ጥቅምት 10 ፣ 2014

በጫት ልጅነታቸውን የተቀሙ ታዳጊዎች

City: Bahir Darማህበራዊ ጉዳዮች

በግብርናው መስክ ታዳጊ ህፃናት በጫት ለቀማ ስራ ተሰማርተው እየደረሰባቸው ያለው የጉልበት ብዝበዛ ጉዳት ስር የሰደደ ነው።

Avatar: Ayele Addis
አየለ አዲስ

Ayele Addis is an award winner Journalist, Journalism, Trainer, Researcher, and Media & Communication Development Consultancy for Thomson Reuters' Foundation, Africa News Channel, Amhara Media, and Journalists Association. Ethiopian Mass Media Action (EMMA News), ARMA Media Production.Woldia University and Bahir Dar University and founder of Journal of Ethiopian Media and Communications.

በጫት ልጅነታቸውን የተቀሙ ታዳጊዎች

በአማራ ክልል በዘንዘልማ፣ እንፈራንዝ ቀበሌዎች፣ ደራ፣ ባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ እና አካባቢው በስፋት የህፃናትን ጉልበት ብዝበዛ የሚዳራጉ ታዳጊ ህፃናት በርካታ ናቸው። በተለይም በግብርናው መስክ ታዳጊ ህፃናት በጫት ለቀማ ስራ ተሰማርተው እያደረሰባቸው ያለው ጉዳት ሰፊ ነው።

በትናንሽ ጣቶቻቸው ጫት የሚለቅሙት ታዳጊ ህፃናት ከሌሊቱ 8:00 ከእንቅልፋቸው ይነሳሉ። ሰዓቱ የኤሌትሪክ መብራት በሌለባቸው ገጠራማ አካባቢዎች አስፈሪ የሚባል ጨለማ ያለበት ጊዜ ነው። ሕጻናቱ በሌሊት ጨለማ፣ በጨረቃ ብርሃን የቆረጡትን የጫት ምርት በፍጥነት ወደ ገበያ ለማድረስ ዘወትር ትጋት ላይ ናቸው። የጸሐይዋ ሙቀት ከሮ ቅጠሉ ሳይጠወልግ ወደ ተጠቃሚው እንዲደርስ ይጣደፋሉ። በዚህ ሳቢያ ታዳጊ ህፃናት እና ወጣቶች በጫት ቆራጭነት ብቻ ሳይሆን በሱስ ተጠቅተው ከህይወት ጎዳና እየወጡ ስለመሆኑ ነገሬ ብሎ ያስተዋለ ስለመኖሩ ያጠራጥራል።

የሕጻናቱ ወላጆች በሥራ የሚያግዟቸው፣ በኢኮኖሚ የሚደግፏቸው፣ የኑሮን ሸክም የሚያቀሉላቸው ልጆች በመውለዳቸው መደሰታቸውና እንደ ትክክለኛ ነገር መመልከታቸው የጉልበት ብዝበዛው ስር የሰደደ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል።

ከእነዚህ ህፃናት መካከል የ9 ዓመቱ ታዳጊ ገብሬ ቢረሳው ከሌሊት እስከ እኩለ ቀን የጫት ቀንበጥ በመቀንጠስ ያሳልፋል። ጫት ለቅሞ ለነጋዴዎች ማስረከብ ገንዘብ የሚያገኝበት ሥራው ነው። ከዚህ ከባድ ሥራው በኋላ ትምህርት ቤት የሚጓዘው ታዳጊ ዘወትር በአርፋጅ መዝገብ ላይ እንደተመዘገበ ነው። የልጅነት ጣዕሙን ሳይጨርስ የአዋቂነት ሸክም ወድቆበታል።

የታዳጊው አባት አቶ ቢረሳው ልየው “የልጄ ገቢ ጥሩ ነው። ሰርቶ ቤቱን እየደጎመ ነው። ልጆቻችን እኛን ማገዛቸው የወረደ አረፈ እንደሚባለው ነው” ይላሉ። አባት ቢረሳው የልጃቸው በውድቅት ሌሊት ወደ ስራ መሰማራት ቢከብዳቸውም በአነስተኛ የእርሻ ማሳቸው ብቻ ቤተሰባቸውን ሊያስተዳድሩ እንደማይችሉ ይናራሉ።

የ8 ዓመቱ ታዳጊ አበባው እንደሚለው ከሌሊት እስከ እኩለ ቀን ድረስ ባለው የሥራ ጊዜው እስከ ሶስት ኪሎ የሚደርስ ጫት የመቁረጥ ግዴታ አለበት። ትምህርት ማርፈድ እና መቅረት የተለመደ ነው። ትምህርቱም በጣም ከባድ ሁኖበታል። የቀኑን ግማሽ ክፍለ ጊዜ በማንቀላፋት ማሳለፉ፣ ወደ ቤት እንደተመለስም ማለዳ ለመንቃት በፍጥነት መተኛቱ ለትምህርቱ የተሰጠው ትኩረት ማነሱን ያሳያል።

የ11 ዓመቷ ጥበበ ቤት ውስጥ ከሚጣልባት ኃላፊነት እንጨት ለቀማ እና የቤት ስራውን ማገዝ በተጨማሪ የጫት ቆረጣው ስራ እስከ 1,300 ብር እንድታጠራቅም አርጓታል። ይህ ብር ለሷ ትልቅ እና ጥሪት የመቋጠር ያህል የሚታይ ምሳሌ ነው። እሷም እንደ እኩዮቿ ትምህርቷን ሰውታ ጫት ቆረጣውን በትጋት እየሰራች ነው።

የታዳጊው ገብሬ እናት ወ/ሮ ሸጋየ ባያብል ታዳጊው ልጃቸው ጓዳቸውን የሚሸፍን፣ የገበያ ገንዘብ የሚያመጣ እጁን የሚጠብቁ አንዱ የገቢ ምንጫቸው ነው። ብዕር በሚይዘበት እጁ የጉልበት ሰራ ውስጥ የገባው ታዳጊ ሳንቲም ማገኘቱ ከቤተሰቦቹ ሞራል ብርታት እንጅ ነቀፌታ አላመጣበትም። ወ/ሮ ሸዋዬ ልጃቸውን ትምህርት ቤት ያልላኩበትን ምክንያት ሲጠየቁ “ትምህርቱ የት ይሄድበታል” በሚል ጥያቄ አዘል ምላሽ ያስቀድማሉ።

“ተምረውም፣ ተመርቀውም እዚሁ እኛ ካልተማርነው ጋር ነው ያሉ። ያው መጨረሱ አይቀር” ብለውኛል።

ይህንን የሚያረጋግጡት መምህር ታምራት ፈረደ የእንፍራንዝ 1ኛ ደረጃ ርዕስ መምህር ናቸው። “ተማሪዎች መፍዘዝ፣  ሰውነታቸው መዛል፣ የንቁ ተሳትፎ እና ከፍተኛ የሆነ የትምህርት ማቋረጥ፣… ተዘውታሪ የተማሪዎች ችግር ነው” ይላሉ። ወደፊትም በታዳጊዎች የሞራል እና የስብዕና ጉዳይ ራሱን የቻለ ችግር ይፈጥራል የሚሉት ርዕሰ መመህሩ ህጻናቱ ከጫት ቆራጭነት ወደ ሱሰኝነት የማደግ እድላቸው ሰፊ መሆኑ ያሰጋቸዋል። ርዕሰ መምህሩ በተጨማሪም ሕጻናቱ እንደ ልፋታቸው ተመጣጣኝ ክፍያ አያገኙም ብለዋል።

የወረዳው ሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወሰን መላሽ “የግንዛቤ ስራ መስራት ይጠበቅብናል። ለአንድ ኪሎ 30 ብር ጫት ክፍያ ከሌሊቱ 8፡00 እስከ ቀኑ 5 ስዓት ሰብስበው የሚያገኙት ገንዘብ ይሄነው ተብሎ ለውጥ የሚያመጡበት ሳይሆን ወደፊት ራዕያቸውን የሚያጨልም እና መሰረታቸውን የሚዲያበዝዝ ነው የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል።

አርሶ አደር አዲሱ ጌጡ፤ ጫት አልሚ አርሶ አደር ናቸው። የልጆችን በጫት ለቀማ ስራ መሳተፍ በበጎ የማይመለከቱት ሲሆን “ድሮ አምስት ብር ነበር አሁን ግን ተሻሽሎ 30 ብር ለኪሎ ቆረጣ ክፍያ አድርሰነዋል” ይላሉ። ክፍያው ጨምሯዋል ሲሉ ህፃናት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሩ ለምን አቀዋቂዎችን በዘርፉ እንዳላሰማሩ ጠይቀናቸው ህፃናት ጣቶቻቸው ቀጫጭን እና ፈጣን ሲሆን በቀላሉ ተሽሎኩልከው ለመልቀም ከአዋቂዎች የተሻለ ምርታማ መሆናቸውን ይናገራሉ። አርሶ አደሩ ከ10 ዓመት በላይ የሆናቸው ሁሉ ሌሊቱን በባትሪ ብርሃን ታግዘው ከአውሬ ጋር ተጋፍጠው በአሰፈሪው ሌሊት ጸሐዩ ሳይከር፣ ሙቀቱ ሳይበረታ፣ ጫቱ ሳይጠወልግ ለማድረስ የሚታትሩት ህፃናት፣ ድካም ያዛለቸውን ሰውነት ይዘው ትምህርት ቤት ከመሄድ ይልቅ ማቋረጥ እጣፈንታቸው መሆኑን ግን አልካዱም።

አስከፊ የህፃናት ጉዳበት ብዝበዛ /worest form of child labour/ በተመለከተ አቶ አጥናፉ ሲገልፁ በተለይም ህፃናት ለወታደርነት በመመልመል ለጦርነትና ለግጭት የማሰለፍ፣ ለወሲብ ንግድና ወሲብ ቀስቃሽ ለሆኑ ትይንቶች የማሰማራት፣ ህፃናትን በዕፅ ማምረትና ማዘዋወር ሥራ ማስማራት፣ በጤና፣ ደህንነትና ሞራል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ፣ ህፃናትን በባርነት ይዞ በግዳጅ ሥራ ማሰማራት፣ ወዘተ… የሚሉትን ያካትታል። 

የህፃናት ጉልበት ሥራ (child labour) ምንድን ነው? የህፃናት የጉልበት ስራን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡን የአማራ ክልል ሰራተኛ እና ማኅበራዊ  ጉዳይ ቢሮ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ አጥናፉ በላይ እንደሚት “የህፃናት ጉልበት ሥራ ማለት የዝቅተኛ ክፍያ ለረዥም ሰዓት የሚከናወን፣ የብዝበዛ ባህርይ ያለውና የቅጥር ግንኙነት የሚንጸባረቅበት፣ ለተለያዩ አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊና ፆታዊ ጥቃትና በደል የሚዳርግ፣ በወላጆች (በቤተሰብ አባላት) የቅርብ ድጋፍ (እገዛ) ቤት ውስጥ የሚከናወንና የቅጥር ግንኙነት የሚንፀባርቅበት ሥራ ነው።

አስከፊ የህፃናት ጉልበት ሥራ በተመለከተ የወጡ ህግጋቶች  

በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9/4 ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል  ናቸው። ሀገራችን ከአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ጋር የተያዙ 22 የሚደርሱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ፈርማለች ከእነዚህ መካከል 8 ዋና ዋና  (መሰረታዊ) ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ይገኙበታል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት በአንቀፅ 36/1/መ/ ጉልበቱን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣ በትምህርቱ፣ በጤናው፣ በደህንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሥራዎች ከመስራት የመጠበቅ፣ የወላጆቹን ወይም የአሳዳጊዎችን እንክብካቤ የማግኘትና በህይወት የመኖር መብት ይደነግጋል። በአንቀፅ 18/1/2/ና/3/ በሰው መነገድን በባርነት መያዝን እና ግዴታ ለማሟላት  እንዲሰራ ያለመገደድ መብት ይሰጣል።

በወንጀል ሕጉ አንቀጽ  525 መርዛማ ወይም የናርኮቲክ  መድሀኒቶችን   ወይም ዕፆችን ማምረት፣  መስራት፣  ማዘዋወር  ወይም  መጠቀም እና በአንቀፅ  525 (2) (ሐ) ወንጀለኛው  ወንጀሉን  የፈጸመው ሕፃናት ለወንጀል  አፈጸጸም መጠቀምያ  በማድረግ  እንደሆነ  ቅጣቱ  ከአስር  ዓመት የማያንስ ጽኑ እስራት…  አንቀጽ 596 ሰውን በአገልጋይነት መያዝ ሌላውን ሰው አስገድዶ በተያዥነት የያዘ… በጉልበቱ የተገለገለና ድርጊቱ በህፃናት ላይ ከሆነ ከ10-20 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲሁም ከአንቀጽ 635-637 ሴቶችንና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ለዝሙት አዳሪነት በማቃጠር መነገድ/ በህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የተመለከቱ ቅጣቶች ይዘው እናገኛቸዋለን።

በአሰሪና ሠራተኛ ሕግ እና የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ከአንቀጽ 89-91 ለወጣት ሠራተኞች (እድሜ 15 የሞላቸው 18 ያልሞላቸው) ጥበቃ የተመለከተው ከ15 ዓመት በታች መቅጠር ክልክል መሆኑ፣ ከ18 ዓመት በታች በአደገኛ ሥራዎች መቅጠር፣ በቀን ከ7 ሰዓት በላይ፣ የትርፍ ሰዓት ስራ፣ በበዓላት እና በዕረፍት ቀናት፣ የለሊትና የትርፍ ሥራ እንዳይሰሩ ጥበቃ ያደርግላቸዋል። ለወጣት ሰራተኞች የተከለከለ ስራ ዝርዝር መመሪያ 2005 ዓ.ም. ህፃናትን ከአደገኛ የስራ ዘርፎች ለመጠበቅ የወጣ ድንጋጌ ያለ ሲሆን አሁንም ለማሻሻል በሂደት ላይ ነው።

የዓለም ሥራ ድርጅት  2017 እ.አ.አ ያወጣው መረጃ ዕንደሚያሳየው  በዓለም አቀፍ ደረጃ እድሜቸው  ከ5-17 የሆነ 151 ሚሊየን ህፃናት በጉልበት ሥራ ተሰማርተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 72.5 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ለደህንነታቸውና ለጤንነታቸው እጅግ በአደገኛ (ደህንነታቸው፣ ጤንነታቸው እና ሞራላዊ እድገታቸው በአደጋ ውስጥ ያለ) ሥራ ተሰማርተው ይገኛሉ።

በ2015 እ.አ.አ ስለ ህፃናት ጉልበት ብዝበዛ በኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታትስቲክ ኤጀንሲ እና የዓለም ሥራ ድርጅት የተጠና ጥናት እድሜቸው 5-17 ከሆኑ ህፃናት 51% በተለያየ የኢኮኖሚ ዘርፍ በጉልበት ሥራ የተሰማሩ ሲሆን 64% በአማራ ክልል 54.4% በኦሮሚያ ክልል ይገኛሉ። 89.4% በግብረና ሥራ (እርሻ፣ ደን ልምት እና በዓሣ ማስገር) ላይ የተሰማሩ ናቸው።

የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ከተስፋፋባቸው ሐገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት። እድሚያቸው 5-17 የሆነ 28% ያህሉ ሕጻናት ወንዶች ለጉልበት ብዝበዛ በተጋለጡ ሥራዎች ተሰማርተዋል። 18.2% የሚሆኑት ሴት ሕጻናትም የብዝበዛው ተጠቂዎች ናቸው። ጉዳዩን በክልሎች ደረጃ ከፋፍለን ስንመለከተው ደግሞ አፋር 31.3% አማራ 30.4% ድሬዳዋ 4.7% አዲስ አበባ 3.6% በመቶ በመያዝ በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል።  

ለደህንነትና ጤንነት በአደገኛ በሆነ ሥራ ከተጋለጡት ህፃናት መካከል 87% የሚሆኑት በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆኑ በገጠር 91.4% በከተማ 35.2 % ናቸው። ከህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ስርጭት አኳያ አማራ ክልል 33.3%፣ አፋር 31%፣ ሶማሊ 28.1%፣ ኦሮሚያ 27.7% እና የትግራይ 26.8% ሲሆን ዝቅተኛ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ የተመዘገበው አዲስ አበባ 1,133,274 ህፃናት 3.7% እና ድሬደዋ ከ180,731 4.9 % ናቸው። 

የዓለም ሥራ ድርጅት  2017 እ.አ.አ ያወጣው መረጃ ዕንደሚያሳየው  በዓለም አቀፍ ደረጃ እድሜቸው  ከ5-17 የሆነ 151 ሚሊየን ህፃናት በጉልበት ሥራ ተሰማርተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 72.5 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ለደህንነታቸውና ለጤንነታቸው እጅግ በአደገኛ (ደህንነታቸው፣ ጤንነታቸው እና ሞራላዊ እድገታቸው በአደጋ ውስጥ ያለ) ሥራ ተሰማርተው ይገኛሉ። 

በ2015 እ.አ.አ ስለ ህፃናት ጉልበት ብዝበዛ በኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታትስቲክ ኤጀንሲ እና የዓለም ሥራ ድርጅት የተጠና ጥናት እድሜቸው 5-17 ከሆኑ ህፃናት 51% በተለያየ የኢኮኖሚ ዘርፍ በጉልበት ሥራ የተሰማሩ ሲሆን 64% በአማራ ክልል 54.4% በኦሮሚያ ክልል ይገኛሉ። 89.4% በግብረና ሥራ (እርሻ፣ ደን ልምት እና በዓሣ ማስገር) ላይ የተሰማሩ ናቸው።

አስተያየት