ታህሣሥ 14 ፣ 2013

በዋርደር ከተማ ያለ ጥናት በተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶች ምክንያት የውሃ እጥረት ችግር ተከሰተ

City: Jigjiga

አዲስ ዘይቤ የህብረተሰቡን ቅሬታ ይዛ የዋርደር ከተማ የውሃ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ባሽር መሀመድ ሙሁመድን አነጋግራለች።

Avatar: Mohammed Hassen
Mohammed Hassen

journalism and communications graduate and an expert in communications affairs in the region and mobile journalist at Addis Zeybe.

በዋርደር ከተማ ያለ ጥናት በተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶች ምክንያት የውሃ እጥረት ችግር ተከሰተ

አብዱላሂ አሊ አብዲ የዋርደር ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ ነው። በሚኖርበት ከተማ የዉሀ እጥረት ችግር እንደሚያጋጥመው  ይናገራል።  በተለይም የ01,02 እና 04 ቀበሌ ነዋሪዎች በንፁሀ መጠጥ ዉሀ ችግር ለብዙ ጊዜ እየተሰቃዩ እንደሚገኙና በአስተዳደር ችግር ምክኒያት ከፍተኛ የአሰራር ችግር እንዳለ ይገልፃል።

ሁሴን ኑር ሚሰጠፍ ዩሱፍ የቀን ሰራተኛ ነው። አምስት ልጆች አሉት፣ ባላቤቱ ስራ የላትም የሚያገኘው ብር ከእጅ ወደአፍ እንደሆነና በዛ ላይ የዉሀ ችግር ሲጨመር መከራ እንደሆነበት ይናገራል። “በየቀኑ ብር አውጥተን ውሃ ለመግዛት አቅማችን አይፈቅድም የሚመለከተው አካል አቤቱታችንን ሰምቶ ይህንን ችግር እንዲቀርፍልን እንጠይቃለን” እያለ ምሬቱን ይገልፃል። 

አዲስ ዘይቤ የህብረተሰቡን ቅሬታ ይዛ የዋርደር ከተማ የውሃ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ባሽር መሀመድ ሙሁመድን አነጋግራለች።  አቶ ባሽር በወረዳዉ የሚኖር ህዝብ ቁጥር 145 ሺ እንዳለ ገልፅዋል። “በከተማው ውስጥ አምስት የዉሀ ጉድጎዶች አሉ ከእነዚህ መካከል የሚሰሩት ሁለት ብቻ ናቸው። ጉድጓዶቹ ጥናት ሳይደረግባቸው ነው የተቆፈሩት አሁን ግን በክልሉ ዉሃና ፍሳሽ ቢሮ ጥናት ተደርጎ  ችግሩ ተፈቶ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነዉ” ብሏል።

የዋርደር ከተማ ምክትል አስተዳደር አቶ አብዲሀክም ፍራህ ጅብሪል በበኩላቸው የሶማሊ ክልላዊ መንግስት ዉሃ ሀብት ልማት የዉሀ አቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ተናግሮ በዋርደር ከተማ የውሃ አቅርቦት ዲዛይን ላይ ጥናት እየተካሄደ እንደሆነ ገልፀዋል። “ከዚህ በፊት ክልሉን ሲያሰተዳድሩ የነበሩ ሰዎች ለግል ኮንትራክተሮች ፕሮጀክቶችን ሰጥተዋል፣ ኮንትራክተሮቹም ሀላፊነት በጎደለው መልኩ ስራዉን ሳያጠናቅቁ ቀርተዋል። ይህንን አሰራር ለመቀየር እና የንፁህ  ዉሃ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ከክልሉ መንግስት ጋራ አየሰራን እንገኛለን” ብልዋል።

አዲስ ዘይቤ በከተማው ውስጥ ስላሉት አምስት የውሃ ጉድጓዶች ሃላፊውን ጠይቃ ነበር። ማን እንደገነባቸው፣ ከተገነቡት መሃል ለምን ሶስቱ እንደማይሰሩ አንስታ ሃለጠየቀችው ጥያቄ ጉድጎዶቹ የተቆፈሩት ክልሉን ስያሰተዳድር በነበረው በአብዲ ኢሌይ ጊዜ እንድነበር እና  ፕሮጀክቱ ለሱ ቅርብ ለሆኑ ሰዎች ተሰቶ ከተመደበለት 65 ሚልየን ብር  60% ለኮንትራክተሮች እንደተከፈለ ተረድታለች።  “እኚህ ኮንትራክተሮች ባሁኑ ሰዓት ሃገር ውስጥ እንኳን የሉም” ያለው ምክትል አስተዳደር “የንፁሀ መጠጥ ዉሃ ችግር ከገጠመን ሶስት ወር አልፎታል ህዝቡ ያቀረበውን ቅሬታ ይዘን ከሚመለከተው አካል ጋር በቅርብ እየሰራን ነው። በጥያቄያችን መሰረት የክልሉ ዉሃ ልማት ቢሮ ባጭር ጊዜ ውስጥ ጥናት አድርጎ ጥናቱ 70% የደረሰ ሲሆን ጉድጓድ የሚቆፈርበት ምቹ የሆነ ቦታ በባለሞያዎች ተጣርቶ ወደ ስራ ከተገባ አንድ ወር አልፏል ፕሮጀክቱ  2014 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል” በማለት ምላሹን ሰቷል።  

አያይዞም “የክልሉን የውሃ ሽፋን በተገቢው መንገድ እንዲሰራበትና አጥጋቢ ውጤት ለማምጣት ከእቅድ ጀምሮ እስከ ትግበራ ድረስ የክልሉ ውሃ ሀብት ልማት ቢሮ ከፍተኛ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እስከ ቀበሌ ድረስ በመሄድ በየጊዜው ተከታታይ ክትትል እና ቁጥጥር እያደረጉ ይገኛሉ” ብሏል። 

አስተያየት