በምስራቅ ኢትዮጵያ የምትገኘው ድሬዳዋ ከተማ በጎርፍ አደጋ ክፉኛ ስትጎዳ የቆየች ሲሆን ሀምሌ 28፣1998 በጣለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ የድሬዳዋ ከተማ በጎርፍ መጥለቅለቋ የሚታወስ ነው፡፡ በጊዜው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉ፣ የብዙ ሰዎች ህይወት እንዲያልፍ እና በውል የማይታወቁ ሰዎች እንዲጠፉ ምክኒያት ሆኗል፡፡ ክስተቱ ለድሬዳዋ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያዊያንን ያሳዘነ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ አሁን ድረስ የጎርፍ አደጋ በከተማዋ የሚከሰት ሲሆን በነዋሪዎቿ ላይ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን አስከትሏል፡፡
ጎርፉ የሚያልፍበት መንገድ ከተማዋን በሁለት በሚከፍለው የአሸዋ መንገድ ላይ ሲሆን እዛ ላይ በተለምዶ ሰልባጅ ተራ ተብሎ በሚታወቀው የንግድ ስፍራ ውስጥ በንግድ ስራ እሚተዳደሩ ግለሰቦች የአደጋው ከፍተኛ ተጎጂዎች ናቸው፡፡
ገዛኸኝ አበበ በሰልባጅ ንግድ ስራ ለስምንት አመታት የሰራ ሲሆን ጎርፍ በመጣ ቁጥር ልብሶች፣ የጥላ እንጨት እና ሸራ በየጊዜው እንደሚወሰድበት እና በግርግር መሃል ዝርፊያ እንደሚያጋጥመው ይናገራል፡፡ በጎርፉ ምክኒያት መንገዱ ስለተበላሸ ወደውስጥ መግባታቸውን አክሎ ተናግርዋል፡፡ ሌላኛው በዚው በሰልባጅ ንግድ ስራ ላይ የተሰማራው አስፋው ይርጋ ለአንድ አመት ያህል እዚህ ቦታ ሲሰራ እንደቆየ እና በተደጋጋሚ ጊዜ ጎርፍ መከሰቱ ለጥላ የሚያቆመውን ሸራ፣ እንጨት እና ሸራ እንደሚወስድበት ለአዲስ ዘይቤ ገልፅዋል፡፡
አሸዋ (ሰልባጅ ተራ) ትልቅ ግብይት የሚከናወንበት የንግድ ማዐከል ሲሆን ከነምበርዋነን ወደ አሸዋ የሚሄደው አስፋልት በቀን ውስጥ ትልቅ የትራፊክ ፍሰት ያለበት ስፍራ ነው፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ግዜ ወዲህ አስፋልቱ በመደርመሱ ምክንያት በአካባቢው ላይ የትራንስፖርት ችግር አስከትሏል፡፡
በከተማዋ ነዋሪ የሆነችው አልማዝ በየነ ለረጅም ግዜ ከነምበርዋነን ወደ አሸዋ የሚሄደው አስፋልት ተጠቃሚ መሆኗን ገልፃ አስፋልቱ ከተደረመሰ በኃላ ታጥሮ እንደነበረ እና በዚያ ምክንያት በአካባቢው የነበረውን የትራንስፖር ፍሰት መዛባቱን ትናገራለች። “አሁን ደግሞ መጨናነቁን ለመቀነስ ታስቦ ነው በሚል ወደ ሳቢያን ለመሄድ ወይ በድሬዳዋ ምግብ ኮምፕሌክስ በኩል አሊያም በታይዋን ገበያ አዳራሽ በኩል ሆኗል መንገዱ በዚህ ሳቢያ በጣም እንግልት እየበዛብን ነው። በፊት 15 ደቂቃ የሚፈጅ መንገድ አሁን 30 እና ከዛ በላይ ይፈጃል” ብላለች፡፡
ሌላው በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ የከተማዋ ነዋሪ የሆነው ሃሰን ኡስማን፣ አስፋልቱ ከመደርመሱ በፊት መንገዱ ባለሁለት መስመር እንደነበር ከተደረመሰ ጀምሮ አካባቢው ላይ በጣም መጨናነቅ እንደመጣ ይገልፃል። “ከቅርብ ግዜ ወዲህ መጨናነቁን ለመቀነስ ባለአንድ መስመር በመደረጉ እዛው አሸዋ ውስጥ በፊት አዙረን የምነወጣውን አሁን ግን በአሸዋ አድርገን በድሬዳዋ ምግብ ኮምፕሌክስ አሊያም በታይዋን ገበያ አዳራሽ ነው ምንወጣው የሄ ደግሞ ለሹፌሮች ከታሪፉ አንፃር ሲታይ ኪሳራ ነው ለተሳፋሪውም ግዜ ማባከን ነው” ብልዋል፡፡
አቶ ደረጀ ፀጋዬ የድሬዳዋ መንገዶች ባለስልጣን ኃላፊ ነው። “ነምበርዋነን ከአሸዋ እሚያገናኘው መንገድ በ1990 ዓም የተሰራ ነው። ስፍራው የጎርፍ መሄጃ መንገድ ስለሆነ በሰአቱ በአርማታ (በኮንክሪት) የተሰራ አነስተኛ ጅረት ወይንም ፍሳሽ ውሀ መተላለፊያ መንገድ ላይ እንደ አማራጭ የሚሰራ መንገድ (ፎርድ) ተሰርቶ ነበር” ይላል። እንደ አቶ ደረጀ ገለፃ ከሆነ በሁለት ምክንያት በፎርዱ ላይ ጉዳት ሊደርሰበት ችሏል፡፡ “የመጀመሪያው ምክኒያት አካባቢው ላይ በሰልባጅ ልብስ ንግድ ላይ የተሰማሩት ግለሰቦች መንገድ ስለዘጉ ጎርፍ በሚመጣበት ሰአት በአንድ በኩል ብቻ እየወረደ ፎርዱ ላይ ጫና ፈጥሯል። ሌላኛው በአካባቢው ላይ ተደራጅተው በአሸዋ ጫኝ እና አውራጅ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ከሌላ ቦታ አሸዋ ማግኘት እየቻሉ ነገር ግን ፎረዱ ስር ተጠግተው አሸዋ ሲጭኑ ቦርዱ ያረፈበት አሸዋ ከስሩ እየተሸረሸረ በመሄዱ ፎርዱ ጉዳት አጋጥሞታል” ብልዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ ስራ እየተሰራ እንደሆነ አቶ ደረጀ ይናገራል። “ፎርዱ የተወሰነ ጥገና ተደርጎለት በስፍራው የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይቋረጥ፣ በንግድ ስራ የተሰማሩትን ነጋዴዎች ወደ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ እና ከሚመለከተው አካል ጋር በመተባበር የትራፊክ ፍሰቱን በተወሰነ መልኩ ወደ ሌላ አቅጣጫ የማሲያዝ ስራ ተሰርቷል” ብልዋል፡፡ “በተጨማሪም የዳሰሳ እና የዲዛይን ጥናት ተደርጎ ሙሉ በሙሉ መፍረስ እና እንደገና መገንባት እንዳለበት የተወሰ ሲሆን ነገር ግን የድሬዳዋ መንገዶች ባለስልጣን ቢሮ ለዚህ ስራ የተመደበ አመታዊ በጀት ስለሌለው ለአስተዳደሩ ካቢኔ ውሳኔ እንዲሰጥ አስተላልፈናል” ያለ ሲሆን አክሎም “ጉዳዩ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ በወረዳ ጨረታ ማውጣቱ ጊዜ ስላሚጠይቅ የከተማዋ ከንቲባ ይሄንን ተገንዝቦ ቅድሚያ እንዲሰጠው ጠይቀናል፤ የመጨረሻ ውሳኔ እየጠበቅን ነው” በማለት ለአዲስ ዘይቤ ገልፅዋል፡፡