ኩዒታ - Kuéta የተባለ ከ2100 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ ታህሳስ 10፣ 2013 ዓ.ም ወታደሮችን የሚያሳይ ምስል 2000 ኪ.ሜ የሚሆነው አከራካሪ ድንበር ሙሉ በሙሉ በሱዳን ቁጥጥር ስር መሆኑን እና ቅንጣት ያክል መሬቱን እንደማይስጡ የሚገልፅ ፅሑፍ አክሎ ለጥፏል። ከምስሉ ላይም የተፃፈው ፅሁፍ “... የሱዳን መንግስት ተጨማሪ ብዙ ሺ ማጠናከሪያ ሰራዊት ወደ ድንበር ማጓጓዙ ታውቁዋል፡፡ የግብጽ መንግስትም የሱዳን ሉአላዊነትን ከማስከበር አንጻር የትኛውንም አይነት ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል በመግባት ከሱዳን ጎን መሰለፉን አስታውቋል…” ሲል ይነበባል። ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት ከስር በምስሉ ላይ የሚታዩት የሱዳን ወታደሮች በቅርቡ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር የተፈጠረው ግጭት ላይ መሆናቸውን የሚያሳይ አለመሆኑን አረጋግጧል፤ ስለዚህ ሀሰተኛ ምስል መሆኑን አረጋግጧል።
ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮ-ሱዳን ድንበር በአማራ ሚሊሻ እና በሱዳን ወታደሮች መካከል ግጭት መከሰቱ የሚታወቅ ነው ሲሆን በ8 ታህሳስ 2013 ዓ.ም የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን እና የሱዳንን አዋሳኝ ድንበር ግዛቶች መቆጣጠሩን ገልጿል። ሰራዊቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያሉት ዓለም አቀፍ ድንበሮች ግልፅና የማያከራክሩ እንደሆኑና ሱዳን ከክልሏ ቅንጣት እንደማትሰጥ በወቅቱ መግለፁም ይታወቃል ፡፡ የሰራዊቱ መግለጫ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ዓለም አቀፍ ድንበር ግልፅ እና አጠራጣሪ አለመሆኑን የበለጠ ሲያብራራ ሱዳን ሉዓላዊ ግዛቷ በሌላ ሀገር እንዲተዳደር አትፈቅድም ብሏል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ፒ.ኤች.ዲ) በ8 ታህሳስ 2013 ዓ.ም በትዊተር ገፃቸው አስተዳደራቸው ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር የተፈጠረውን የድንበር ግጭት በቅርብ እየተከታተለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉት ግጭቶች የሁለቱን አገራት ትስስር አያፈርሱም በማለት ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ፍጥጫ አቃለውታል። ታህሳስ 13፣ 2013 ዓ.ም ሀገሪቱን የሚያዋስኑ ድንበሮችን ለመለየት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሱዳን ባለሥልጣናት ጋር በካርቱም ተነጋግረዋል።
በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ከላይ የተጠቀሰው መረጃ ቢሰራጭም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ ዘዴ እንደሚያመለክተው በመረጃው ላይ የተጠቀመጠው ምስል የተነሳው የቻይናው ዥንዋ ጋዜጣ ጋዜጠኛ በሆነው መሀመድ ባቢከር ሲሆን ምስሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው መጋቢት 4 2009 ዓ.ም (በፌስቡክ ተጠቃሚው ከመለቀቁ 3 አመት ከ9 ወር እና 6 ቀን በፊት) አላሚ በተባለው የእንግሊዝ ፎቶግራፊ ኤጀንሲ ነበር። ምስሉ 11,450 የሚሆኑ የሱዳን ፈጣን ድጋፍ ሰራዊት በካርቱም በተመረቁበት ወቅት በተካሄደ ሰልፍ የተነሳ መሆኑንም ሀቅቼክ አረጋግጧል።
Original Image:
በመሆኑም ምንም እንኳን መረጃው በፌስቡክ በተጋራበት ወቅት የሱዳን ጦር የኢትዮ-ሱዳን ድንበር አከባቢ ያለውን ቦታ መቆጣጠሩ እውነት ቢሆንም ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መረጃውን ለመደገፍ ተያይዞ የተለቀቀው ምስል ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው እና ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።
አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ
ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው
አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ
ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው።