኤርሚያስ…. እንደነገሩን የመጽሐፍት ችግርን ለመቅረፍ ከኦሮሚያ የግል ት/ቤቶች ማህበር ጋር በመነጋገር እየሰሩ እንደሆነና ከ30 ብር እስከ 100 ብር ድረስ ለተማሪዎች እያቀረቡ እንደሆነ ነግረውናል። "ማህበሩ በአዳማ ተወካዩ በኩል ለቀጣይ ዓመት ምን ያክል እንደምንፈልግ ብዛት እና የክፍል ደረጃውን እንገልጻለን። ቅድሚያ ከፍለን እንጠብቃለን። " ያሉት ርዕሰ መምህሩ በሌሎች ትምህርት ቤት እንደሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ እንደማያደርጉም ይናገራሉ። "ተጨማሪ የምናስከፍለው መጽሐፉን ለማጓጓዝ የወጣውን ወጪ ብቻ ነው።" የሚሉት መምህር ኤርሚያስ ችግሩን ለመቅረፍ ለተቀመጠው መፍትሔ የሁሉም ት/ቤቶች አመራሮች ቁርጠኛ ሆነው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።