ኅዳር 29 ፣ 2013

ለራስ ዘብ ስለ መቆም:- ራስን ከጥቃት የመከላከል ጥበብ

Book

ሰዎች ለወትሮው ጉዳያቸው ሲንቀሳቀሱ በሰላም ውለው እንዲገቡ ይመኛሉ፡፡ ይህ ግን የማይሰካበት ዕለት አይጠፋም፡፡ በተለይ ሴቶች እና ህፃናት በመንገዳቸው…

ለራስ ዘብ ስለ መቆም:- ራስን ከጥቃት የመከላከል ጥበብ

ሰዎች ለወትሮው ጉዳያቸው ሲንቀሳቀሱ በሰላም ውለው እንዲገቡ ይመኛሉ፡፡ ይህ ግን የማይሰካበት ዕለት አይጠፋም፡፡ በተለይ ሴቶች እና ህፃናት በመንገዳቸው አካላዊ ፣ ወሲባዊ ወይም አእምሯዊ ጉዳት የሚያስከትል ማስፈራራት ፣ ማስገደድ ወይም  ነፃነትን ማገድን የሚያጠቃልል ችግሮች ያጋጥማቸዋል፡፡  በኢትዮጵያ እንደዚህ ላሉት ጥቃቶች የበለጠ ተጋላጭ የሆኑት ሴቶች እና ልጃገረዶች ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከልና ብሎም ለማስወገድ ብዙ ጥረቶች ሲያደረጉ አይታይም፡፡ 

የማርሻል አርት ማስተር የሆነው መንግስቱ ምንአለ ይህንን ችግር ለመፍታት በማለም “ራስን ከጥቃት የመከላከል ጥበብ” በሚል ርዕስ ጥቃትን መከላከል ዘርፍ ውስጥ ሚና ለመጫወት በተለይ ለሴቶች ራስን የመከላከል ልምድን ማዳበር የሚዳስሰውን አዲስ መፅሐፍ ለአንባብያን አብቅቷል፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ 100 ብር ሲሆን 81 ገጾች አሉት፡፡ በሜክሲኮ አካባቢ ፣ ከንግድ ኮሌጅ በስተጀርባ ጃፋር መጽሐፍ መደብር እና ሰአዳ መጽሐፍ መደብር ይገኛል፡፡

የማስተር መንግስቱ መጽሐፍ ራስን የመከላከልን ክህሎት እንዴት ማዳበር እንደሚቻል ይዳስሳል፡፡ ከሃያ ዓመት የማርሻል አርት ልምምዱና ለአሥራ ሁለት ዓመታት ለሴቶች ራስን የመከላከልን ጥበብን በማስተማር ባካበተው ክህሎት መሰረት መፅሐፉን የጻፈው የክህሎቱን መስፋፋት ለማገዝ እንደሆነ ይናገራል፡፡ መጽሐፉ የሚያንፀባርቀው አንድን ሰው ራስን ከጥቃት የመከላከል ችሎታ እንዲኖረው ለማዳበር ስለሚያስፈልገው አእምሮአዊ ፣ ማህበራዊና አካላዊ ችሎታ ነው፡፡

መጽሐፉ በመጀመርያ ገፆቹ ጥቃት ምን እንደሆነ እና አንድ ሰው ራሱን ከምን መጠበቅ እንዳለበት ለአንባቢ ያሳውቃል፡፡ በግርድፉ ጥቃት ምን እንደሆነ እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ደግሞ በተለየና በተብራራ ይዘት በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ በመቀጠልም መጽሐፉ ራስን ለመከላከል ፍች ይሰጣል፡፡ አንድ ሰው ራስን የመከላከል ችሎታን ለማዳበር ስነ ልቦናዊ እና አካላዊ የሕይወት ችሎታን ማዳበር ቁልፍ እንደሆነና ራስን የመከላከል ችሎታ ከህይወት ክህሎት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

ስነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ክህሎቶች በመጽሐፉ አምስቱ የ "መ" ሕግጋት ተብለው የተገለፁትን ያካተቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሕግጋትም መተማመን ፣ መቆጠብ ፣ መከተል ፣ መግባባት እና መፍታት ናቸው። መጽሐፉ ከራስ ጋር የጥሞና ጊዜ በማሳለፍ መልካም ሥነ ምግባር እንዴት እንደሚገነባ ምስላዊ ማብራርያ ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም አንባቢው ከራሱ ጋር አዎንታዊ ንግግር የማድረግ ችሎታን እንዲለማመድ ያስችለዋል ፡፡ የሕግጋቶቹ አካል የሆነው “መከተል” የራሱ የሆነ ስድስት መተግበርያ መርሆዎች አሉት እነሱም ማክበር ፣ ትዕግስት ፣ ሀቀኝነት ፣ እውነት ፣ ጥንቃቄ እና በመጨረሻም ራስን የመከላከል ጥብን በአግባቡ መጠቀም ናቸው፡፡

የአካላዊ ክህሎቶች ቴክኒክ በመጽሐፉ ውስጥ ተግባር ተኮር ከሆኑ ምስሎች ጋር ተብራርቷል፡፡ በመጀመሪያ ከሰው አካል ክፍሎች የትኞቹ ጠንካራ እና ደካማ እንደሆኑ ይለያል፣ አንድ ሰው ጠንካራ የአካል ክፍሎቹን እንዴት ለመከላከል እና ለማጥቃት ሊጠቀምበት እንደሚችልም ይገልጻል፡፡ መጽሐፉ መሰረታዊ የአካል ብቃት ጥንካሬ ግንባታ እንቅስቃሴዎችን በተግባራዊ ምስል ያብራራል በመቀጠልም ራስን የመከላከል ክህሎትን ለመለማመድ እንዲያስችል ደረጃ በደረጃ መመሪያዎችን ያቀርባል::

ራስን የመከላከልን ጥበብ ማለትም የማጥቃት እና የመከላከል እንቅስቃሴዎችን እንደሚያጠቃልል በመጽሐፉ በግልፅ ተቀምጧል እንቅስቃሴዎቹ በምስሎች ተደግፈው ከዝርዝር ማብራሪያ ጋር ቀርበዋል፣ ለመለማመድ ቀለል እንዲሉ ይመስላል በማብራርያ እና በምስል ታጅበው የቀረቡት፡፡ መጽሐፉ የዝግጅት አቋቋም ፣ ማምለጥ ፣ ማገድ እና በመጨረሻም ማጥቃትን የሚያካትት ራስን የመከላከል አካላዊ ብቃትን በአጥጋቢ ሁኔታ ያሳያል፡፡ በተጨማሪም ከላይ የተጠቀሱትን የራስ መከላከያ ቴክኒኮችን በማጣመር የራስ መከላከያ ችሎታዎችን ለመተግበር ደረጃ በደረጃ መመሪያ ይሰጣል ፡፡ "Antigrabbing skills" ወይም ራስን ከአካላዊ ቁጥጥር ነፃ የማድረግ ችሎታዎች መጽሐፉ ለአንባቢው የሚያቀርበው ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ራሱን ከአጥቂው አካላዊ ቁጥጥር እንዴት ነፃ ማድረግ እንደሚችል የተለያዩ ዘዴዎችን በምስል ከማብራርያ ጋር በሚገባ አቅርቧል፡፡

ራስን ከወሲባዊ ጥቃት እና ትንኮሳ ለመከላከል ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መፅሃፉ ከወሲባዊ ጥቃት ራስን የመከላከል ቴክኒኮችን በቅድመ ጥቃት ፣ በጥቃት ወቅት እና ከጥቃት በኋላ በማለት ቴክኒኮቹን ይከፋላቸዋል፡፡ አንድ ሰው ራስን ከጥቃት ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑትን ማህበራዊና ሥነ ልቦናዊ ክህሎቶችን ስለማዳበር መጽሐፉ ለምን በመጀመርያ ገፆቹ  እንዳነሳ ስለቅድመ ወሲባዊ ጥቃት መከላከያ ዘዴዎችን ሲገልፅ መረዳት ይቻላል:: ደራሲው አንድ ሰው ሥነ ምግባርን እና ማኅበራዊ ንቃተ-ህሊናን በማጣመር እንዴት የጾታ ጥቃት ክስተቶችን መቀነስ እንደሚቻል ይገልፃል፡፡ በተጨማሪም ጥቃቱ በሚከሰትበት ወቅት እራስን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ተግባራዊ የምስል መመሪያ ሰጥቷል፡፡ ለተግባራዊ አሠራሩ መጽሐፉ የጊዜ ማዕቀፍ ይሰጣል ፡፡በመጨረሻም መጽሐፉ ከጥቃት በኋላ መወሰድ ያለባቸውን ህጋዊና የህክምና እርምጃዎችን ያቀርባል፡፡ 

ደራሲው በመጽሐፉ ውስጥ ለወላጆች መልዕክትን አካቷል፡፡ ራስን የመከላከያ ዘዴዎችን ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ማስተማር እንዳለባቸው ይዘረዝራል፡፡ በመፅሀፉ ላይ ወላጆች በመጀመሪያ ልጆቻቸውን ስለ አካላቸው እና ስለ ግል የሰውነት ክፍላቸው ማስተማር እንዳለባቸው ተጠቁመዋል ፡፡ በተጨማሪም ወላጆች ስለዚህ ጉዳይ በነፃነት እንዲወያዩ ለልጆቻቸው ምቹ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው በሚስማማ መንገድ ስለ ጥቃት እንዴት ማስተማር እንደሚችሉም በዝርዝር ቀርቧል፡፡

የመጽሐፉ ርዕሰ-ጉዳይ የተገነባበት አወቃቀር መልካም እመርታዎች አሉት፡፡ ክህሎቱን ለማዳበር የሚረዱ መንገዶችን በበቂ ሁኔታ አብራርቷል ፡፡ መጽሐፉ ራስን ከጥቃት የመከላከል ጥበብን በሚገባ የማስተማር ግቡን እንደመታ ለመደምደም ይቻላል ሆኖም ግን ክህሎቱን የተገበሩ እና ስልጠናውን የወሰዱ ሰዎች ተግባራዊ ልምዳቸውን እና ከስልጠናው እንዴት እንደተጠቀሙ በመጽሀፉ ቢካተት የመጽሐፉን ይዘት ይበልጥ ለማጠንከር ይረዳ ነበር:: 

ራስን የመከላከል ጥበብ የተባለውን መጽሐፍ ለልጆቻቸው ስለ ጥቃት እና ራስን መከላከያ ዘዴዎች ማስተማር ለሚፈልጉ ወላጆች ፣ ራስን የመከላከል ችሎታን ለማዳበር ለሚፈልጉ ግለሰቦች በተለይም ሴቶች እና ልጃገረዶች እንዲያነቡት አዲስ ዘይቤ ትመክራለች፡፡   

አስተያየት