መስከረም 27 ፣ 2014

አደገኛው የ“ካናቢስ” ተጠቃሚ ወጣቶች መስፋፋት

City: Adamaጤናመልካም አስተዳደር

ቁማርን ጨምሮ ለአስካሪና አደንዛዥ እፆች የተጋለጡ የአዳማ ወጣቶች ቁጥር ከእለት ተእለት ቢያሻቅብም ጉዳዩን ነገሬ ብሎ ተመልክቶ ችግሩን ሊቀርፍ የተነሳ የመንግሥት አካል ዐይታይም።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

አደገኛው የ“ካናቢስ” ተጠቃሚ ወጣቶች መስፋፋት

አዳማ ከተማ ከአጠቃላይ የኗሪዎቿ ቁጥር ሲሶ ያህሉ ወጣት እንደሆነ አጥኚዎች ይገምታሉ። የጤናማ መዝናኛ እና የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ስፍራዎቿ የወጣቶቿን ብዛት ያገናዘበ እንዳልሆነ ተደጋግሞ ተነስቷል። ቁማርን ጨምሮ ለአስካሪና አደንዛዥ እፆች የተጋለጡ ወጣቶቿ ቁጥር ከእለት ተእለት ቢያሻቅብም ጉዳዩን ነገሬ ብሎ ተመልክቶ ችግሩን ሊቀርፍ የተነሳ የመንግሥት አካል ዐይታይም።  

በስያሜያቸው እና በተጠቃሚዎቻው ቁጥር ከኢትዮጵያውያን ሱሰኞች ሩቅ የነበሩት አደንዛዥ እጾች ቅርብ ለመሆናቸው ማሳያ የሚሆኑን የእፆቹ ጠረን “የተለመደ ሽታ” መሆኑ ነው። ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የጋራ መኖርያ ቤቶች፣ መዝናኛ ስፍራዎች እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ የሚያውደው “የተለመደ ሽታ” የወጣቶች የሱሰኝነት ደረጃ እንደ ጫት፣ ሲጋራና አልኮል ባሉ ማኅበራዊ አደንዛዥ እጾች ብቻ አለመገታቱን ማሳያ ነው። 

ስሙን በማንገልጸው ዩንቨርሲቲ ተማሪ የሆነው ወጣት “ብሎክ ውስጥ ፕሮክተሮች ስለማይኖሩ በዶርሞች ውስጥ እና በመጸዳጃ ቤቶች ሲጋራም ሆነ ጋንጃ ሲጨስ ከልካይ የለም። ለዚህም በየቀኑ በጽዳቶች ተጠርጎ የሚወጣው የሲጋራ እና የወረቀት ቁርጥራጭ ምስክር ነው” ይላል። 

የካናቢስ እና ሌሎች ሱሶች ተጠቃሚነት በሴት ተማሪዎችም ዘንድ የተለመደ ተግባር ሆኗል። የ2013 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎችና የተማሪዎች ሕብረት ፕሬዘዳንቷ ጋዲሴ ተፈሪ ስትናገር ከምክር ባለፈ ከአደንዛዥ እጽ ጋር በተገናኘ በ2013 ዓ.ም. በተማሪዎች ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ሴቶችም የቅጣቱ ሰለባ ሲሆኑ ይስተዋላል ትላለች። 

የዩኒቨርሲቲው የመኝታ አገልግሎት ኃላፊ አቶ መሠረት ዳባ “ሰራተኞቻችን የሚሰሩት በፈረቃ ነው እርሱም የፈጠረው ክፍተት አለ። ድንገተኛ ክትትልም ሆነ በጥቆማ እርምጃዎች እንወስዳለን ተማሪዎች ጋር ግን የመሸፋፈን እና የማስመለጥ ችግር አለ” ያሉ ሲሆን  ምን ዓይነት እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ የጠየቅናቸው ኃላፊው ከትምህርት ከማገድ ጀምሮ በሕግ እስከመጠየቅ እየተሰራ እንደሆነ ነግረውናል።

በተለያዩ የከተማዋ  የቪአይፒ የጫት መቃሚያና እና የሺሻ ማስጨሻ አገልግሎቶች ተለምደዋል። በእነኚህ አገልግሎቶች ውስጥ ካናቢስ በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል መመልከታቸውን ከተለያየ ሰዎች ይደመጣል። 

"በትልልቅ የከተማዋ የምሽት ክበቦች  ውስጥ  ማጨስ ባይቻልም በአካባቢዎቹ ከሚገኙ የመንገድ ላይ ነጋዴዎች (ጀብሎ) ገዝቶ ማጨስ የተለመደ ነው።" የሚለው በሽያጭ ሰራተኝነት የተሰማራው ዮሐንስ ኃይሌ በአንዳንድ በከተማዋ አካባቢዎች ግን "በመጠጥ ቤቶች ውስጥ ጭምር በግልጽ ይጨሳል። ባለቤቶቹ ደንበኛ እንዳይርቃቸው  ዝምታን ይመርጣሉ" ሲል ትዝብቱን ለአዲስ ዘይቤ ይናገራል።

የሕግ አስከባሪዎቹም ከመጠጥ ቤቶቹ ላይ ያላቸው ቁጥጥር እጅግ ደካማ ነው።

የእጹ በቀላሉ መገኘት፣ የመዝናኛው ዘርፍ  እና  የታዋቂ ሰዎች ተጽዕኖ ታክሎበት በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ዘንድ በሚዘጋጁ እንደ ልደት፣ ክሬዚ፣ ቤቢ፣ ፕሮሬሽናል፣ ካልቸር፣ ፕሮም (መለያያ) እና መሠል ዝግጅቶች (ፓርቲዎች) ላይ ካናቢስ መጠቀም ተለምዷል። በውጤቱም ልቅ ለሆነ ወሲብ፣ የዝርፊያ ወንጀል እንዲሁም በቡድን ጸብ የህይወት የአካል እና የንብረት ጉዳት ዋነኛ መንስኤ እየሆነ ነው።

የእጹ መስፋፋት ዓይነተኛ ምልክቶች መሀከል በኮንደሚኒየም ኗሪዎች የሚያቀርቡት ቅሬታዎች ናቸው። ሽታው ረጅም ርቀት መጓዝ መቻሉና በቶሎ ሱስ የማስያዝ አቅሙ ብዙዎችን ክፉኛ አሳስቧል። "ወለሉ ላይ ካለው መጠጥ ቤት ወጥተው ጋንጃ የሚያጨሱ ወጣቶች በመኖራቸው ጭሱ እጅግ በጣም እየረበሸን ነው። ቤት የሚውሉት ታናናሾቼ ሱሰኛ እንዳይሆኑ በጣም እጨነቃለው።" የሚለው የሙዚቃ አቀናባሪው ዮሚዩ ሳምሶን ነው። በተደጋጋሚ ለአካባቢው ፖሊስ እና ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ኮሚቴ ቢናገርም መፍትሔ እንዳላገኘ ይናገራል።

የምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 ዓ.ም. መሠረት ናርኮቲክ እጾችን ይዞ መገኘት የስድስት ወር እስር ሲያስቀጣ መሸጥ እና ማዘዋወር እስከ ከ100ሺህ ብር ጀምሮ እንደየአፈጻጸሙ ያስቀጣል።

ይህ ሕግ ቢኖርም በተጨባጭ የሚታየው ግን ከጉዳዩ እጅግ የራቀ ነው። የአዳማ አብዛኛው የካናቢስ አቅርቦት ከሻሸመኔ እና አካባቢው እንደሆነ ቢታመንም አገልግሎት በማይሰጡ፣ ተጀምረው በቆሙ ሕንጻዎች፣ በከተማዋ ዙሪያ ባሉ ከተሞች፣ እንዲሁም አዳማ ውስጥ በግለሰብ መኖሪያ ጊቢዎች እንደሚመረት ይነገራል።

በወንጂ ከተማ ኗሪ የሆነው ወጣት ሔኖክ ግርማ በፊት በፊት በጣም ጥቂቶች በድብቅ ይጠቀሙ እንደነበር ያስታውሳል። "በአሁን ወቅት አመሻሽ አካባቢ በሸንኮራ አካባቢዎች ወጣቶች ሁለት ሦስት ሆነው ሲያጨሱ ማግኘት እየተለመደ መጥቷል" ይላል።

"እጹን በጓሮ ማብቀል እና ለራስ፣ ለአካባቢው ሽያጭ ማቅረብ የተለመደ ተግባር ነው።" ሲል አስተያየቱን ይቋጫል። በሞጆ፣ በአዋሽ መልካሳ እና ከአዳማ ዙሪያ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች ተግባሩ እየተስፋፋ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

"ዋጋው በኪሎ በግምት ከ4ሺህ 500 እስከ 5 ሺህ ብር ነው። በአብዛኛው ግን ተቆንጥሮ በ50 እና በ100 ብር ይሸጣል።" የሚለው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የከተማዋ ኗሪ ወጣት እንደ ደረጃው ዋጋው ከፍ ዝቅ እንደሚልም ይናገራል። በተጠቃሚዎቹ ዘንድ ድሬድ፣ ሲድ፣ ሀይ ግሬድ የተባሉ ደረጃዎች አሉት።

"እያንዳንዱ ሰፈር የራሱ ክልል ያለው ካቦ (የሰፈር አለቃ) አለው። ማንም የማንንም ድንበር አልፎ አይሰራም። የሚሸጡትም ልጆች ለካቦው ገንዘብ ይከፍላሉ" የሚለው ወጣቱ ስራው የብዙ ሰዎች የገበያ ሰንሰለት የሚሰራ እንደሆነ እንደሚያምን ይናገራል።

ከናርኮቲክ እፆች ውስጥ የሚመደበው ካናቢስ በውስጡ ቴትራሔድራል ካናቢኖል (THC) የሚባል ንጥረ ነገር ይገኛል። በእጹ እና በተጠቃሚዎቹ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ዕንደሚያሳዩት ንጥረ ነገሩ በተጠቃሚው ላይ እንደ ፍርሃት፣ ቅዠት፣ ልብ ምት መጨመር ያሉ ያልተለመዱ ባህርያትን ያስከትላል። የማሽተት፣ የመቅመስ፣ የማየት አቅምን ይቀንሳል። ከረጅም ጊዜ አንጻር ለማሰብ ችሎታ መቀነስ፣ ለማኅበራዊ እና ግለሰባዊ ህይወት መቃወስ፣ ለደስታ ማጣት፣ ለድብርት ያጋልጣል።

ከጤና ተጽዕኖ አንጻር የሚያስከትለውን ጉዳት የጠየቅናቸው ዶ/ር ታሪኩ ገለሼ ከግለሰብ ጤና አንጻር “ከፍተኛ ደስታ (Euphoria)፣ ዝንጋኤ፣ ለሰዓት፤ ሰዎች እና ቦታዎች የሚኖረን አረዳድ መሳት፣ ወሲብ እና ወንጀል ነክ ነገሮችን ማሰብ እንዲሁም ለአፋጣኝ የስነ-ልቦና እና የአዕምሮ አሰራር ቀውስ (Psychosis) ተጋላጭ መሆን፤ የእውነታ፣ የስብዕና እና የማንነት ቀውስ (Depersonalization and derealization) ይዳርጋል። ሳይንሳዊ ጥናቶች የተሟላ ድምዳሜ ላይ ባይደርሱም ለስኪዞፍሬኒያ (Schizophrenia) የመጋለጥ እድልን በእጅጉ ይጨምራል ተብሎ ይታመናል።” ሚሉት ዶ/ር ታሪኩ በዚህ ዓይነት የእጹ ተጠቃሚዎችን ለከፋ የጤና እክል እየዳረገ ሀገራዊ ጤና በጀት ለእነኚህ በሽታዎች በማዋል የጤና ስርዓቱን እንደሚጎዳም አክለው ተናግረዋል።

ሱስ እንደማንኛው በሽታ ታክሞ የሚድን መሆኑ ታውቆ ሕብረተሰቡ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት መጠቀም እንዳለበትም ምክራቸውን ለግሰዋል።

አስተያየት