ኅዳር 25 ፣ 2013

አሶሳ፡ መስተዳድሩ የመሬት ወረራን ለመከላከል እርምጃ መውሰድ ጀመረ

ኢትዮጵያኣሶሳ

(አዲስ ዘይቤ- አሶሳ) በአሶሳ ከተማ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ ለመከላከል የህግ ማስከበር ሥራ እያከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡ ከተማ…

አሶሳ፡ መስተዳድሩ የመሬት ወረራን ለመከላከል እርምጃ መውሰድ ጀመረ

(አዲስ ዘይቤ- አሶሳ) በአሶሳ ከተማ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ ለመከላከል የህግ ማስከበር ሥራ እያከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በ20 ግለሰቦች ላይ እርምጃ የወሰደ ሲሆን ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑንም አስታውቀዋል። የከተማው ከንቲባ አቶ ዑመር አህመድ በአሶሳ ከተማ በስፋት የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ መሬት ወረራና የቤት ግንባታ ለመከላከል በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ « በድርጊቱ ላይ እየተሳተፉ ያሉት የከተማ ቦታ ያላቸውም የሌላቸውም ነዋሪዎች ናቸው፡፡

ህገ-ወጥ ድርጊቱን ለመከላከል ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደሥራ ገብቷል» በማለት አክለዋል፡፡ ቤት ገንብተው የፈረሰባቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው «እርምጃው ቤት ከሠራን በኃላ የተወሰደ በመሆኑ ለኪሳራ ተዳርገናል» ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡ በአሶሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አበበ ይሁን በበኩላቸው «ከ1 ወር በፊት 2 ክፍል ቤት ሠርቼ ብገባም፣ ከተማ አስተዳደሩ አፍርስብኛል፡፡ ቤቱን የሠራንበት ቦታ በከተማ አስተዳደሩ ያልተሰጠንና በህገ-ወጥ መንገድ መሆኑን ብናውቅም ቀድሞ መከላከል ሲቻል ቤት ከሠራን በኋላ እርምጃ መወሰዱ ኪሳራ ላይ ወድቀናል» ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በህገ-ወጥ መንገድ ቤት ለገነቡ ግለሰቦች በራሳቸው የሚያፈርሱበት በቂ የማስጠንቀቂያ ጊዜ መሰጠቱን የሚናገሩት ከንቲባው ደግሞ በተሰጣቸው ጊዜ ንብረታቸውን ባላነሱት ላይ ግብረ-ኃይሉ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህገ-ወጥ ግንባታው የሚከናወነው ጨለማን ተገን በማድረግ መሆኑ ህግ የማስከበር ተግባሩን ፈታኝ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡ (ነጻነት ካሳሁን)

አስተያየት