ታህሳስ 4 ቀን 2013 Mooyiiboon Dhuufeera የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ (432 ጓደኛዎች ያሉት አንድ የፌስቡክ አካውንት) ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ንምስረታ ሃገረ ትግራይ (31.2 ሺ አባላት ያሉት የፌስቡክ ቡድን) ተብሎ በሚጠራ የፌስቡክ ግሩፕ ላይ አራት የተለያዩ ምስልዎችን የያዘ የፌስቡክ ጽሁፍ ያጋራ ሲሆን የፌስቡክ ተጠቃሚው ግለሰብ በፌስቡክ መልዕክቱ የቀረቡት ምስሎች ላይ የሚታዩት የተጋጩ ተሽከርካሪዎች በ4 ታህሳስ 2013 ቀን በምዕራብ ጎንደር በዳንሻ ወረዳ ዘመቲን ቀበሌ በተከሰተ የትራፊክ አደጋ ወድመዋል ከሚል መረጃ ጋር አያይዞ አቅርቧል፡፡
የፌስቡክ ፅሁፉ አደጋው የ 38 ሰዎችን ህይወት እንደቀጠፈ ጠቅሶ የፌስቡክ ግሩፑ አባላት ለጓደኞቻቸው እንዲያጋሩት ይማጸናል። በተጨማሪም የፌስቡክ ጓደኞቹን ከጽሁፉ ጋር ተያይዞ የቀረበውን መስፈንጠርያ በመጠቀም የሟቾችን ማንነት በቴሌግራም ቻናል እንዲመለከቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ሆኖም በቴሌግራም ቻናሉ ላይ የሟቾች አስከሬን ፎቶ እንደተጠቀሰው አይገኝም፡፡ ሀቅ ቼክ ከዚህ በታች ያሉት ምስሎች ሰሞኑን በምዕራብ ጎንደር የተከሰተ የትራፊክ አደጋን እንደማያሳዩ አረጋግጧል ፣ በመሆኑም መረጃውን ሀሰት በማለት ፈርጆታል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የመኪና አደጋዎች ከሚከሰቱባቸው አገሮች መካከል አንዷ መሆኗ እርግጥ ነው። ባለፈው በጀት ዓመት በመላው አገሪቱ በትራፊክ አደጋ ምክንያት 4,133 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታ በአማራ ክልልም ከፍተኛ መጠን ያለው የመኪና አደጋዎች እንደሚከሰቱ የሚታወቅ ነው፡፡ አዲስ ዘይቤ በቅርቡ እንዳስነበበው ከሆነ በታህሳስ ወር የመጨረሻዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በባህር ዳር ከተማ ብቻ 59 የትራፊክ አደጋዎች ተከስተዋል። የትራፊክ አደጋዎቹ የ40 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን 25 ሰዎችን ለከባድ የአካል ጉዳት ዳርጓል። በተጨማሪም 19 ሰዎች ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ለአዲስ ዘይቤ በላከው መግለጫ መግለፁ የሚታወስ ነው። ስለዚህ መረጃው በአማራ ክልልና በአጠቃላይ በሀገሪቱ የትራፊክ አደጋ ከፍተኛ ችግር መሆኑን መረዳት ይቻላል።
ምስል 1:
ምስል 1: ትክክለኛ ምስል
በፌስቡክ ገጹ ላይ የተለጠፈው ምስል ሪቨርስ ኢሜጅ ሰርች በተሰኘ የምስል መፈተሻ መንገድ ሲፈተሽ የመኪናው አደጋ በምዕራብ ጎንደር እንዳልተከሰተ አመልክቷል። ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በፌስቡክ ላይ የተለጠፈው በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ነሐሴ 13 ቀን 2012 ዓ.ም ነበረ። ምስሉ ነሐሴ 2012 በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም በደጀና ወረዳ ዘመቲን ቀበሌ ላይ የተከሰተ የትራፊክ አደጋ ምስል ነው። በአደጋው የጭነት መኪና እና አውቶቡስ ተሽከርካሪዎች ተጋጭተው 39 ሰዎች ሲሞቱ 11 ሰዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተጨማሪም 26 ሰዎች ለቀላል ጉዳት ተዳርገዋል። በፌስቡክ ገጹ ላይ የሚገኘውን ልጥፍ በሚከተለው መስፈንጠርያ በመጠቀም ማግኘት ይችላል።
በዚህም መሰረት ሀቅቼክ መረጃውን በተመለከተ ባደረገው ማጣርያ በምስሉ ላይ የሚታየውን የትራፊክ አደጋ በምዕራብ ጎንደር ታህሳስ 4 ቀን 2013 ዓ.ም የተከሰተ የትራፊክ አደጋ እንዳልሆነ በማረጋገጥ መረጃውን ሀሰት በማለት ፈርጆታል።
አጣሪ: ሓጎስ ገብረኣምላኽ
አርታኢ: ብሩክ ነጋሽ ጠዕመ
ተርጓሚ፡ ቤዛዊት መስፍን
ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው።