መስከረም 28 ፣ 2014

አሳሳቢው የታዳጊዎች እና የወጣቶች የሱስ ተጋላጭነት

City: Bahir Darጤናማህበራዊ ጉዳዮች

በዓለም ዙርያ ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ አዕምሮን የሚያነቃቁ ንጥረ-ነገሮች (ቅመሞች) የያዙ ዕፅዋት መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህም መካከል ወደ 60 የሚሆኑት በሰው ልጆች የሚዘወተሩ ናቸው። ጫት እነዚህ ውስጥ ይመደባል።

Avatar: Ayele Addis
አየለ አዲስ

Ayele Addis is an award winner Journalist, Journalism, Trainer, Researcher, and Media & Communication Development Consultancy for Thomson Reuters' Foundation, Africa News Channel, Amhara Media, and Journalists Association. Ethiopian Mass Media Action (EMMA News), ARMA Media Production.Woldia University and Bahir Dar University and founder of Journal of Ethiopian Media and Communications.

አሳሳቢው የታዳጊዎች እና የወጣቶች የሱስ ተጋላጭነት
Camera Icon

ምስል: ከማህበራዊ ሚዲያ

በዓለም ዙርያ ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ አዕምሮን የሚያነቃቁ ንጥረ-ነገሮች (ቅመሞች) የያዙ ዕፅዋት መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህም መካከል ወደ 60 የሚሆኑት በሰው ልጆች የሚዘወተሩ ናቸው። ጫት እነዚህ ውስጥ ይመደባል። የዚህ ማኅበራዊ እጽ አብቃይ ከሆኑ ሐገራት ቀዳሚዋ ኢትዮጵያ እንደሆች ይነገርላታል። (Malcom,1972 cited in Austin, 1979)። 

በኢትዮጵያ የጫት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ እንደሚገኝ በርካታ ጥናቶች አመላክተዋል። ጾታ፣ ዕድሜና ኃይማኖት ሳይለይ ተጠቃሚዎቹ እየበዙለት ስለመሆኑ እነኚሁ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የጫት ተጠቃሚነትን የሚያግድ ምንም ዐይነት ሕግ አለመኖሩ ስርጭቱ እንዲስፋፋ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል። እንደ ዘጋርዲያን ጋዜጣ የ2004 ዘገባ ጫት በአሜሪካና ካናዳ እንዲሁም በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ዓለም አቀፍ ክልከላ ከተደረገባቸው አደገኛ መድኃኒቶች ተርታ ተመድቧል። እንደ ዘገባው ጫት ከሄሮይን እና ኮኬይን ተርታ ተፈርጆ ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረግበታል። 

በተለይ ችግሩ እየተስፋፋ መጥቶ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዲግሪ ብቻ ሳይሆን ልጀ በሱስም ተመረቀ እንዲሉ የሚያስገድድ ሁኔታዎች እየተፈጠረ መሆኑን ወላጆች ይገልፃሉ። በተለይም በዩንቨርሲቲዎች እና ከ2ኛ ደረጃ በላይ ተማሪዎች አምሽቶ በማጥናት፣ በጓደኛ ግፊት፣ ለመዝናናት በሚሉ ሰበቦች ሱስ ውስጥ እየተዘፈቁ ስለመሆናቸው ጥናቶች አመላክተዋል።

በአደገኛ እጾች ገፅታም በኢትዮጵያ የሻሸመኔ ከተማ ካናቢስ በስፋት ከሚመረትባቸው ሰፍራዎች መካከል መሆኗ ይታወቃል። እንዲያውም ካናቢስ ከአርባ ዓመት በላይ በሻሸመኔና በአካባቢዋ ሲመረት እንደቆየ ካሳዬ እና ጓደኞቹ በ1999 ያወጡት መረጃ ያሳያል። በኢትዮጵያ የፌድራል ፖሊስ የሱስ አስያዥ ነገሮች ቁጥጥር ክፍል እንዳስታወቀው ካናቢስ በኢትዮጵያ ስራ አጥ በሆኑ ሰዎችና በጎዳና ተዳዳሪዎች እንዲሁም የወንጀል ድርጊት በሚፈጽሙ ሰዎች በስፋት የሚወሰድ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። 

ጌጤ ፀጋዬ በ2010 ዓ.ም. ባወጡት ወጣት ልማት በኢትዮጲያ በተሰኘ የምርምር ሰብስብ መድብል እንደገለፀው በአሁኑ ወቅት በተለይም በትልልቆቹ የኢትዮጵያ ከተሞች ሺሻ ማጨስ እየተስፋፋ መሆኑ ይታወቃል። ገዛኸኝ ተስፋየ፣ አንዱዓለም ድረስ፣ ምትኩ ተሾመ በ2013 ባወጡት የጥናት ሪፖርት ደግሞ በአሁኑ ወቅት የችግሩ ስርጭት የት/ቤቶችን፣ የመምህራንን፣ የወላጆችን፣ የኅብረተሰቡንና የመንግሥትንም ትኩረት ሁሉ የያዘ ማኅበራዊ ችግር ወደመሆን ደረጃ ያደገ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል። የማኅበራዊ የጥናት መድረክ ባጠናው ጥናት ተማሪዎች መካከል ከ40% በላይ የሚሆኑት ባለፉት 12 ወራት አልኮል፣ አደንዛዥ ዕፆችና አደገኛ መደኃኒቶች አንዱን ወይንም ከአንድ በላይ መጠቀማቸውን ሪፖርት አድርገዋል። 

በማኅበራዊ የጥናት መድረክ እንደተመለከተው የአልኮል ሱስ በወጣቶች ዘንድ የ31.2% ደርሻ አለው። ለዚህም አልኮል በቤት ውስጥ መዘጋጀት የመቻሉና በዚህም ልጆች በቀላሉ ሊያገኙት የሚችሉበት ዕድል መኖሩ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ዓለም አቀፍ የጥናት ወረቀቶችን የሰሩት ናዛሪያስ እና ሮጀርስ ያብራራሉ (Nazarius & Rogers, 2005)። በተመሳሳይም መረጃዎች ዕንዳሳዩት በየበዓላቱና አውደ ዓመቱ በቤት ውስጥ ጠላን የመሳሰሉ የአልኮል መጠጦች ስለሚዘጋጁ ልጆች አልኮልን በቀላል የሚያገኙትና መጀመሪያ የሚሞክሩት እንደሆነ ገልጸዋል። በተለይም አንዳንድ ወላጆች እና ዐዋቂ የቤተሠብ አባላት ህፃናት የዐዋቂዎችን ትራፊ እያነሱ ሲጨልጡ ከመገሰፅ ይልቅ የሚስቁ፣ የሚያበረታቱና እና እንዲያውም አልኮል ለህፃናት የሚያቀምሱ መኖራቸውን ተናግረዋል። 

በሀገራችን ከአልኮል በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ (15%) ተጠቃሚ ያለው ጫት ነው። በተመሳሳይ በባህር ዳር፣ ሀዋሳና በሻሸመኔ በተለያዩ የክልል ከተሞች እና አካባቢዎች የተካሄዱት ጥናቶች እና ሪፖርቶች እንዳመለከቱት ጫት በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ዕፅ ሲሆን፤ በተለይም በወጣት ተማሪዎች መካከል ጫት የመቃም መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል። የጫት ተጠቃሚነት የሚጀምረው ገና በወጣትነት ወቅት ነው። 

በአፍንጫ የሚሳቡ ወይንም የሚሸተቱት ቤንዚንና የመሳሰሉት ደግሞ የ8.9% ተጠቃሚ ያላቸውና በሦስተኛ ደረጃ የሚታዩ ናቸው። በአፍንጫ የሚሸተቱት እንደ ቤንዚን የመሳሰሉትን ይበልጥ አዘወትረው የሚጠቀሙ የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ ልጆች መሆናቸውን ጌጤ ጸጋየ “የአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚነት እና ባህሪያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ጠንቆቹ በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጥናት አስረድተዋል። ከጥናቱ ውጤት መገንዘብ የተቻለው በቤት ውስጥ ከወላጆቻቸው ጋር የሚኖሩ ልጆችም የችግሩ ተጠቂ መሆናቸውን ነው። በተመሳሳይ የሚሸተቱ እንደ ሙጫ (ማስቲሽ) እና የሚነፉ ቀለሞችንም (spray paints) ማሽተት የተስፋፋ በመሆኑ ቁጥሩ ጨምሯል። 

ለዚህ ዘገባ ሐሳባቸውን የጠየቅናቸው ወጣቶች በባህር ዳር እና አካባቢዋ የሺሻ ማስጨሻ ቤቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ መምጣታቸውንና ወጣቶችም ሺሻ ማጨስን እንደዘመነኛነት እየቆጠሩት እንደሆነ ገልፀዋል። ወጣቶቹ ሺሻን የሚያጨሱበት ዋነኛው ምክንያት ለመዝናናት ቢሆንም፤ ሺሻ ከማዝናናት በዘለለ ቆዳን የሚያጠራና ውበትን የሚጨምር ንጥረ ነገር በውስጡ አለው የሚል አመለካከት አላቸው። ሽሻ ቀላል፣ መሳጭ እና የአፍ ጠርንን የማይቀይር መሆኑን እንደሚገፋፋቸው አስረድተዋል። ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ በብዙዎች ዘንድ ሲስፋፋ ብዙዎችን ለጉዳት መዳረጉ አይቀሬ ይሆናል። 

ለወጣቶች ወደ አልኮል፣ ዕጽና መድኃኒት መገገፋት በምክንያትነት ያቀረቧቸው በርካታ ምክንያቶች ሲኖሩ። ከእነዚህም መካከል በሀገራችን በጥናት የለተለዩት ዋና ዋናዎቹ፤  

የአቻ ግፊት፤ በት/ቤት የክትትል ማነስ፤ በዕፆች ላይ ሕጋዊ ክልከላ ያለመኖር፤ ዕፅ ተጠቃሚነትን እንደ ዘመናዊነት መመልከት፤ የአልኮል፣ ዕፅ ወይንም አደገኛ መድኃኒቶች ተጠቃሚነት ጉዳትን አለማወቅ፤ ጤናማ የሆነ መዝናኛ ስፍራ በተለይ በረጅሙ የክረምት እረፍት ወራት ወጣቶቹ ማጣታቸው፤ አዲስ ነገር የመፈተሽ (የመሞከር) ፍላጎት፤ ከቤተሠብ ርቆ በሌላ ከተማ መማርና የዐዋቂ ቁጥጥር በቅርብ አለመኖር፤ በፈተና ግዜ አምሽቶ ለማጥናት መፈለግ፤ የወላጆች የተጣበበ የሥራ ፕሮግራም ልጆችን በተገቢው መንገድ ለመምራትና ለማገዝ ያለማስቻሉ፤ የወላጆች የዕፅ ወይንም መድኃኒት ተጠቃሚነት ናቸው።

አልኮል፣ አደንዛዥ ዕፅና አደገኛ መድኃኒቶችን መጠቀም ከፍተኛ የሆነ የባሕሪ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ጥናቶች ያሳያሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ ገብረ ስላሴ ግብሬ ጥናት ውጤት እንደሚያሳየው አልኮል፣ ዕፅ ወይንም አደገኛ መድኃኒት የሚወስዱት ተሳታፊዎች ከማይወስዱት ይበልጥ በጭንቀትና በድብርት ስሜቶች የሚጠቁ መሆኑ ብለዋል። በጥናታቸው እንዳረጋገጡት  ከሌላው ሰው ይልቅ ዕፅ ወይም አደገኛ መድኃኒት የሚጠቀሙ ሰዎች ከማይወስዱት ሰዎች ይልቅ ለአዕምሮ ችግር የበለጠ የተጋለጡ መሆናቸውን ነው (WEB MD, 2007)። የሆኖ ሆኖ እነዚህን ነገሮች መጠቀም በቀጥታ የድብርት እና የጭንቀት ምክንያት እንደሆነ መውሰድ አያስችልም። በተጨማሪም ተማሪዎች ከሱስ አስያዥ ንጥረ ነገሮች ጋር በተገናኝ ያለውን ችግር እንደገለፁት ቁጡነት፣ ብቸኝነት፣ ዝቅተኛ የትምህርት ውጤትና የባህሪ ችግር አልኮል፣ አደንዛዥ ዕፅ ወይንም አደገኛ መድኃኒት በሚወስዱ ተማሪዎች ላይ አዘውትሮ የሚታዩባቸው ባህሪያት መሆናቸውን ገልፀዋል።

አልኮል፣ አደንዛዥ ዕፅና አደገኛ መድኃኒት ከሚወስዱ ተማሪዎች የሚያወጡት ወጪ ሲጠየቁ የገንዘብ ምንጫቸው ‹‹ከወላጆቻቸውና ከቤተ-ዘመድ፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከቤት ወይንም ከውጪ በማጭበርበርና በመስረቅ፣ በትርፍ ሠዓታቸው ሥራ በመሥራት፣ ከተለያየ ምንጭ ገንዘብ እንደሚያገኙ ገልፀዋል።

አቶ ጌጤ ፀጋየ እንደሚያብራሩት የአልኮል፣ አደንዛዥ ዕፅና አደገኛ መድኃኒት ተጠቃሚ ከሆኑት ተማሪዎች መካከል 30.6% ተማሪዎች የግብረ-ስጋ ግንኙነት መጀመራቸውን ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን በአንጻሩ ተጠቃሚ ካልሆኑት ተማሪዎች ግብረ-ስጋ ግንኙነት የፈጸሙት 12.7% ብቻ ሆነው ተገኝተዋል። ከአልኮል፣ ዕፅና አደገኛ መድኃኒት ተጠቃሚዎቹ መካከል 18.7% ከተለያዩ ሠዎቸ ጋር  የግብረ-ስጋ ግንኙነት እንደሚፈጽሙ ሲታወቅ፤ በአንጻሩ የአልኮል፣ ዕፅና አደገኛ መድኃኒት ተጠቃሚ ካልሆኑት ተማሪዎች መካከል ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈጽሙት 4.9% ብቻ መሆናቸው ታውቋል።

ዛሬ ማሪዋና በከተሞች ትምህርት ቤት ተጠቃሚዎች ዕየታዩ ነው። አልኮል፣ ጫትና በአፍንጫ የሚሳቡ እንደ ቤንዚን ያሉ ነገሮች በቅደም ተከተል ከሌሎቹ ይልቅ በተማሪዎች መካከል በርካታ ተጠቃሚዎች ያሏቸው አሏቸው ሲሉ ተመራማሪው አቶ ጌጠየ ይገልፃሉ። 

ተማሪዎችን ለአልኮል፣ አደንዛዥ ዕፅና አደገኛ መድኃኒቶች ተጠቃሚነት ከሚያጋልጧቸው ምክንያቶች ዋነኞቹ የአቻ ግፊትና የዕፆቹ በአካባቢዎቹ በቀላሉ መገኘት መሆኑም ታውቋል። ስለሆነም የችግሩ ስፋት በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ ወላጆች፣ ት/ቤቶች፣ ህብረተሠቡና መንግሥት በቅንጅት የአልኮልና አደንዛዥ ዕፅ እንዲሁም የአደገኛ መድኃኒቶችን ስርጭት ለመቆጣጠርና ለማጥፋት ተግተው መስራት እንደሚኖርባቸው ባለሙያው ያሳስባሉ።

አስተያየት