ኅዳር 29 ፣ 2013

አዲስ አበባ፡ “በባቡሩ ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት እየሞከርን ነው”

Feature

በአዲስ አበባ የቀላል ባቡር አገልግሎት መሰረተ ልማቱ ላይ እየተስተዋለ የሚገኘው ብልሽት እና በሌሎች ተሽከርካሪዎች የሚደርስበት ጉዳት የከተማውን ነዋሪዎች…

አዲስ አበባ፡ “በባቡሩ ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት እየሞከርን ነው”

በአዲስ አበባ የቀላል ባቡር አገልግሎት መሰረተ ልማቱ ላይ እየተስተዋለ የሚገኘው ብልሽት እና  በሌሎች ተሽከርካሪዎች የሚደርስበት ጉዳት የከተማውን ነዋሪዎች እንዲህ ነው ለማይባል እንግልት እያዳረገ ይገኛል። ለምሳሌ ያህል ከአያት እና ከሰሚት መስመር ወደ መገናኛ መስመር ለመሄድ በጣም አዳጋች የሚሆኑባቸው ጊዜያት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ለእነዚህ እንግልቶች ዋነኛ መንስኤ ተብሎ የሚጠቀሰው ደግሞ አደጋዎች ሲከሰቱ በጊዜ መፍትሄ ለመስጠት መዘግየት ነው።

አዲስ ዘይቤ ያነጋገረችው ስሙን መግለጽ ያልፈለገ የታክሲ ሹፌር እንደሚለው ከሆነ “ባቡሩን በተመለከተ ማንኛውም አይነት አደጋ ወይም ብልሽት ሲፈጠር ከሰሚት ኮንዶሚኒየም ወደ መገናኛ የሚወስደው መንገድ እና ከአያት ወደ ሲኤምሲ መገናኛ የሚወስደው መንገድ ይጨናነቃል። የትራፊክ ፍሰቱ በጣም ከመጨናነቁ የተነሳ አንድ ቦታ ከግማሽ ሰአት በላይ ለመቆም እንገደዳለን” ሲል የሚደርስበትን እንግልት ይገልጻል። የባቡር አገልግሎቱን በስፋት የሚጠቀመው አቶ አለሙ እንዳለው "ባቡሩ ሲበላሽ የጥገና ባለሙያዎች በቦታው ተገኝተው ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ ጊዜያችን ይጠፋል። ይሄ ብቻ ሳይሆን አጉል ቦታ ከተበላሸ ወርደን ታክሲ እስከምናገኝ በእግር መጓዝ ይኖርብናል። ይህ አይነት ችግር በማታ ሲከሰት ደግሞ ችግሩን ያባብሰዋል" ይላል። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን አሰፋ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ለምን አስቸጋሪ ሆነ ብላ አዲስ ዘይቤ ለጠየቀችው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ አደጋዎቹ የሚከሰቱበት አካባቢ እንደሚወስነው እና የጥገና ሰራተኞቹ በቦታው ለመገኘት ጊዜ ስለሚወስድባቸው እንደሆነ ገልፅዋል።

አቶ ሙሉቀን ምን መፍትሄ እንደታሰበ ሲናገር “ሰራተኞቹን ወደ እነዚህ አደጋ ወደሚበዛባቸው አካባቢዎች ቀረብ አድርጎ ለመመደብ መስሪያ ቤቱ እቅድ ይዟል” ያለ ሲሆን ሃላፊው ባቡሩ መሃል መንገድ ላይ ብልሽት ቢያጋጥመው እንኳን አቅራቢያው ወደሚገኝ የጥገና ማዕከል መሄድ እንደሚችል ገልፆ ብልሽቱ ከባድ ከሆነ በሌላ ባቡር ተጎትቶ እንዲነሳ እንደሚደረግ ተናግሯል።   በሌሎች ተሽከርካሪዎች ለሚደርስበት ጉዳት ለምን ጉዳት አድራሾቹ ተገቢውን የጉዳት ካሳ እንዲከፍሉ አይደረግም ለሚለው ጥያቄ ሃላፊው ከመድን አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ጋር አብሮ እየሰራ እንደሆነ አስታውሶ እስከዛሬ ወደ አምስት ሚሊዮን ብር የሚሆን የጉዳት ካሳ እንደተከፈለ ገልፅዋል። 

የባቡር መንገዱን ከሌሎች አሽከርካሪዎች የሚለየው አጥር ላይ በሚደርሰው ጉዳት ሳቢያ እግረኞች መሰረተ ልማቱን ከታሰበለት አላማ ውጪ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፣ እነዚህ የተቆራረጡ አጥሮችን በመጠቀም ወደ ተቃራኒ የመንገድ አቅጣጫ ሲሻገሩም ይታያል። ይህ ደግሞ ለአስከፊ አደጋ የማጋለጥ አዝማሚያው ከፍተኛ ነው። ታዲያ እነዚህ አጥሮች ለምን በጊዜ አስፈላጊውን ጥገና አይደረግላቸውም ለሚለው ጥያቄ አቶ ሙሉቀን በምላሹ አጥሮቹ ተሰርተው ይመጡ የነበሩት ከቻይና እንደነበር እና ወጪያቸው ከፍተኛ እንደነበር አስታውሶ አሁን በሃገር ውስጥ ለመስራት አስፈላጊውን የሙከራ ሂደቶችን አልፎ በቀጣይ ሁለት ሳምታት ውስጥ ወደ ጥገና እነደሚገባ ገልፅዋል። 

“መስሪያ ቤቱ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ጋር አብሮ እየሰራ ይገኛል፣ የመንገድ ላይ ምልክቶችን በመትከል እና ለመንገድ ደህንነት አስፈላጊ የተባሉ ሌሎች ባቡሩን የሚመለከቱ መሰረተ ልማቶችን በይበልጥ የማጠናከር ስራ እየሰራ ይገኛል” ብሏል። እነዚህ ምልክቶች የአሽከርካሪዎችን ፍጥነት እና ክብደት የሚያመለክቱ ምልክቶች ናቸው ያለው አቶ ሙሉቀን እነዚህ ምልክቶች እየደረሱ ያሉትን አደጋዎች ይቀንሳሉ ተብሎ ይታመናል ያለ ሲሆነ የሀይል መቆራረጥ ችግር ሲያጋጥም ከመብራት ሃይል፣ የተለያዩ ድንገተኛ አደጋዎች ቢያጋጥሙ ከእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠሪያ እንዲሁም ከውሃና ልማት መስሪያ ቤቶች ጋር አብሮ እየሰራ እንደሆነ ገልፅዋል። 

አስተያየት