ታህሣሥ 2 ፣ 2013

ጅማ ዞን፡ ለ12 ዓመታት የተጓተተው መንገድ ነዋሪዎችን ለእንግልት ዳርጓል

City: Jimma

በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን፣ የሸቤ ሶምቦ-ሀንገጫ መንገድ ለ12 ዓመታት በመጓተቱ ምክንያት የወረዳው ነዋሪዎች ለእንግልት ተዳርገዋል። የሸቤ ሶምቦ-ሀንገጫ…

ጅማ ዞን፡ ለ12 ዓመታት የተጓተተው መንገድ ነዋሪዎችን ለእንግልት ዳርጓል

በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን፣ የሸቤ ሶምቦ-ሀንገጫ መንገድ  ለ12 ዓመታት በመጓተቱ ምክንያት የወረዳው ነዋሪዎች ለእንግልት ተዳርገዋል። የሸቤ ሶምቦ-ሀንገጫ መንገድ በኦሮሚያ ከልላዊ መንግስት እየተሰሩ ከነበሩት መንገዶች አንዱ ሲሆን መንገዱን ለመስራት ከተዋዋለው ተቋራጭ ጋር ባለመስማማታቸው ለ12 ዓመታት በመጓተቱ የወረዳው ነዋሪዎች ለተለያየ ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛና ለህገ-ወጥ አጓጓዦች መጋለጠቸውን ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር አዲስ ዘይቤ አጣርታለች፡፡

አቶ ናስር አባዝናብ የሸቤ ሶምቦ ወረዳ ነዋሪ ነው፣ መንገዱ ባለመሰራቱ ከተማረሩ የህብረተሰብ አካላት ውስጥ አንዱ ሲሆን ምሬቱን እንደዚህ ይገልፃል “መንገዱን የሰራው ኦሮሚያ ነው ይባላል፣ እስካሁን ሳያልቅ ግን ይኸው ለህገ-ወጥ አሽከርካሪዎች ዳርጎናል” ይላል “መንገዱ ትልቅ ችግር እያደረሰብን ይገኛል በአንድ ሞተር እስከ አምስት ሰዎች በመጫን እየዘረፉን ይገኛሉ አንድ አይሱዙ መኪና ከ60 በላይ፣ ሚኒባስ ደግሞ እስከ 25 ተሳፋሪዎችን እንደ ከብት እየጫኑን መጫወቻ አድርገውናል፡፡ ልጆችና እርጉዝ ሴቶች ታርጋ በሌላቸው በህገ-ወጥ ሞተሮች በመንገድ ላይ እየተገጩ ይገኛሉ፡፡ እያለቅን ነው፤ ለምንድን ነው የሚመለከተው አካል መፍትሄ የማይሰጠን?” ሲል ቅሬታውን ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል፡፡

ሌላኛው የሸቤ ሶመቦ ወረዳ ነዋሪ ነዚፍ አባዝናብም የአቶ ናስርን ሃሳብ ይጋራል፣ “በአይሱዙ መኪና፣ በሞተርና በግለሰብ ተሽከርካሪዎች ከአቅም በላይ እየጫኑን፣ ከአቅማችን በላይ እያስከፈሉን ስለሆነ መንግስት መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል” ይላል። ኤሊያስ አባራያም የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ሲሆን የመንገዱን ችግር ሲናገር “በኦሮሚያ ተሰራ የተባለው መንገድ በጣም እያሰቃየን ነው፡፡ አይሱዙ በ30 ብር፣ አንድ ሞተር እስከ አምስት ሰዎች በመጫን ከአንድ ሰው እስከ ሃምሳ ብር ያስክፍላሉ፡፡ ስለዚህ መንግስት አፋጠኝ መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል” ሲል ለአዲስ ዘይቤ አስረድቷል፡፡

በሸቤ ሶምቦ ወረዳ በ2001 ዓ.ም የተጀመረው የገጠር መንገድ ፕሮጀክት የወረዳውን ገጠር ቀበሌዎች ለማገናኘት የታለመ ሲሆን ዝቅተኛ የሥራ አፈፃፀም ማሳየቱን የወረዳው ኮንትራክተር አስተዳደር ቡድን ሀላፊ፣ አብደላ አወል ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል፡፡ ሀላፊው “የህዝቡ ቅሬታ ትክክል ነው የሸቤ ሶምቦ-ሀንገጫ መንገድ መጓተቱን እናውቃለን። የቅሬታው ምንጭ ስናጣራ በኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣንና በመንገዱ ተቋራጭ መሃል በነበረው አለመግባባት ህጋዊ ርክክብ ስላልተደረገ ኮንትራቱ እንዲቆም መደረጉ መሆኑን ደርሰንበታል” ያለ ሲሆን በ2012 ዓም ባለስልጣኑ ከጅማ ዞን ጋር በመነጋገር በዞኑ የጥገና ዘርፍ አማካኝነት ቀሪውን የመንገዱን ሥራ እንዲያጠናቅቅ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግሯል፡፡ በአሰራር ስርዓቱ መሰረት ህጋዊ ርክክብ ሳይፈጸም ጥገና ማድረግ እንደማይቻል ቢታወቅም መንገዱ እስካሁን ሁለቴ ጥገና እንደተደረገለትም አቶ አብደላ አንስቷል፡፡ 

የህዝቡ ችግር ለምን አልተፈታም ስትል አዲስ ዘይቤ ለሸቤ ሶምቦ ወረዳ መንገዶች ባለስልጣን የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ኢደሪስ ኑር ላቀረበችለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ እስከአሁን ህጋዊ ርክክብ ባለመደረጉ ምክንያት የትራንስፖርት ቢሮው ለመንገዱ ታሪፍ ለማውጣት ርክክብ የተደረገበትን ሰነድ ስለሚፈልጉ ታሪፉ ታውቆ፣ ተሽከርካሪዎች እንዲመደቡ ማድረግ እንዳልተቻለ ያነሳል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን፣ የመንገድ ጥገና ዳይሬክተር የጅማ ቅርንጫፍ ሀላፊ አቶ ንፍታሌም ነገሮ በበኩሉ “እኔ ስለ መንገዱ ፕሮጀክት ታሪክ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ፕሮጀክቱ ለምንና እንዴት እንደተቋረጠ አላውቅም፡፡ የጥገና ሥራውን እንዲሠራ በ2012 ዓ.ም ከኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን ጋር በመነጋገር ማሺነሪ አስገብተን ወደ ሥራው የገባን ሲሆን አሁንም ጥገናውን እያካሄድን እንገኛለን፡፡” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል፡፡

በተጨማሪም የጅማ ዞን መንገዶች ባለስልጣን ሀላፊ፣ ነጃት ከድር የመንገዱ ቁጥጥር በኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን ክትትል ስር ስለሆነ ስለ ፕሮጀክቱ ዝርዝር ሁኔታዎች ምንም እንዳማታውቅ ገልፃ፣ ፕሮጀክቱ ለምንና እንዴት እንደተቋረጠ አለማወቋን ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች፡፡ ሀላፊዋ በማከልም፣ “በኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን የተጻፈ ደብዳቤ ወደ መንገድ ጥገና ዘርፍ ጅማ ቅርንጫፍ መምጣቱንና መንገዱ ጥገና ስር መሆኑን ነው የማውቀው” ብላለች፡፡

እንደ የሸቤ ሶምቦ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ሀላፊው፣ ሁሴን አባተማም ገለፃ ከሆነ ለ12 ዓመታት በአግባቡ ሥራ ሳይጀምር የከረመው 18 ኪ.ሜ የሚሸፍን የሸቤ ሶምቦ-ሀንገጫ የጠጠር መንገድ ህዝቡን ለተያዩ ህገ-ወጥ አጓጓዦችና ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛዎች አጋልጧል፡፡ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ደግሞ በተለየዩ ህገ-ወጥ ሥራ የተሰማሩት ባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪዎች፣ ሞተር ሳይክልና ብስክሌት የወረዳውን ህዝብ አማርረዋል። 

አሽከርካሪዎቹም ተሳፋሪዎችን ለመጫን ሲሻሙ የተለያዩ ጉዳቶችን ሲያደርሱ እንደነበር ይነገራል፡፡ በመሆኑም የወረዳው ፖሊስ ከወረዳው አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ባደረገው ቁጥጥር በህገ-ወጥ ሥራ ተሰማርተዋል የተባሉ 150 ሞተሮችና 50 ብስክሌቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የወረዳው ኮምዪኒኬሽን ሀላፊ ተናገሯል፡፡ የተያዙት ሁሉም ተሽከርካሪዎች ሰሌዳ እንደሌላቸውና ከፊሉ ደግሞ የደቡብ ክልል ታርጋ እንዳለቸው ገልጾ፣ ህጋዊ እስኪሆኑ ድረስ ተሽከርካሪዎቹ ቁጥጥር ስር እንደሚቆዩ አቶ ሁሴን ለአዲስ ዘይቤ ተናገሯል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የታሰበ ነገር ካለ ብለ አዲስ ዘይቤ ለሀላፊዎቹ ላቀረበችው ጥያቄ፣ ከጅማ ዞን የመንገዶች ባለስልጣን ጋር በመነጋገር በጊዜያዊነት ሁለት ዶልፊን ተሽከርካሪዎች ህዝቡን  በትራንስፖርት እንዲያገለግሉ እንደተመደቡ በመግለጽ በዘላቂነት ግን መንገዱ ቶሎ መጠናቀቅ በሚችልበት ሁኔታ ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በመነጋገር ችግሩን እንደሚፈቱ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል፡፡ 

በስተመጨረሻም አዲስ ዘይቤ የመንገዱ ፕሮጀክት ለምንና እንዴት እንደተጓተተ፣ ከኮንትራክተሩ ጋር ለምን ስምምነት እንዳቋረጠ፣ ምንም አይነት ህጋዊ ርክክብ ሳይደረግ እንዴት ወደ ጥገና እንደተገባና የማን ጥፋት እንደሆነ በዝርዝር ለማጣራት ወደ ኦሮሚያ መንግዶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተርና የጥገና ዘርፍና የመንገድ ሀብት አስተዳደር ሥራስኪያጅ፣ አቶ አበራ አቦሼ እንዲሁም የሸቤ ሶምቦ-ሀንገጫ መንገድ ፕሮጅክትን ከመጀመሪያ አንስቶ ሲከታተል የነበረው  የባለስልጣኑ ባለሞያ፣ አቶ ጫለ አብዲን ለማናገር ያደረገችው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ አልተሳካም፡፡ (ወርቅነህ ድሪብሳ)

አስተያየት