ታህሣሥ 1 ፣ 2013

የ100 ዓመቱ ነፍስ አድን ሰራተኛ

(አዲስ ዘይቤ-ሀዋሳ) "አሳ መመገብ እና መልካም ማሰብ እድሜን ያረዝማል" ይላሉ እድሜ ጠገቡ ብርቱ ሰው ጋሽ ሺፌ ካያሞ (ሾፌር) ። ጋሽ ሽፌ አቀላጥፈው…

የ100 ዓመቱ ነፍስ አድን ሰራተኛ

(አዲስ ዘይቤ-ሀዋሳ) "አሳ መመገብ እና መልካም ማሰብ እድሜን ያረዝማል" ይላሉ እድሜ ጠገቡ ብርቱ ሰው ጋሽ ሺፌ ካያሞ (ሾፌር) ። ጋሽ ሽፌ አቀላጥፈው መመለስ ቢቸግራቸው እንኳ ብዙ ቋንቋዎች ያዳምጣሉ፤ ጨዋታ አዋቂም ናቸው፡፡

በቀድሞ ስሙ የሲዳማ አውራጃ (አዳሬ) የአሁኗ ሀዋሳ ከተማ ተወልደው ያደጉት ጋሽ ሺፌ አብዛኞቹ የእድሜ እኩዮቻቸው አቺን አለም በሞት ተሰናብተዋል።

«የሀዋሳን ሀይቅ በዋና  አቋርጠው በመሻገር ወንዶ ጢቃ ደርሰው ተመልሰዋል» እንደሚባልላቸው አዲስ ዘይቤ ከተለያዩ ሰዎች መረጃን ስትቃርም አግኝታለች።

«እድሜዬን በውል ባላውቀውም 100 አልፎኛል:: ብዙ ሰዎች እራሳቸውን ለማጥፋት ዘለው ሀይቅ ውስጥ ይገባሉ፡፡ እነሱን የማውጣት ስራ የኔ ሀላፊነት ነው። በአንድ አጋጣሚም እራሱን ሊያጠፋ ሀይቅ የገባን ሰው አትርፌው ለምን አተረፍከኝ በሚል የግድያ ሙከራ አደድረርጎብኝም ነበር፡፡» ይላሉ ረጋ ባለው በትሁት አንደበታቸው፡፡

የአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ የቅስና ትምህርት እስከ አንደኛ ክፍል ድረስ መማራቸውን አጫውተውናል። ከዛም  ወታደር ቤት ገብተው ነበር፡፡

የሀዋሳ ሀይቅ ጀልባ መዝናኛ ሁለገብ ህብረት ስራ ማህበር (ፍቅር ሀይቅ) በቀን አበል ከ 25 እስከ 50 ብር ድረስ እየተከፈላቸው እርጅናን አሸንፈው የእለት ጉርሳቸውን ያገኛሉ፡፡

የማህበሩን ጀልባዎች ከሽርሽር ሲመለሱ ቦታ ማስያዝ፣ ማፅዳት እና ሰዎች ሀይቅ ውስጥ ሲሰምጡ የማውጣት፤ ህይወት የመታደግ ስራቸውን እድሜዬ ገፍቷል ብለው እንኳ አልተውትም ፤ አሁንም ብርቱ ናቸው።

"ቅን ናቸው ፈገግታ አይለያቸውም የብዙ ሰዎችን ህይወት ከባህር ወለል በታች ወርደው አውጥተዋል፣ አትርፈዋል። ሊመሰገኑ የሚገባቸውን ያህል አልተመሰገኑም" ሲሉ ይገልጿቸዋል። "አልተጠቀምንባቸውም! በሳቸው ላይ ብዙ መስራት እንችል ነበር፤ አሁንም እቅዱ አለን። ማህበሩም ከመመስረቱ በፊት ቀድመው አከባቢውን ያቀኑት እሳቸው ናቸው፡፡ እኛ ሳናስቸግራቸው መቀመጥ እርጅናን ያመጣል ብለው አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ያግዙናል፡፡ በማህበሩ ውስጥም መካሪያችን ናቸው" ይላል የሀዋሳ ሀይቅ ጀልባ መዝናኛ ሁለገብ ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ ጋምቡራ፡፡

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑትን አቶ በለው ገበየሁን ደግሞ ስለ ጋሽ ሽፌ ሳቅ እየቀደማቸው ሲያጫውቱን "አቶ ሺፌ ከአሳ ማህበር የእለት ስራቸው በኋላ አልፎ ከልፎ እኛ ቤት ይዝናኑ ነበር፡፡ ጎጄ ጠጅ ቤት የድሮው ፒያሳ የአሁኑ አዋሽ ህንፃ ያለበት 1979 ዓ.ም ገደማ ነው አስታውሳለሁ" ይላሉ "በሃያአምስት ሳንቲም ሁለት ሲጃራ እንድገዛላቸው ከላኩኝ በኋላ አምስት ሳንቲም ሽልማቴ ነበረች፡፡ ያኔ ሁለት አንጓ ሸንኮራ ይገዛ ነበር"

 እድሜ ጠገቡ ሰው መጠጣቸውን እየተጎነጩ ፈገግታ የማይለየው ፊታቸውን እየቸሩን «አሁን ላይ ሙሉ ጤነኛ ነኝ ገና እርጅና አልመጣም ይላሉ፤ ሙሉ እድሜዬንም ያሳለፍኩት እዚሁ ሀይቅ ላይ ነው።»(በሙሉነህ ካሳ)

(በሙሉነህ ካሳ)

አስተያየት