ኅዳር 25 ፣ 2013

ጎንደር፡ ነዋሪው ያልተጠቀመው የካፒታል እቃ ብድር አገልግሎት

ጎንደር

የካፒታል እቃ ብድር አቅራቢ ተቋም (ሊዝ ፋይናንሲንግ) ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ በአምስት ክልሎች ፍላጎት ያላቸውን ተጠቃሚዎች የማምረቻ መሳርያ…

ጎንደር፡ ነዋሪው ያልተጠቀመው የካፒታል እቃ ብድር አገልግሎት

የካፒታል እቃ ብድር አቅራቢ ተቋም (ሊዝ ፋይናንሲንግ) ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ በአምስት ክልሎች ፍላጎት ያላቸውን ተጠቃሚዎች የማምረቻ መሳርያ ባለቤት ለማድረግ የተቋቋመ ነው። አንድ ባለሙያ፣ ግለሰብ ወይም ማህበር በንግድ ስራ ላይ ሆኖ ተጨማሪ የማምረቻ እቃ የሚፈልግ ከሆነ ይህ ብድር አቅራቢ ተቋም እቃውን ያለምንም መያዣ ገዝቶ ያቀርብለታል። ለምሳሌ የጣውላ ስራ ባለሙያ በመጠነኛ ካፒታል እየተንቀሳቀሰ ከፍተኛ ካፒታል የሚፈልግ መሳርያ መግዛት ቢፈልግ ያለምንም መይዣ (collateral) የመሳርያውን 15-30 በመቶ በመቆጠቡ ብቻ እቃውን ያቀርብለታል::

ይህ አሰራር ከመደበኛ የባንክ ብድር የሚጠየቀውን ማስያዣ አስቀርቶ ከ25ሺህ እስከ 10ሚልዮን ብር ማምረቻ እቃ መግዣ ብድር ይሰጣል። በትግራይ ክልል ካዛ እቃ ካፒታል - በደቡብ በኦሮሚያ በድሬዳዋ እና በአማራ ክልል ዋልያ ካፒታል እቃ የሚባል ሲሆን አዲስ ዘይቤ የጎንደር ቅርንጫፉን አነጋግራለች። 

ዋልያ ካፒታል ጎንደር ቅርንጫፍ ቀበሌ 15 ስቴድየም ፊት ለፊት ይገኛል። የቅርንጫፉ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋሁን አያሌው በጎንደር ከተማ ይህ ተቋም በሥፋት እንደማይታወቅ እና በክልሉ በዝቅተኛ በጀት ተርታ እንደሚሰለፍም ይናገራሉ “የዘንድሮው በጀት እስከ 22 ሚልዮን ብር ድረስ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ሰባት ሚልዮን ብቻ ነው ለብድር አገልግሎት የዋለው” ዋልያ ካፒታል ከ2007 ዓ.ም ከተቋቋመ ወዲህ በከተማዋ የነበረው አለመረጋጋት ተቋሙን ራሱን እንዳያስተዋውቅ ማድረጉን የሚናገሩት ኃላፊው በጎንደር ከተማ በብድር አቅርቦት የመስራት ባህል አለመኖሩ በአሰራር አኳያም መጠነኛ የሆነ ቢሮክራሲ ችግርን ጨምሮ ሌሎች ምክንያቶችን ስለተቋሙ ያብራራሉ። 

“በሌሎች ከተሞች እስከ 100ሚልዮን ብር ድረስ ለብድር አቅርቦት ተከፍሏል ጎንደር ከተማ ግን ከሌሎች በተለየ ዝቅተኛ እንቅስቃሴ አለው” በማለትም ስላለዉ ዝቅተኛ ድርሻ ይናገራሉ። የመብራት ኃይል አቅም ማነስ - የመስሪያ ቦታ ችግር፣ የግንዛቤ እጥረት፣ የሙያ ማነስ እና የተለያዩ ምክንያቶች ዝቅተኛው እንቅስቃሴ እንዲመዘገብ ካደረጉት ናቸው ሲሉም ያክላሉ።  ስለዚህ ተቋም ጠቀሜታ ሲገልፁ “በተለይ በንግድ ስራ ለተሰማሩ ኗሪዎች ይህ ተቋም ብዙ ጥቅም አለው” ያሉት ኃላፊው በጋራ ርብርብ ከፍተኛ የሆነ ግንዛቤ በመስጠት ከተማዋን ማነቃቃት እንደሚያስፈልግም ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል::

የከተማዋ አስተዳደር ይህንን የኢኮኖሚ እድል ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ እንዲጠቀምበት እድል ለምን አያመቻችም ብላ አዲስ ዘይቤ ለጠየቀችው ጥያቄ የማህበራት ማስፋፊያ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አቶ ምስጋናው ሽብሩ የተሰጠ ብድር ቶሎ አለመመለሱ በዚያ ላይም የቅንጅት ስራ አለመኖሩን አብራርተው የመብራት እና የቦታ ምሪት ችግሮች እስካሉ ድረስ በየትኛውም መልኩ ለውጥ እንደማይመጣም ተናግረዋል:: የተቋሙ በራሱ ከፍተኛ የሆነ የፕሮሞሽን ስራ መስራት እንደሚጠበቅበትም አያይዘው ጠቅሰዋል።

አስተያየት