ታህሣሥ 8 ፣ 2013

ከጎዳና ላይ ተሰብስበው በሜቴክ ስልጠና ያገኙ ወጣቶች ተቸግረናል አሉ

ዜናዎች

በመከላከያ ሰራዊትና በግብርና ሚኒስተር ድጋፍ ከሶስት ዓመታት በላይ በአፋር ክልል አዋሽ አርባ አካብቢ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሰልጥነው በስራ ላይ የነበሩ…

ከጎዳና ላይ ተሰብስበው በሜቴክ ስልጠና ያገኙ ወጣቶች ተቸግረናል አሉ
በመከላከያ ሰራዊትና በግብርና ሚኒስተር ድጋፍ ከሶስት ዓመታት በላይ በአፋር ክልል አዋሽ አርባ አካብቢ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሰልጥነው በስራ ላይ የነበሩ 522 ወጣቶች ተገቢውን ትኩረት ስላልተሰጣቸው በችግር ላይ እንገኛለን ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ አስታወቁ።በ2007 ሀገራዊ ምርጫ ወቅት ከተለያዩ ክልሎች ከጎዳና ላይ ተሰብስበው ለሥልጠና የተላኩት ከ10 000 በላይ ወጣቶችን በተለያዩ ሙያዎች በማብቃት ኃላፊነት የወሰደው የግብርና ሚኒስቴር ሲሆን ስልጠናውን ከሚሰጠው ኤልሻዳይ ሪልፍ ኤንድ ዴቨሎፕመን አሶሴሽን ነጥቆ ለየኢትዮጵያ ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን(ሜቴክ) ተሰጥቷል።  እንደኤልሻዳይ አይነት በዘርፉ የተሰማሩና ውጤታማ የሆኑ ድርጅትን ነጥቆ ምንም ልምድ ለሌለው መከላከያ መስጠቱ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል ሲሉ የድርጅቱ ሚዲያ ዳይሬክተር ነጋሽ በዳዳ የችግሩን መንስኤ ገልፀዋል።እንደሰልጣኞቹ ቅሬታ ከሆነ “በሰለጠነው መስክ ስራ የለም በሚል ምክንያት ከዚህ በፊት ሰርተነው የማናውቀውን የእርሻና የከብት እርባታ እንድንሰራ ተገደናል፤ ሆኖም በስኬት የተወጣነው ቢሆንም የትርፉ ተካፋዮች አልሆንም።  በስማችን የባንክ ሂሳብ ውስጥ የግባ ገንዘብም የለም።” ብለዋል።የኤልሻዳይ ድርጅት የሚዲያ ዳይሬክተር ነጋሽ በዳዳ አስተያየት ደግሞ “በመጀመሪያውና ሁለተኛው ዙር የሰለጠኑት ውጤታማ ሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በተለያዩ የመንግስት ሚንስቴር መ/ቤቶች ተቀጥረው በመስራት ላይ ይገኛሉ። አሁን ቅሬታ ያቀረቡት የ3ኛ ዙር ሰልጣኞች ‘ሰርዶ የተቀናጀ የግብርና ልማት ማእከል ስራ ማህበር’ በሚል ተቋቁመውዋል፤ በሰለጠኑበት መስክ የስራ እድል ባለመገኘቱ ወደ ግብርና ዘርፍ እንዲገቡ ተደርጓል፤ ተገቢውን ክፍያ ስለመፈፀሙ የባንክ ቤት ማስርጃዎች ማቅረብ ይቻላል። “ በማለት ተቀባይነት እንደሌለው ያስረዳሉ።ይህን ጉዳይ በበላይነት የሚመራው የግብርና ሚንስቴር ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።የልማት ማኀበሩ ተወካይ ወጣት አብደላ እንደሚለው ከሆነ ያለፈቃዳችን ከመምጣታችን በተጨማሪ ድጋፍ ሊያደርጉልን ቃል የገቡ ሚንስቴር መ/ቤቶች ምላሽ እየሰጡን አይደለም፤ አሁን የምንገኘው በጃንሜዳ ግቢ በድንኳን ውስጥ ነው። ሰሞኑን የዘነበው ዝናብም ለጤናችን አስጊ ሆኗል፤ በመካከላችን ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና ሴቶች ይገኛሉ ። ስለዚህ አፋጣኝ መፍትሄ እንፈልጋለን በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል።“እዚህ መቆየት አንፈልግም ወደ መጣንበት ሄደን ተደራጅተን እንስራ፤ አልያም መንግስት ያደራጀን ባሉት መስረት ወደየመጥጡብት ሄደው እንዲሰሩ የጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት በሰጠው ትእዛዝ ወደየክልላቸው እንደመጡና የመንግስትንን ይሁንታ የሚጠብቁት የተወሰኑት ሰልጣኞች ደግሞ በዚያው እንደሚገኙ በአፋር ክልል የስልጠና አስተባባሪው ኮ/ል ጋሻው ተናግረዋል። አያይዘውም “ወጣቶቹ ያቀረቡት ቅሬታ ከእውነት የራቀ ነው፤ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።” ብለዋል።ላለፉት ሦስት ዓመታት ያለአግባብ ጉልበታችን ተበዝብዟል፤ ጤናማ የሆነ የምግብ አገልግሎት አልቀረበልንም፤ በዚህም በርካታ አባላት ለህመም ተዳርገዋል፤ ለሚለው ቅሬታ ነጋሽ በዳዳ ምላሽ ሰጥተዋል። “እዚያ ያለው አባል በሙሉ የሚመገበው እንጂ ለሰልጣኞች ብቻ በተለየ መንገድ የሚሰራበት መንገድ እንደሌለና ከዚህ ቀደም ሲስራበት የነበረ ነው። የእንጀራ አቅርቦት እንዳናደርግ ደግሞ በየእለቱ እያቦኩ ለመጋገር ሁኔታዎች ስለማይመቹ ነው። ነገር ግን ይሄን መመገብ ለማይፈልግ የኪስ ገንዘብ በየወሩ ይሰጣቸውዋል።” ብለዋል።ኮ/ል ጋሻው በበኩላቸው ከኪስ ገንዘብ በተጨማሪ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እስከ 60,000 ብር የሚደርስ ድጋፍ እንደተደረገላቸውና እሳቸው በኃላፊነት ያስረከቡት የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ውጤታማ እንደሆነ ይገልፃሉ። ነጋሽ በዳዳ እንደሚሉት ከሆነ “ወደ አማራ ክልል የተመለሱት ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማድረጋቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል፤ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ለመቀበል ቃል የገቡ ድርጀቶች ግን ቃላቸውን ባለመጠበቃቸው ለዚህ ችግር እንደመንስኤ ይጠቀሳል፤ ኤልሻዳይ ግን ካለማንም ድጋፍ በራሱ የድንኳን መጠለያን ጨምሮ የኪስ ገንዘብ በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

አስተያየት