በኪቶ ፉርዲሳ ሁለገብ ልማት ኢንተርፕራይዝ ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች በወርሃዊ ክፍያ የሚቀርብ የወተት አገልግሎት ላይ የዋናው ግቢ ተጠቃሚዎች ቅሬታ እንዳላቸው ለአዲስ ዘይቤ ገለፁ፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በኪቶ ፉርዲሳ ሁለገብ ልማት ኢንተርፕራይዝ አማካኝነት ለሰራተኞቹ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ወተት በወርሃዊ ክፍያ ማቅረብ አንዱ ነው፡፡ አገልግሎቱ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ከማገዝ ባሻገር ዩኒቨርሲቲው ለውስጥ ገቢ ማመንጫነት ይጠቀምበታል፡፡ ሃሳቡ ጥሩ ሆኖ ሳለ በወተት አቅርቦቱና አጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር ተጠቃሚዎች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡
ከበደ አለነ የወተት አቅርቦቱ ተገልጋይ ነው። ከበደ በወተት አቅርቦቱ በጣም እንደተማረረ ይገልፃል። “ወተት ለመውሰድ ተመዝግቤ ሁለት ዓመት ሙሉ ሳላገኝ ስጠባበቅ ነበር፡፡ ማድረግ ባይጠበቅብኝም በጎን ሄጄ ተመዝግቤ ወተት መውሰድ ጀመርኩ” ይላል። “ወተት መውሰዱ ደግሞ በራሱ ብዙ ችግር አለበት፡፡ ወተቱ የሚመጣበት ሰዓት ከአራት እስከ አምስት ነው ይባላል፡፡ አንዳንዴ ቀድሞም ሌላ ግዜ ደግሞ ዘግይቶ ይመጣል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ወይ ታገኛለህ አሊያም አታገኝም፤ ዛሬ አልቋል ነገ ውሰዱ ይባላል፡፡ በንጋታውም ስትጠይቅ ዛሬም አልተረፈም ነገ፣ ነገ… እየተባልክ ትቀጥላለህ”።
ከበደ አገልግሎት አሰጣጡ በዚህ አመት እንደባሰበት ይናገራል፣ “ድሮ እንኳን በጋ ወቅት ላይ ነበር የወተት እጥረት የሚያጋጥመው፡፡ አሁን ግን በጥቅምትና ህዳር ወራት ወተት አላገኘንም፡፡ ሁሌም እከፍላለሁ ግን አንዳንዴ የ30ቀን ከፍለህ የ15ቀን ብቻ ትወስዳለህ” በማለት ምሬቱን ገልፅዋል። “ለምን እንዲህ ይሆናል ብዬ ለመጠየቅ ራሱ እፈራለሁ፡፡ ምክንያቱም ስለጠየቅኩ ብቻ ይሄ ወተት አይሰጥህም ብባል የኔ ጎሮሮ አይደለም የልጄ ጎሮሮ ነው የሚዘጋው ለዚህ ስል እፈራለሁ፡፡ ሁሉም ሰው ደግሞ የዚህ ችግር ተጋሪ ነው” ሲል በጅማ ዩኒቨርሲቲ ወተት አሰጣጥ ዙሪያ ያለውን ችግር ይናገራል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ለልጁ ሲል ዩኒቨርሲቲው የሚያቀርበውን ወተት ተጠቃሚ ለመሆን ተምዝግቦ እየተጠባበቀ የሚገኘው የዩኒቨርሲቲው ሰራተኛ፣ ፍሮምሳ ጎዳና ይሄን ቅሬታ ይጋራል። “ዩኒቨርሲቲው የሚያቀርበው የወተት አገልግሎት ብዙ ችግር አለበት፡፡ እኔ ወተት ለመውሰድ የተመዘገብኩት ከሁለት ዓመት በፊት ነው፤ ግን ማንም አልጠራኝም፡፡ ከኔ በኋላ መተው ከአገልግሎት ሰጪው ጋር ግንኙነት ስላላቸው ብቻ ወተት እየወሰዱ ያሉ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የምትሆነው በተመዘገብከው ቅደም ተከተል ሳይሆን በትውውቅና በጉቦ ነው፡፡ አገልግሎት ሰጪዎቹ የሆነ ነገር እንድትሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ድብቅ አይደለም”።
ተጠቃሚዎቹ የወተቱ ጥራት ላይም ጥያቄ እንዳላቸው ገልፀዋል። “አንዳንዴ የወተቱ ጥራትም ችግር አለበት፣ ሲረጋ ግማሹ ውሃ የሚሆንበት ግዜም አለ” በማለት ቅሬታቸውን ይገልፃሉ።
ሌላ ማህበሩ የሚያቀርበውን ወተት ተጠቃሚ የሆነችው ሌሊሴ ግርማ በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ ያጋጠማትን ችግር ስትገልፅ “ለግማሽ ሊትር በወር 450ብር እከፍላለሁ፣ በየግዜው የወተት እጥረት አለ ስለሚባል ወሩን ሙሉ ብር ብንከፍልም አብዛኛውን ግዜ ወተት አናገኝም፡፡ በጥራትም ቢሆን ከግማሽ በላይ ወተት ውሃ የሚሆንበት ግዜ አለ፡፡ የወተት አሰጣጡ ግዜን በጣም ይወስዳል፡፡ ከአራት ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት ይሰጣል ቢባልም እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ድረስ የምንጠብቅበት ግዜም አለ፡፡ ይህ በጣም መሻሻል ያለበት ጉዳይ ነው” ትላለች።
በተጨማሪም ወተት ለመውሰድ በሚሄዱበት ሰዓት በተደጋጋሚ ወተት እንዳለቀና በቀጣዪ ቀን መውሰድ እንደሚችሉ ተነግሯቸው እንደሚመለሱ፣ ነገር ግን በቀጣዪም ቀን ተመሳሳይ ነገር እንደሚያስተናግዱ ትገልፃለች፡፡
ለአዲስ ዘይቤ ሀሳባቸውን የሰጡት ተገልጋዮች ዩኒቨርሲቲው በወተት አቅርቦት ዙሪያ የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በአፋጣኝ መፍታት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የኪቶ ፉርዲሳ ሁለገብ ልማት ኢንተርፕራይዝ በከብት፣ ዶሮና ንብ እርባታ እንዲሁም በጓሮ እርሻ የተሰማራ ማህበር ነው። የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዬ ዘሪሁን ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት ከሆነ በዋናነት ለዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች የሚቀርበው የወተት ምርት ሲሆን በተጨማሪም የስጋ በሬዎች፣ እንቁላልና ዶሮዎችን እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘይቤ የተጠቃሚዎቹን ቅሬታ ለማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቅርባለች። “አንዳንዴ ያረጁ ላሞችን ቀንሰን ሌላ ገዝተን እስክንተካ ወይ ደግሞ ያሉት እስኪወልዱ ድረስ የወተት እጥረት ይፈጠራል፡፡ በዚህ መልኩ የሚፈጠረውን እጥረት ወተት ሲተርፍ ለማካካስ እንሞክራለን” ብሏል። ከተጠቃሚዎች የሚነሳው የወተት እጥረት ያለመካካስ ቅሬታ “የተጋነነ ነው” ያለው ቅዳሜና እሁድ የማካካስ ሥራ እንደሚሰራም ገልፅዋል፡፡ “ወተት የሚመረትበት ስፍራ ኪቶ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ነው። በክረምት ወራት መንገዱ አመቺ ስላልሆነና የወተት ተሽከርካሪ መግባት ስለማይችል እስከ ቴክኖሎጂ ግቢ ድረስ በትራክተር ነው የሚመጣው በዚህ ምክኒያት በግዜ ለማቅረብ እንቸገራለን፣ በበጋ ግን እንደዚህ አይነት ችግር ይቀንሳል” ብሏል።
በሌላ በኩል ተመዝግበው ለሁለት ዓመት እድል ሳይደርሳቸው ስለቆዩት ሰራተኞች ለተጠየቀው ጥያቄ “ለወደፊትም ላይደርሳቸው ይችላል” ይላል፡፡ “የወተት አቅርቦት እጥረቱን ከሚፈጥሩት አንዱ የተጠቃሚዎች ብዛት በመሆኑ እነሱም በኛ ላይ ብቻ ጥገኛ ባይሆኑና ሌላ አማራጭ ቢፈልጉ የተሻለ ይሆናል” ሲል መክሯል፡፡
በስተመጨረሻም በበጋ ወራት ከዚህ የባሰ የወተት እጥረት እንዳይከሰት ምን ታስቧል ስትል አዲስ ዘይቤ ለሥራ አስኪያጁ ላቀረበችው ጥያቄ አቅርባለች “ከዚህን በፊት ያጋጠመንን ችግር አሁን አውቀናል፡፡ ያረጁ ከብቶችን አስወጥተን፣ የደረሱ እርጉዝ ላሞች አስገብተናል ጊደሮችንም ቀይረናል፡፡ በዚህ ወር ያጋጠመንን ችግር ከጥር ወር በኋላ ያቃልልናል ብለን እናስባለን” ብሏል። በምዝገባው ዙሪያ በትውውቅና ጉቦ ይሰራል ብለው ቅሬታ የሚያቀረቡ ሰራተኞችን ጉዳይ አዲስ ዘይቤ አንስታለታለች እንደምላሽም እሱ ምንም የሚያውቀው ጉዳይ አለመኖሩን ገልፆ “አንዳንዴ ግን ሰራተኞች ጡረታ ሲወጡና ሥራ ለቅቀው ሲሄዱ ለሌላ ሰው ሰጥተው ስለሚሄዱ የራሳቸው ባልሆነ ኩፖን ወተት የሚወስዱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ እንዳይፈጠር ተጠቃሚዎቹ እንዲጠቁሙን እንነግራቸዋልን፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ይሰራል የተባለው የመድልዎ ሥራ የለም” ሲል አቶ ታዬ ዘሪሁን ተናግሯል፡፡
የልማት ኢንተርፕራይዙ የከብት፣ ዶሮና ንብ እርባታ እንዲሁም በጓሮ እርሻ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አምስት አመት አስቆጥሯል፡፡ በዋናነት ለዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች የሚቀርብ የወተት አገልግሎት ደግሞ አሁን ከ500 ተጠቃሚ በላይ በሶስቱም የዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች ያቀርባል፡፡ ባሁኑ ግዜ 65 የሚታለቡ ላሞች ሲኖሩ በአማካኝ በቀን 400 ሊትር ያስገኛሉ ተብሏል፡፡ ለወደፊት የሚታለቡ ላሞችን 200 በማድረስ በቀን 2000 ሊትር ለማግኘት እቅድ አለ ብሏል ሥራ አስኪያጁ፡፡