ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በ2010 ዓ.ም "ጎንደርን ፍለጋ" ወጣሁ ብሎ ከዳባት እስከ ናበጋን፤ ከሀገረ ሰላም እስከ ጉና፤ ከደንበያ እስከ ሀረር፤ ከጎርጎራ እስከ ጃናሞራ፤ ከፋርጣ እስከ ደብረ ታቦር መኳተኑን ሳነብ ሀሞቴ ፍስስ አለ፡፡ ሰው እንዴት ከተማ አሰሳ ወጥቶ እንደ ሽፍታ በዱር በገደሉ ሲዞር ይከርማል?
እኔ እንደሁ ከሀዋሳ ሳልነሳ በሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት አሳብቤ ጥቁር ውኃ ሳልደርስ እንደ ሳንቡሳ ቂጣ ጥቅልል ብየ ተመለስኩ፡፡የቅርብ እሩቅ የሆነችውን ከተማ ለመቅመስ እንደጓጓሁ ቀረሁ፤ እንደተመኘሁ ሰነፍኩ፡፡
ጎንደር አለማየሁ ገላጋይ "መለያየት ሞት ነው" በሚለው መጸሀፉ እንዳስቀመጣት ናት፤ የህልም ከተማ! ታሪኳ ፊቴ ላይ ይመላለሳል፤ ትዝታዋ አይኔ ላይ ይንከላወሳል፤ ፍቅሯ ልቤ ላይ ይጎማሸራል፡፡ ጡት እደነጠቁት ህጻን ያብሰከስከኛል፡፡ የከተማው ቀለም እንደ ታቦት መጎናጸፊያ ያብረቀርቃል፤ የከተማው ነፋስ እንደ ይርጋ ጨፌ ቡና ይለሰልሳል፤ የከተማው እሴት እንደ ቁጫ ቅቤ ካንጀት ጠብ ይላል፡፡ መረጋጋት ተሳነኝ፡፡ አዝማሪው እንዲህ ያለው ለካስ ወዶ አይደለም፤
"ጸሀይ መውጫ ጎንደር
ንፋስ መውጫ ጎንደር
የማለዳ ጮራ፤ የ13 ወር ጸጋ
አንቺን ላልጎበኘ፤ ጨለማው አይነጋ"
ከተማዋን በምናቤ ስየ ጨርሻታላሁ፡፡ በባለ አስራ ሁለቱ በር የፋሲል ግንብ ስወጣ ስገባ፤ ከጃን ተከል ዋርካ ስር ሰቀመጥ ስነሳ፤ በእንኮየ መስክ ወዲያና ወዲህ ስል፤ በአንገረብ ወንዝ ዳር ቀለስ መለስ ስል አነጋለሁ፡፡ Cities and Urban Cultures በሚለው መጸሀፏ የምትታወቀው Deborah Stevenson (2003) እንኳን የነጻነት፣ የጥበብ፣ የብዘሀነትና የንግድ ማዕከል የሆኑትን ከተሞች አለመናፈቅ አይቻልም ትላለች፡፡ "እናት ዓለም" ጎንደር ከዚህ ከፍም ትላለች፡፡ ስሟ በሙዚቃው አድማስ ሁሌ እንደ ናኘ ነው፤ ገድሏ በታሪክ መዛግብት ነጋ ጠባ እንደተተረከ ነው፤ ግብሯ በሚድያው ሜዳ ሰርክ እነደተቀነቀነ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜማ ሀዋሳ ተኝቼ ጎንደር የነቃሁ ሁሉ ይመስለኛል፡፡ ቁስቋምን ተሳልሜ፣ በፋስል መዋኛ ለቅለቅ ብየ፣ በእቴጌ ምንትዋብ አዳራሽ ቁርስ አፌን አሟሽቼ ፣ በአጼ ዳዊት ቤተ መንግስት ጎርደድ ጎርደድ ካልኩ በኃላ ወደ አዲስ አለም ወርጄ ሼህ አሊን እዘይራለሁ፡፡ በእኔ ዓለም "የማያወቁት ሀገር አይናፍቅም" ይሉት ብሂል ፍሬ ከርስኪ ነው፡፡
አምና ግን ሞልቶልኝ አባይን ተሻገርኩ...
በ1627 ዓ.ም አፄ ፋሲል ጎንደር ሲደርሱ ይህ ነው የሚባል መንደር አልነበረም፡፡ ቀጥ ቢሉ የተራራ ሰንሰለት ነው፤ ዞር ቢሉ የደንበያ ሜዳ ነው፤ ወረድ ቢሉ የቀሃ ወንዝ ነው፡፡ “አጼው ቢቸግራቸው ህዝቡን በዋርካ ስር ይሰበስቡ ነበር” ይላል የአማራን ባህል የእጁ መዳፍ ያህል የሚያቀው ዶናልድ ሌቪን በWax and Gold መፅሐፉ፡፡ እኔም በ2012 ዓ.ም ጎንደር ስሄድ የከተማዋን ጓዳ ጎድጓዳ ለመመርመር ነዋሪው ለጥምቀት እስኪሰበሰብ መጠበቅ ነበረብኝ፡፡
የስበት ማዕከል (Center of Gravity)
ቤተ እምነት፣ ቤተ መንግስተና የገበያ ቦታዎች ለቀደምት ከተሞች መከተም ፣ መጽናትና መቀጠል ላይ የሚታይ ተጽዕኖ ማሰፋራቸውን በኢትዮጵያ ታሪክ ቀዳሚ የነበሩ ከተሞችን አከታተም ያጠናው Donald Crummey ይናገራል፡፡ እነዚህ ተቋማት የሰው ልጅ መስተጋብር እዲሳለጥና እንዲጠና ማህበራዊ መንገድ ያመቻቻሉ፡፡ የንግድ ስፍራዎች የህብረተሰቡ ፍላጎትና ጥያቄ የሆኑ ቁሶችን በማቅረብ ልውውጡ ፈር እንዲይዝ ያስችላሉ፡፡ የመንግስት ተቋማት በበኩላቸው ህዝብ በህግ የሚተዳደርበትን መንግስት ደግሞ የሚያሰተዳድርበትን መንገድ ያሳልጣሉ ፡፡ በሌላ በኩል ቤተ እምነቶች ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙበትን መንፈሳዊ መንገድ ያበጃሉ፡፡
ጎንደር ከእምነቱም አለችበት፤ ከሲራራ ንግዱም ነበረችበት፤ ለማዕከላዊ መንግስት መቀመጫነትም ለ200 ዓመታት አገልግላለች ፡፡ ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ ደግሞ ምንም እንኳን ሲቆረቆሩ ለውስን ሚና የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያ በርካታ ዘመናዊ ከተሞች ተመስርተዋል።
ለአብነትም እንደ መዲናችን አዲስ አበባ እና አንኮበር ያሉ ከተሞች አመሰራራታቸው ለወታደራዊ ካምፕነት፣ እንደ መቐለ ያሉ ከተሞች በፖለቲካ አስተዳደር ማዕከልነት እንዲሁም እንደ መንገድ ግንባታ እና ባቡር ዝርጋታ ያሉ መሰረተ ለማቶች እድገታቸውን ያፋጠኑላቸው ድሬደዋ እና ሀረር ከተማ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ጎንደርን ለማየት ጥምቀትን፤ ጥምቀትን ለማወቅ መንፈሳዊ ስነ ስረዓትን ፤ ሰርዓቱን ለመረዳት ደግሞ ስነ ሰብዕ (Anthropology) ምርጥ መነጸር ነው፡፡
ስነ ሰብዕ መንፈሳዊ ተግባራት ከራሱ ከከዋኙ ማህበረሰብ አለበለዚያ ከሰጠው ወይም ከተቀበለው ማህበረሰብ የወረሰው የራሱ ትርጉምና ፋይዳ እንዳላቸው ይገነዘባል፡፡ የዘመናዊው ስነ ሰብዕ አባት ተብለው ከሚጠቀሱት ጥቂት ምሁራን መካከል አንዱ የሆነው Bronislaw Malinowski (1922) የባህልንና የእምነትን ብያኔ በዝርዝር ጽፏል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ እምነትን ከግለሰባዊ ፋይዳ ጋር ብቻ በማቆራኘቱ ወደ በኃላ ነቀፋ ደርሶበታል፡፡ He agreed that function was a central issue but not the function that Malinowski and the “individualists” promoted. Rather, Radcliffe-Brown emphasized the needs of the group or of society. በሌላ በኩል ጉምቱው አንትሮፖሎጂስት A. R. Radcliffe-Brown (1881–1955) እምነትን ከማህበራዊ እና ቡድናዊ ፋይዳው ጋር አያይዞ ትርጉም ሰቶታል፡፡ በዋናነት የStructural functionalism ንድፈ ሀሳብ አቀንቃኝ የሆነው ራድክሊፍ ብራውን እንደሚለው የህበረተሰቡን መስተጋብርና ውህደት የሚያቀላጥፉት ማህበራዊ ተቋማት ወይም ተግባራት የሚሚዘኑት በጠቀሜታቸው ነው፡፡
በStructural functionalism ጽንሰ ሀሳብ መሰረት እምነት አንድ ማህበረሰብ ቀጣይነት እንዲኖረውና የጋራ ማንነት፤ ዕጣፈንታ፣ መነሻ እና መዳረሻ እንዲኖረው ያስችላል፡፡ Religion plays its most important role in the creation and maintenance of the group and society. So, as Durkheim stated, religion gives members of society a common identity, activity, interest, and destiny (Durkheim፤ 1965). ስለሆነም ነገረ ጥምቀትን (ከሀይማኖቱ ዳራ ባሻገር) እና እሴተ ጎንደርን የምለካው በዚህ የርዕዮት ’ቴርሞ ሜትር’ ይሆናል፡፡
44ቱን ደብር በጉያዋ ይዛ
በሰፊው አዳራሽ ቄጠማ ጎዝጉዛ
ባህረ ጥምቀቱን ታቦቱን አንግሳ
ኑ ትላለች ጎንደር በእጅጉ ደግሳ፡፡
የጥምቀት ለታ ጎንደር አንዳች ነገር ያደርጋታል፡፡ ታቦቱ ሲነገስና ጥምቀተ ባህሩ ሲቀደስ ደግሞ የከተማው ድባብ ወደ ልዩ ከፍታ ይሸጋገራል፡፡ የልጆቹ ፈገግታ የወጣቶቹ ዝማሬ እና የአዛውንቶቹ ፉከራ እንደተጠና የተውኔት ድግስ፤ እንደተቀመረ ሙዚቃ፤ በራሱ ዘዬ ኮለል ብሎ ይፈሳል፡፡ አምስቱም የስሜቴ ህዋሳት ስራ ላይ ናቸው፡፡ ብዙ ሰው ከነ አያሌ ቀለሙ አያለሁ የቀሳውስቱ ጥላ፣ የታቦታቱ አልባሳት፤ የቅዱሳን ስዕላት። ብዙ ድምጽ ከነ ውህደቱ እሰማለሁ መዝሙሩ፣ ሆያ ሆየው፣ እልልታው። ብዙ አካል እነካለሁ የዘመድ ጉንጭ፣ የመስቀል፣ የእምነት አመድ። ብዙ ሽታ ከነምናምንቴው ያውደኛል የእጣን፣ የሽቶ፣ የናፍቆት። ብዙ ነገር ከነ ጥፍጥናው እቀምሳለሁ ጸበል፣ ጠላ፣ ዳቦ ወ.ዘ.ተ፡፡
ጥምቀት ሰውና አምላክን ብቻ ሳይሆን ሰውና ሰውንም ያገናኛል፡፡ የቃሉ ትርጓሜ አጥመቀ፤ አጠመቀ፤ ነከረ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ መሆኑን የሀይማኖቱ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ የአማርኛ ፍቺው ደግሞ መላ ሰውነትን በውኃ ውስጥ መንከር ወይም ማጥመቅ ማለት ነው፡፡
ከተራ የሚል ሰያሜ በተሰጠው በዋዜማው ጥር 10 ከ44 በላይ የሆኑት ታቦታት ከአብያተ ክርስቲያናቱ ወደየባህረ ጥምቀቱ መንፈሳዊ ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ በማግስቱ የጥምቀት ዕለት "ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ" ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ የሚል ያሬዳዊ ዝማሬ ከካህናቱ ይሰማል፤
እዩት ወሮ ሲመለስ
መድኃኔዓለም በፈረስ
ወሮ ሲመለስ
የሚካኤል አንበሳ
ሎሌው ሲያገሳ፡፡
እያሉ የሚዘምሩ ወጣቶች፤ ባለ ጥለት ሴቶች፣ ፍልቅልቅ ህጻናት ታቦታቸውን ይሸኛሉ፡፡ እነዚህ ደማቅ ኩነቶች ከሀይማኖታዊ ፋይዳቸው ባሻገር በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ጤናማ መስተጋብር ያንጸባርቃሉ፡፡ ከሀይማኖቱ ሀገር በቀል ባህሉም እጅግ የሚደምቀበት ነው፡፡ ይህ እሴት በርግጥም በኮሚቴና በአበል ብቻ ተሰናድቶ በትኩሱ የቀረበ ለብ ለብ አይደለም፡፡ የተደከመበት፤ የሁሉንም ላብ የጠየቀና በጥልቅ ፍላጎት የሚከወን "ተግባረ ፍቅር" መሆኑን ስነ ስረዓቱ ይመሰክራል፡፡
ወደ ፋሲለደስ መዋኛ እየተመምን ነው፡፡ እንደ አምፑላንስ መብራት ቦግ ያለ ቀይ ጥለት፤ እንደ ጤዛ የሚለሰልስ አረንዴ ጥለት፤ እንደ ሱፍ አበባ ከሩቅ የሚስብ ቢጫ ጥለት እዛም እዚህም ይውለበለባል፡፡ በየቀሚሱ፤ በየጃኖው እና በየአካባቢው ላይ ፈሶ የሚታየው የሀገር ምልክት ነው፤ የሀገር ፍቅር ነው፤ የሀገር ጌጥ ነው፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም የሚዘንብ ይመስላል፡፡ በምትበር ባጃጅ ላይ፤ በሚያሳሳ ብላቴና ጉንጭ፤ በእድሜ ባለጸጋ መቋሚያ ላይ፤ በየሰፈሩ (አራዳ፣ ፒያሳ፣ መስጊድ) የውስጥ ለውስጥ መንገድ፤ በየንግድ ተቋም ውስጥ "ያችን ባንድራ" ታዩዋታላችሁ፡፡ በበኩሌ ጥምቀትን እያከበርኩ ይሁን ኢትዮጵያን እየሞሸርኩ ድብልቅልቅ ብሎብኛል፡፡ ይህንን ልብ የሚያሞቅ ትዕይንት ታዝቦ ነው መሰል አቀንቃኙ ቴዲ አፍሮ "ጎንደር ጎንደር የቴዎድሮስ ሀገር፤ ያንዲት ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር" ሲል የገለፀው፡፡ ሙሉቀን ፈቃዴና ጓደኞቹ በበኩላቸው እኤአ በ2018 በሰሩት የጥናት ወረቀት የጎንደር እሴት ሁሉን አካታች እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ It is also important to reiterate that the Gondarian values have holistic nature as Gondar is one of the icons of the Ethiopian center of religion and culture that glued national unity፡፡
በበርግጥ የጎንደር ጥምቀት በገለጻ ብቻ የሚያልቅ የአደባባይ በዓል አይደልም፤ በመተግበር እንጂ፡፡ ከሽኝቱ ሲሳተፉ፤ ከጨዋታው ሲቋደሱ፤ ከገንዳው ሲዋኙ፤ ከጸበሉ ሲቀመሱ የከተማው ትልቅነት ወለል ብሎ ይታያል፡፡ የታሪክ መዛግብት እንደሚነግሩን ጎንደር ከመመስረቷ ከ300 ዓመት በፊት የአጼ አምደ ጽዮን ዜና መዋዕለ ላይ ጎንደር የሚለው ስም ሰፍሯል፡፡ ሲሳይ ሳህሌ የተለያየ አፈታሪኮችን አጣቅሶ እንደጻፈው "ጎንደር የሚለው ቃል የማን እንደሆነ ባይታወቅም ’ጉንደ ሀገር’ (የሀገር ግንድ) ወይም ታላቅ ሀገር ማለት ነው"፡፡ ታዲያ ከዚህ ትልቅ ከተማ ማንስ ይቀራል? ያውም በጥምቀት?